በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ የመልስ ጨዋታ ታንዛኒያ ላይ ቡማሙሩን የገጠሙት ፋሲል ከነማዎች 3-1 በሆነ የድምር ውጤት በማሸነፍ ተከታዩን ዙር ተቀላቅለዋል።
ፋሲል ከነማዎች ከቀናት በፊት ባህር ዳር ስታዲየም ላይ የቡሩንዲውን ቡማሙሩን 3-0 በረቱበት ጨዋታ የተጠቀሙበት የመጀመሪያ ተመራጭ ስብስብ ላይ ለውጥ ሳያደርግ የዛሬውን ጨዋታ ማድረግ ችለዋል።
በመጀመሪያው ጨዋታ ሽንፈት ያስተናገዱት ቡማሙሩዎች በዛሬው ጨዋታ ገና ከጅምሩ ጫና በመፍጠር የጀመሩበት ነበር ፤ ምንም እንኳን በኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው ቢመስልም ወደ ማጥቂያው ሲሶ በመድረስ ግን እድሎችን ለመፍጠር ተቸግረው ተመልክተናል።
በአንፃሩ ፋሲል ከነማዎች በተለይ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ያለ ኳስ ቦታዎችን በመዝጋት የጥንቃቄ አጨዋወት ላይ አተኩረው ተመልክተናል ፤ በዚህም በተደራጀ መልኩ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ 13 ያክል ደቂቃዎችን ለመጠበቅ ተገደው ነበር።
ቀስ በቀስ በጨዋታው ከመስመሮች በሚነሱ ኳሶች አደጋ መፍጠር የጀመሩት ቡማሙሩዎች በተለይም ከግራ መስመር ወደ ሳጥን በሚጣሉ ተደጋጋሚ ኳሶች ፋሲልን ሲፈትኑ አስተውለናል ፤ ታድያ በ22ኛው ደቂቃ ላይም ከግራ መስመር መነሻውን ያደረገ ኳስ በግንባር ተገጭቶ ለቡድናቸው ተስፋን የፈነጠቀች ግብ ማስቆጠር ችለዋል።
ግብ ካስተናገዱ በኃላ በተሻለ እርጋታ ኳሱን መቀባበል የጀመሩት ፋሲል ከነማዎች የጨዋታውን እንቅስቃሴ በተጋጣሚያቸው አጋማሽ በማድረግ ወደ ቡማሙሩ ሳጥን ተጠግተው እድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ አስተውለናል በዚህም ሱራፌል ዳኛቸው በ30ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ወደ ግብ የላካትን ኳስ ጨምሮ ሦስት ጥሩ ጥሩ እድሎችን ፈጥረው መጠቀም ሳይችሉ የመጀመሪያው አጋማሽ በቡሩንዲው ቡድን መሪነት ተጠናቋል።
ከሳጥን ሳጥን መመላለሶች በበዙበት የሁለተኛው አጋማሽ ቡማሙሩዎች ተጨማሪ ግቦችን ፍለጋ ከመጀመሪያው አጋማሽ አንፃር ይበልጥ ቀጥተኝነትን ጨምረው ለመጫወት ጥረት ያደረጉበት ሲሆን በአንፃሩ በንንፅር የተሻለ አጀማመርን ያደረጉት ፋሲሎች ደግሞ በፈጣን ቅብብሎች ለማጥቃት ጥረት ሲያደርጉ ተመልክተናል።
መጣደፉችን በሁለቱም ቡድኖች በኩል በተመለከትንበት በዚሁ አጋማሽ ፋሲል ከነማዎች በንፅፅር የተሻለ መልኩ ወደ ማጥቃት ቀጠናዎች መድረስ ቢችሉም የተጫዋቾቻቸው ፍፁም እርጋታ ያልተከለባቸው ውሳኔዎች ጉዳይ ሆነ እንጂ ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር በቻሉ ነበር።
በ70ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ እና ታፈሰ ሰለሞንን በሀብታሙ ገዛኸኝ እና በዛብህ መለዮ ምትክ ቀይረው ያስገቡት ፋሲሎች በተቀሩት ደቂቃዎች በተወሰነ መልኩ ጨዋታውን ለመቆጣጠር እና ያለአግባብ የሚባክኑ ኳሶችን ለመቀነስ ሙከራ ሲያደርጉ ተመልክተናል።
ጨዋታው በቡማሙሩዎች የ1-0 የበላይነት ቢጠናቀቅም ኢትዮጵያን የወከሉት ፋሲል ከነማዎች 3-1 በሆነ የድምር ውጤት በማሸነፍ በቀጣዩ ዙር የቱኒዚያውን ሴፋክሲያንን የሚገጥሙ ይሆናል።