ከአዲሱ የዐፄዎቹ ተጫዋች ታፈሰ ሰለሞን ጋር የተደረገ ቆይታ

👉”ፋሲል ትልቅ ክለብ ነው ፤ ትልቅነቱን ደግሞ ሊጉ ላይ ብቻ ሳይሆን በዚህ መድረክም ማሳየት እንፈልጋለን”

👉”ኢትዮጵያ ቡናን ስቀላቀል ደስተኛ ነበርኩ ፤ ግን ከተወሰነ ወቅት በኋላ ብዙም ደስተኛ አልነበርኩም”

👉”ጎል በማግባቴ ደግሞ ደስ ብሎኛል። ከዚህ በኋላም ያሉትን ጨዋታዎች በጥሩ ብቃት ፋሲልን ለማገልገል ተዘጋጅቻለው”


👉”ከዲሲፕሊንም ጋር ተያይዞ ከዚህ በኋላ ፈፅሞ የፋሲል ከነማን ስም በእኔ ምክንያት እንዲጠራ አልፈልግም”

ፋሲል ከነማ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ በሜዳው የብሩንዲውን ቡማሙሩን አስተናግዶ 3ለ0 በሆነ ውጤት ሲረታ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አዲሱ የክለቡ ፈራሚ ታፈሰ ሰለሞን የማሳረጊያዋን ግብ በድንቅ ሁኔታ ከመረብ ማዋሀዱ ይታወሳል፡፡

ዐፄዎቹ ወደ ታንዛኒያ ከማማራታቸው አስቀድሞ አዲስ አበባ ላይ ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን በቆይታቸውም የቀድሞው የኒያላ ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና የአማካይ ስፍራ ተጫዋች የነበረው እና በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት የጎንደሩን ክለብ የተቀላቀለው ታፈሰ ሰለሞን በገለልተኛ ሜዳ ነገ ስለሚደረገው የመልስ ጨዋታ እና ስለአዲሱ ክለቡ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል፡፡

አዲሱን ቡድንህን እንዴት አገኘኸው…?

“ፋሲል ከነማ ጠንካራ ቡድን ነው። ቡድኑን በመቀላቀሌም መጀመሪያም ተናግሪያለሁ ደስተኛ ነበርኩ ፤ ክለቡንም እንደጠበኩት ነው ያገኘሁት። ትልቅ ቡድን የመጣው በመሆኔ በጣም ደስታ ተሰምቶኛል።”

አቅም እንዳለህ ሀገር ውስጥ ያሉ ደጋፊዎች ሁሉ ይመሰክራሉ በአህጉራዊ መድረክ ይሄን ብቃትህን ለማሳየት ምን ያህል እየሠራህ ነው…?

“ኢትዮጵያ ቡናን ስቀላቀል ደስተኛ ነበርኩ ግን ከተወሰነ ወቅት በኋላ ብዙም ደስተኛ አልነበርኩም። ከላይ ባሉ የቦርድ አመራሮች ሙሉ ለሙሉ ደስተኛ አልነበርኩም። ክለቡ በግሉ አቡበከርን ኮከብ አድርጎ በሸለመበት ሰዓት ጥሩ የሚባል አቅሜን እያሳየሁ ነበር። ለቀጣይ ዓመትም የተሻለ ነገር ለመስራት አቅጄ ነበር። በቦርዱ እና ከላይ ባሉ አመራሮች ምክንያት ሞራሌም ስለተነካ የመጫወት ፍላጎት አልነበረኝም። ፋሲል ከመጣሁ በኋላ ግን የአሰልጣኞች ቡድኑ አባላት ወጣቶች ናቸው። ደስ ይላሉ ፤ በሁሉንም ነገር እያገዙኝ ነው። አቅሜን ከዚህ በላይ ለማሳየት ከፋሲል ጋር ጠንክሬ እየሠራሁ ነው።”

ዓርብ ያቺን ድንቅ ግብ ካስቆጠርክ በኋላ ምን ተሰማህ…?

“አንደኛ የመጀመሪያ ጨዋታዬ ነው። ተቀይሬም ነው የገባሁት ፤ ጎልም አስቆጥሪያለሁ በዚህ በጣም ደስተኛ ነኝ። ከዚህም በላይም ጎል ማግባት እንችል ነበር። እውነት ለመናገር ካገባሁ በኋላም በጣም ነው ደስ ያለኝ። ከአሰልጣኜም ጋር ሳወራ ነበር። በብዙ ተፅዕኖ ውስጥ ሆኖ የዲሲፕሊን ችግር ያለበት ተጫዋች አስፈረመ ሲባል ነበር። ከጨዋታው በፊት በነበሩት ቀናት ከአሰልጣኜ ጋር ስለዝግጅት ጊዜያችን እያወራን እየተነጋገርን ነበር እርሱ እንደ ወንድም ይመክረኝ ነበር። ሁለም የአሰልጣኞች አባላት ጠንክሬ እንድሰራ ይመክሩኛል ፤ ደስ የሚል ግንኙነት ነው ያለን። በሕይወቴ ላይም ትልቅ ለውጥ እንዳመጣ ተፅዕኖ አድርገዋል። በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ።ከዚህ በኋላም ያሉትን ጨዋታዎች በጥሩ ብቃት ፋሲልን ለማገልገል ተዘጋጅቻለው።”

ፋሲል በምትጫወትበት ቦታ ላይ ሌሎች ተጫዋቾችም አሉ፤ ይሄንን ፉክክር እንዴት እየተጋፈጥከው ነው…?

“አብዛኞቹ ብሔራዊ ቡድን ላይ የማውቃቸው ናቸው። የእኔ የራሴ አቅም አለኝ። እንደዚህ አይነት ፉክክር በአንድ ቡድን ውስጥ ሲኖር ደግሞ ጥሩ ነው። እንደው ሌላም ተጨማሪ ተጫዋቾች ቢኖር ደስ ይለኛል። ያው የአሰልጣኞች ውሳኔ ነው ፤ እነሱ ያሉት ነው የሚሆነው። እንዳልኩት የእራሴ አቅም አለኝ። በዚህ ደስተኛ ነኝ። ፉክክር ሲኖር ግን ጥሩ ነው።”

በዘንድሮ የውድድር ዓመት ሜዳ ላይም ከሜዳ ውጪም ታፈሰ በምን መልኩ ተሻሽሎ ይቀርባል……?

“እኔ ሜዳ ላይ በተሻለ ደረጃ እየተጫወትኩ ነበር። አንደኛ ቡና ቤት ግብ አላስቆጥርም። ለግብ አመቻችቼ የማቀብለው ግን እኔ ነበርኩ። አሁን ግን ወደ ጎል ማስቆጠር እየገባው ነው። ለዚህም የቡድኑ አጨዋወት ጠቅሞኛል። ጎልም እንዴት ማስቆጠር እንዳለብኝ እየሠራው ነው። ሌላው ከዲሲፕሊንም ጋር ተያይዞ ከዚህ በኋላ ፈፅሞ የፋሲል ከነማን ስም በእኔ ምክንያት እንዲጠራ አልፈልግም። ቡና ቤት ብዙ ይባላል። ጠጪ ነው ይባላል። ብዙ ስም እየተጠቀሰ ሰዎች ይፅፉ ነበር። ይሄ ይሄ ነገር ከፋሲል ጋር ፈጽሞ የለም። ከዚህ በኋላም አይኖርም።”

ግብ ካስቆጠርክ በኋላ ሁለት አይነት የደስታ አገላለጽ አሳይተሃል። መልዕክት አለው…?

“አንደኛ እኔ ያሰብኩት ሌላ ነበር። ሚስቴን ለመግለጽ ቀለበቴን ለመሳም ነበር ያሰብኩት። አብረውኝ ያሉት ልጆች ግን ስላገባሁ ሁሉም ጋር ስለምግባባ ደስታቸው እነርሱ በሚፈልጉት መልኩ ለመግለፅ ችያለው። ያም በማስከተል እንደ አንቶኒ ያሳየውን ትዕይንት ማን እንደሆነ አላውቅም ሲያሳየኝ እሱን አይቼ አልኩኝ እንጂ ለባለቤቴን ነበር መጀመሪያ ደስታ መግለፅ የፈለግኩት።”

የፋሲል ደጋፊዎችን እንዴት አገኘሃቸው…?

“የፋሲል ደጋፊ የታወቁ ናቸው። ሊጉ ላይም ስፖርታዊ ጨዋነት ያላቸው በጣም ድንቅ ደጋፊዎች ናቸው። አቀባበልም ሲያደርጉልኝ ነበር። አይተህ ከሆነ የባለፈው ጨዋታ በጣም ደስ የሚል ድባብ ነበር። ስታዲየሙ ከዚህ የበለጠ ይሞላል ብዬ ነበር። ያው ሀገሪቱ ላይ ባለው ሁኔታ ብዙም አልተገኙም። ያም ቢሆን የመጡትም በጣም ሲደግፉን ነበር። እነርሱንም ማመስገን እፈልጋለሁ። በዚህ ዓመትም የተሻለ ውጤት አስመዝግበን እነሱን ማስደሰት እንፈልጋለን።”

ከነገው የመልስ ጨዋታ ምን እንጠብቅ…?

“ለመልሱ ጨዋታ እየተዘጋጀን ነው ፤ ሊቀለበስ ስለሚችል ገና አላረጋገጥንም። በኳስ ምንም ነገር ማመን የለብንም። አይተህ ከሆነ ባርሳ ከ ፒኤስጂ ስድስት አስቆጥረው ነው የተቀየረው እና መዘናጋት የለብንም። ሁላችንም ከአሰልጣኞች አባላት የተሰጠንን ትዕዛዝ እንዳንዘናጋ ነው። የመልሱን ጨዋታ በጥንቃቄ ተጫውተን በማለፍ ከቱኒዚያውን ክለብ ጋር በብቃት ለመጫወት እናስባለን። ፋሲል ትልቅ ክለብ ነው ብየሃለው ፤ ትልቅነቱን ደግሞ ሊጉ ላይ ብቻ ሳይሆን በዚህ መድረክም ማሳየት እንፈልጋለን። ተጫዋቾቹም በጣም አቅም አላቸው። በአብዛኛው ብሔራዊ ቡድን ይተዋወቃሉ፣ እርስ በእርስ ይከባበራሉ። አሰልጣኞቻችንም እንደምታያቸው ወጣቶች ናቸው ብዙ መሥራት ይችላሉ። ከአሰልጣኞቹ ጋር በመሆን አንድ ነገር ለመስራት የሚያቅተን ነገር የለም ብዬ ነው ማስበው።”

ያጋሩ