ዋልያዎቹ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለማግኘት ተቃርበዋል

በመጪው የዓለም አቀፍ ጨዋታዎች የጊዜ ሰሌዳ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንዲያገኝ የተጀመረው ንግግር ለመሳካት ከጫፍ ደርሷል።

የዓለም አቀፍ የብሔራዊ ቡድኖች አህጉራዊ ጨዋታዎች እና የአቋም መፈተሻ ፍልሚያዎች ከቀጣዩ ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ እንደሚከናወን ይታወቃል። በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የነጥብ ጨዋታ የሚያደርግበት መርሐ-ግብር ባይኖረውም ወቅታዊ አቋሙን እንዲገመግም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እንዲያገኝ ሲጥር ቆይቷል። በዚህም ብሔራዊ ቡድኑ ከሊቢያ አቻው ጋር ወደ ትሪፖሊ በማቅናት ጨዋታ እንዲያደርግ ንግግሮች ተጀምረው የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ውጥኑ ሳይሰምር እንደቀረ ሶከር ኢትዮጵያ ተረድታለች።

የሊቢያው ጨዋታ ባይሳካም ብሔራዊ ቡድኑ ከሱዳን አቻው ጋር እንዲፋለም ድርድሮች እየተደረጉ የሚገኝ ሲሆን በሁለቱ አካላት መካከልም አዎንታዊ ውጤቶች እየተገኙ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታም አዲስ ነገር እስካልተፈጠረ ድረስ እዚሁ ሀገራችን አዲስ አበባ አልያም አዳማ ከሚገኙት አበበ ቢቂላ ስታዲየሞች መካከል በአንዱ ሊደረግ እንደሚችል ሰምተናል።

ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በተያያዘ ዜና ውላቸው ሊገባደድ የቀናት እድሜ ብቻ የቀረው የአሠልጣኝ ውበቱ አባተ ጉዳይ ከሰሞኑን እልባት እንደሚያገኝ ይጠበቃል። አሠልጣኙ እና ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት የደረሱ መሆኑ ሲመላከት ቀሪ ዝርዝር ጉዳዮች ተገባደው በቅርቡም ውላቸው መራዘሙ በይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚበሰር ተጠቁሟል።