ፈረሰኞቹ ለካፍ ደብዳቤ አስገብተዋል

በሳምንቱ መጨረሻ ከአል-ሂላል ጋር ላለባቸው የመልስ ጨዋታ ወደ ሱዳን መጓዝ ያለባቸው ቅዱስ ጊዮርጊሶች አስቀድመው ለካፍ ደብዳቤ ማስገባታቸው ታውቋል።

በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ የቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ ባሳለፍነው ሳምንት በባህር ዳር ስታዲየም የሱዳኑን አል-ሂላልን ገጥመው 2-1 በሆነ ውጤት የረቱት ፈረሰኞቹ በዚህ ሳምንት መጨረሻ የመልስ ጨዋታቸውን ካርቱም ላይ እንዲያደርጉ ቀጠሮ መያዙ ይታወቃል። ከጨዋታው አስቀድሞ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በኩል ለካፍ ደብዳቤ መላካቸውን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች።

የተላከው ደብዳቤ ፍሬ ሀሳብ ሱዳን አሁን ካለችበት ወቅታዊ የፀጥታ አለመረጋጋት በመነሳት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁን በማንሳት ጨዋታውን በዚህ ሀገር ማድረግ ከደህንነት አንፃር ስጋት በመሆኑ ካፍ ጨዋታውን በገለልተኛ ሜዳ እንዲያካሂድ መጠየቅን እንደሆነ ተመላክቷል።

በሌላ በኩል እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ የሱዳኑ ክለብ አል-ሂላል ለቅዱስ ጊዮርጊሶች የመምጫ ጊዜያቸውን እንዲያሳውቁ የጠየቀ ሲሆን በፈረሰኞቹ በኩል እስካሁን ምላሽ እንዳልተሰጠ አውቀናል። አሁን የሚጠበቀው የእግርኳሱ የበላይ አካል ካፍ የሚሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ የሚጠበቅ ሲሆን ካፍ ውሳኔውን ዛሬ እስከ ከሰዓት ድረስ ያሳውቋል ተብሎ ይጠበቃል።