ባህር ዳር ከተማ የመስመር አጥቂውን በቋሚ ዝውውር አስቀርቷል

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በውሰት በባህር ዳር ከተማ የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን አጋማሽ ያሳለፈው የመስመር አጥቂ በይፋ የጣና ሞገደኞቹ ንብረት ሆኗል፡፡

ባህር ዳር ከተማ በ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ ካለፈው ዓመት በተሻለ ቁመና ላይ ለመገኘት የበርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ዝውውር ሲፈፅም ቆይቷል። ነገ በሚጀመረው የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የሆነው ክለቡ ራሱን በማጠናከሩ በመቀጠል የወጣቱን የመስመር አጥቂ አደም አባስን ዝውውር በይፋ አጠናቋል፡፡

ከኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ የተገኘው እና በኢትዮ ኤሌክትሪክ እንዲሁም የተጠናቀቀውን ዓመት በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ በተደለደለው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጥሩ ጊዜን ያሳለፈው አደም አባስ የከፍተኛ ሊግ ውድድር በጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ በውሰት ውል ለባህርዳር ከተማ በፕሪምየር ሊጉ ሁለተኛው ዙር በመጫወት ግልጋሎት ሰጥቷል፡፡ እስከ ነሀሴ 30 2014 ድረስ በንግድ ባንክ ውል የነበረው ተጫዋቹ ውሉ መጠናቀቁን ተከትሎ በሁለት ዓመት ውል በይፋ የጣና ሞገደኞቹ ተቀላቅሏል፡፡