ቡናማዎቹ ኬኒያዊ የግብ ዘብ ለማግኘት ተቃርበዋል

በአሠልጣኝ ተመስገን ዳና የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና የውጪ ዜጋ የግብ ዘብ ወደ ስብስቡ ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሷል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በሊጉ 6ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ኢትዮጵያ ቡና ያለፉትን ሦስት ዓመታት ቡድኑ ከመሩት አሠልጣኝ ካሣዬ አራጌ ጋር ተለያይቶ ተመስገን ዳናን የቀጠረ ሲሆን በዝውውር መስኮቱም የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ለ2015 የሊጉ ውድድር እየተዘጋጀ ይገኛል። በሀዋሳ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሲያደርግ የሰነበረው ቡድኑም ለአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ከትናንት በስትያ ወደ መዲናችን በመምጣት ለቡ በሚገኘው የተጫዋቾች ካምፕ ዝግጅቱን ቀጥሏል።

በቅርቡ ጋናዊውን የመሐል ተከላካይ ኩዋኩ ዱሃን ያስፈረመው ክለቡ አሁን ደግሞ የግብ ዘብ ለማግኘት መቃረቡን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች። ከሳምንት በፊት የደቡብ አፍሪካ የብዙሃን መገናኛዎች ዩጋንዳዊው ግብ ጠባቂ እስማኤል ዋቴንጋ ቡናማዎቹን ዳግም በአንድ ዓመት የውሰት ውል ሊቀላቀል ከጫፍ ደርሷል በማለት የተለያዩ ዘገባዎችን ሲሰሩ የነበረ ቢሆንም ዋቴንጋ ግን ማሩሞ ጋላንትስን ተቀላቅሎ በደቡብ አፍሪካ ሊግ እየተጫወተ ይገኛል። ይህንን ተከትሎ ሌላ የግብ ዘብ ለማግኘት ሲጥሩ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ኬኒያዊውን ግብ ጠባቂ ሆሳኖ ጃኮብ ለማስፈረም ከጫፍ መድረሳቸውን ድረ-ገፃችን አውቃለች።

ለሀገሩ ክለቦች ናይሮቢ ስቲማ፣ ጎር ማሂያ እና ናይሮቢ ሲቲ ስታርስ ተጫውቶ ያሳለፈው ሆሳኖ ጃኮብ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ወደ ሀገራችን የመጣ ሲሆን ከትናንት ጀምሮ ከቡድኑ ጋር ልምምድ መስራት እንደጀመረ ታውቋል። አዲስ ነገር እስካልተፈጠረ ጊዜ ድረስም ተጫዋቹ በቅርቡ በይፋ ለቡናማዎቹ ፊርማውን እንደሚያኖር ይጠበቃል።

ያጋሩ