የሀገራችንን ከፍተኛ የሊግ እርከን የሚመራው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር 3ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በቀጣዩ ሳምንት መጀመሪያ ያከናውናል።
ከሦስት ዓመታት በፊት በፕሪምየር ሊጉ ክለቦች የተመሰረተው አክሲዮን ማኅበር ከዓመት ዓመት በተለያዩ መስፈርቶች መሻሻል እያሳየ ውድድሩን በጥሩ ሁኔታ እየመራ እንደሚገኝ ይታወቃል። ማኅበሩ ሊጉ ገንዘብ እንዲያመጣ የሥያሜ እና የቴሌቪዥን መብቱን ሸጦ በዓመቱ መጨረሻ ከገቢው ክፍፍል በመፈፀም የአባል ክለቦቹን ኪስም እያሳደገ ይገኛል። የ2015 የውድድር ዓመትንም በተሻለ ሁኔታ ለመምራት ዝግጅቱን እያገባደደ እንደሚገኝ የሚገልፀው ማኅበሩም ከሊጉ ጅማሮ አስቀድሞ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በመዲናችን ለማድረግ ቀጠሮ ይዟል።
የዓምናውን ውድድር አፈፃፀም በተመለከተ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች እንደሚነሱበት የሚጠበቀው የማኅበሩ 3ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ የፊታችን ሰኞ መስከረም 9 በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ከጠዋቱ 2:30 ጀምሮ የሚከናወን ሲሆን አባል ክለቦች እና እንግዶችም ጥሪ እንደተላለፈላቸው ታውቋል።