የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታችን ብሔራዊ ቡድን ስድስት ተጫዋቾችን ሲቀንስ አስቀድሞ ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾችም ቡድኑን ተቀላቅለዋል።
በአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ እየተመራ በቀጣዩ ሳምንት ለአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ የመጀመሪያው ዙር የማጣርያ ጨዋታውን ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ብሔራዊ ቡድኑ 37 ተጫዋቾችን በመያዝ ዝግጅቱን መጀመሩ ይታወሳል።
ብሔራዊ ቡድኑ ምንም እንኳን በመጀመርያው ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል አብዛኛዎቹ በብሔራዊ ቡድን እና ክለቦቻቸው ካሉባቸው ተደራራቢ ጨዋታዎች አንፃር የቡድኑን ስብስብ የተሟላ ባያደርገውም በተለያዩ ጊዜያት ለአዳዲስ ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ 25 ተጫዋቾችን በመያዝ የመጨረሻው የዝግጅት ምዕራፍ ላይ የደረሰ ይመስላል።
የዝግጅቱ አካል በማድረግ የተለያዩ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ያደረገው ብሔራዊ ቡድኑ በዛሬው ዕለት ስድስት ተጫዋቾችን መቀነሱን ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች። እነርሱም አስጨናቂ ፀጋዬ፣ አሰጋኸኝ ጼጥሮስ፣ ሳሙኤል ተስፋዬ፣ ብዛዓየሁ ሰይፈ፣ አዲሱ አቱላ እና ኬኔዲ ከበደ ናቸው።
በቡድኑ ውስጥ አስራ ዘጠኝ ተጫዋቾች የቀሩ ሲሆን ከትናንቱ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ማግስት ዛሬ ረፋድ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ልምምዳቸውን ሲሰሩ ዘጠኝ ተጫዋቾች ሲገኙ የተቀሩት አስሩ የፓስፖርት ጉዳይ ለማስተካክ ሳይገኙ ቀርተዋል። አስቀድሞ ከኢትዮጵያ ቡና ከተጠሩት መካከል ኃይለሚካኤል አደፍርስ፣ ብሩክ በየነ፣ ጫላ ተሺታ እና መሐመድኑር ናስር ብሔራዊ ቡድኑን መቀላቀላቸውን ተመልክተናል።
ጨዋታውን ለማድረግ ሰባት ቀን የቀረው ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣይ ቀናት ከፋሲል ከነማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ጥሪ የተደረገላቸውን ተጫዋቾች ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን መስከረም 12 በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የመጀመርያ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።