የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ከጎፈሬ ጋር በመተባበር የሚያዘጋጀው የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሽፋን እንደሚያገኝ ታውቋል።
ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከናወነው የጣና ዋንጫ ውድድር የሥያሜ መብቱን ለአማራ ባንክ በ5 ሚሊዮን ብር ሸጦ በደማቅ ሁኔታ በባህር ዳር ከተማ እንደሚከናወን ይታወቃል። ውድድሩም ድሬዳዋ ከተማ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ባህር ዳር ከተማ እና ኮልፌ ተስፋ እንዲሁም ተጋባዦቹ የዩጋንዳ ክለቦች ቡል ኤፍ ሲ እና ሞደርን ጋዳፊን በማሳተፍ ከመስከረም 8 እስከ 14 ድረስ ይደረጋል። ገና የውድድሩን ጥንስስ ያበሰረው ጋዜጣዊ መግለጫ ከወራት በፊት ሲሰጥም አዘጋጆቹ ውድድሩ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት እንደሚያገኝ ጠቁመው እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን ይሁ ሀሳብ እውን ሆኖ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚከናወነው ውድድር በአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የቴሌቭዢን አማራጭ አማራ ቲቪ እንደሚተላለፍ ተረጋግጧል።
ከቅድመ ውድድር ዝግጅቶች አንዱ ተደርጎ የሚወሰደው ይህ ውድድር የመክፈጫ ጨዋታው የፊታችን እሁድ ሲከናወን አማራ ቲቪ የሚያስተላልፈው ሲሆን እስከ ፍፃሜው ድረስ ያሉ የተመረጡ ተጠባቂ መርሐ-ግብሮችንም ስታዲየም የማይገባ የስፖርት ቤተሰቦች በያሉበት እንዲመለከቱ እንደሚደረግ የውድድሩ የማኅበራዊ ሚዲያ አጋር የሆነችው ሶከር ኢትዮጵያ ከአዘጋጆቹ አረጋግጣለች።