እስካሁን በይፋ ሳይሾሙ በሥራ ላይ የነበሩት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በሁለት ዓመት ውል ኢትዮጵያ መድንን ተረክበዋል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከስምንት ዓመታት በኋላ ዳግም በመመለስ ተሳታፊ መሆኑን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በከፍተኛ ሊግ ተሳትፎዎ ያረጋገጠው ኢትዮጵያ መድን ለ2015 የሊጉ ውድድር በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን በማስፈረም እንዲሁም ደግሞ የነባር ተጫዋቾችን ውል በማራዘም የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን የአዲሱን አሰልጣኝ ቅጥር ይፋ ሳያደርግ በአዳማ ከተማ እየሰራ ይገኝ ነበር፡፡
ክለቡ እስከ ትላንት በስቲያ ድረስ የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን ሹመት ይፋ ሳያደርግ ሰንብቶ አሁን በይፋ መቅጠሩን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡ አሰልጣኙም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቀርበው ለሁለት ዓመት ክለቡን ለማሰልጠን ፊርማቸውን ስለማኖራቸው የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ይግዛው ብዙዓየው ለዝግጅት ክፍላችን አሳውቀዋል፡፡ ከሲዳማ ቡና ጋር በነበራቸው ቀሪ የውል ዘመን እና የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ጋር በተገናኘ የአሰልጣኙ ቅጥር ይፋ ሳይሆን የቀረበት ጉዳይ ስለመሆኑም አውቀናል፡፡
ከክለቡ ጋር በተያያዘ ቡድኑ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ መሆኑ የተረጋጋጠ ሲሆን ሦስት የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸውን ተጫዋቾችን ለማስፈረም በሂደት ላይ መሆኑን ሰምተናል፡፡