ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ለማድረግ ቀጠሮ የያዘችው ሱዳን ለፍልሚያዎቹ ስብስቧን ለይታለች።
የሀገራት ይፋዊ ጨዋታዎች ከቀጣዩ ሳምንት አጋማሽ ጀምሮ የሚከናወኑ ሲሆን የነጥብ ጨዋታዎች የሌለባቸው ብሔራዊ ቡድኖችም የወዳጅነት ጨዋታዎችን ለማድረግ እየተሰናዱ ይገኛሉ። ሶከር ኢትዮጵያም ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዚህ የቀን ሰሌዳ ከሱዳን ጋር ጨዋታ ለማድረግ እየተነጋገረ እንደሆነና በሁለቱም ወገኖች መካከል አዎንታዊ ውጤቶች እየተገኙ እንደሆነ ጠቁማ ነበር። አሁን ደግሞ ከሱዳን ብሔራዊ ፌዴሬሽን ባገኘነው ልዩ መረጃ መሠረት የሱዳን ብሔራዊ ቡድን ከዋልያዎቹ ጋር ላለበት ፍልሚያ ለ24 ተጫዋቾች ጥሪ ቀርቧል።
በአሠልጣኝ ቡሩሀን ቲያ የሚመራው የሱዳን ብሔራዊ ቡድን መስከረም 13 እና 16 ለሚደረጉት ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ለ3 የግብ ዘቦች፣ 8 ተከላካዮች፣ 7 አማካዮች እና 6 አጥቂዎች ጥሪ አስተላልፏል። ከተጠሩት ተጫዋቾች መካከል 12 ተጫዋቾች ዛሬ በባህር ዳር ስታዲየም ከጂቡቲው አርታ ሶላር ጋር ከተፋለመው የአል-ሜሪክ ክለብ ሲገኙ 8 ተጫዋቾች ደግሞ ከነገው የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚ አል-ሂላል መመረጣቸው ታውቋል።