ጣና ዋንጫ | ሞደርን ጋዳፊ ባህር ዳር ከተማን ሦስት ለምንም አሸነፈ

በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ የዩጋንዳው ክለብ ሞደርን ጋዳፊ የውድድሩን አዘጋጅ ከተማ ክለብ ሦስት ለምንም ረቷል።

በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ የመክፈቻ ጨዋታ የተገናኙት ባህር ዳር ከተማ እና ሞደርን ጋዳፊ ሞቅ ባለ የደጋፊዎች ድባብ ታጅበው የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አከናውነዋል። ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የውድድሩ ተሳታፊዎችን እና አጋር ተቋማትን የሚያመሰግን ትዕይንት የተከናወነ ሲሆን በማስከተል የዕለቱ የክብር እንግዳ የሆኑት የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ ድረስ ሳህሉን (ዶ/ር) ጨምሮ የአማራ ባንክ፣ የወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ እና ጎፈሬ አመራሮች ተጫዋቾችን እንዲተዋወቁ ተደርጓል።


የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ወስደው ጨዋታውን ለመከወን ያለሙት ባህር ዳር ከተማዎች የተጋባዦቹን ሞደርን ጋዳፊ ተጫዋቾች ፍጥነት እና ሀይል የተቀላቀለበት እንቅስቃሴ መቋቋም ሳይችሉ ገና በጊዜ እጅ መስጠት ጀምረዋል። ጨዋታው ገና እንደተጀመረ በ5ኛው ደቂቃም ሞደርን ጋዳፊዎች ከማዕዘን የተሻማው ኳስ ሲመለስ በቀኝ በኩል ተቀባብለው የተሻገረውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ሙሲጊ ቻርልስ በቀላሉ በግንባር ገጭቶ ግብ አስቆጥሮ መሪ ሆነዋል።

በምክትል አሠልጣኙ ደረጄ መንግስቱ እየተመሩ ሜዳ የገቡት ባህር ዳሮች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ጠንካራውን የተከላካይ ክፍል አልፎ ግብ ማስቆጠር ተስኗቸዋል። ይባስ በጨዋታው ግማሽ ሰዓት ሴረንኩማ ሲማህ ከመዓዘን ምት በቀጥታ ድንቅ ግብ አስቆጥሮባቸው ሁለተኛ ግብ አስተናግደዋል። በእንቅስቃሴ ረገድ ግን ወደ ቀኝ ያደላ የማጥቃት አጨዋወት ለመከተል ቢወጥኑም እምብዛም ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል።


ጨዋታውን በሚፈልጉት መንገድ እየዘወሩ የነበሩት ሞደርን ጋዳፊዎች ያልተረጋጋውን የባህር ዳር የኋላ መስመር ስህተት በመጠቀም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር መንቀሳቀስ ይዘዋል። በ40ኛው ደቂቃም ውጥናቸው ሰምሮ 3ኛ ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው ሙሲጊ ቻርልስ በመልሶ ማጥቃት በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ከተከላካዮች አምልጦ በመውጣት በጥሩ አጨራረስ የቡድኑን መሪነት ወደ ሦስት አሳድጓል።

አጋማሹን በወረደ አፈፃፀም ያገባደዱት ባህር ዳር ከተማዎች ወሳኙ ተከላካያቸውን ፈቱዲን ጀማል በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በጉዳት ቢያጡም በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ የመናበብ፣ የአቋቋም እና የውሳኔ ችግር የነበረበትን የተከላካይ መስመር ለማረጋጋት ሞክረዋል። ይህ ውጥናቸው ሰምሮም በሁለተኛው አጋማሽ ብዙም ሳይፈተኑ ከእጃቸው ያመለጣቸውን ውጤት ለማግኘት መጣጣር ላይ ትኩረት አድርገው መንቀሳቀስ ጀምረዋል። ይህ ቢሆንም ግን በቁመት ዘለግ ዘለግ ያሉትን የመሪዎቹን ተከላካዮች ሰብሮ መግባት አልሆን ብሏቸዋል። ሞደርኖች ግን ያገኙትን ውጤት ማስጠበቅ ላይ ተጠምደው አጋማሹን ከውነዋል።


በፍፁም ጥላሁን ፍጥነት እንዲሁም በቻርለስ ሪባኑ የከረሩ የርቀት ኳሶች ከጨዋታው አንዳች ነገር ይዞ ለመውጣት ባህር ዳሮች ቢያልሙም ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩት ሦስት ግቦች ፍፃሜውን አድርጓል።

ከመርሐ-ግብሩ ፍፃሜ በኋላ በጨዋታው ሁለት ጎሎችን ያስቆጠረው ሙሲጊ ቻርልስ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ ተመርጦ ከጎፈሬ ትጥቅ አምራች ተቋም መስራች አቶ ሳሙኤል መኮንን ሽልማቱን ተረክቧል።


ከጨዋታው በኋላ የምድቡ መሪ የሚሆኑበትን ውጤት ያገኙት የዩጋንዳው ክለብ ሞደርን ጋዳፊ ዋና አሠልጣኝ ዋስዋ ቦሳ “ጨዋታው ጥሩ ነበር። በምንፈልገው መንገድ ተጫውተናል። ተጫዋቾቻችንም ያልናቸውን አድርገዋል። ሀሳባችን በመልሶ ማጥቃት መጫወት ነበር። እርሱን አሳክተናል። ይህንን ውድድር እንደ አቋም መፈተሻ ጨዋታ ነው የምናየው። የዩጋንዳ ፕሪምየር ሊግ በቅርቡ ስለሚጀመር የተጫዋቾቻችንን ውህደት እና አቋም ለማምጣት እንጠቀምበታለን። ይህ ቢሆንም ግን ይህንን የአማራ ባንክ የጣና ዋንጫ ውድድር ለማሸነፍ ነው ሀሳባችን።” የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የተሸናፊው ክለብ ምክትል አሠልጣኝ ደረጄ መንግስቱ በበኩላቸው “ጨዋታው ጥሩ ነው ማለት ይቻላል። እንደ መጀመሪያ ጨዋታ ኳስን መሠረት አድርገን ለመጫወት ነው የሞከርነው። በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ነገር ለማድረግ ሞክረናል። ጨዋታው እንዳያችሁት ኃይል የተቀላቀለበት ነበር ፤ እነሱ የሚጠቀሙት ጉልበትን ሚዛናዊ ያደረገ ጨዋታ ነው። ሁሉም የተጎዱብን ተጫዋቾች ከነሱ ጋር በነበረ ንክኪ ነው። የነሱ የአጨዋወት መንገድ ተጫዋቾቻችን እንዲጎዱ አድርጓል። ቋሚ ቡድን አይደለም ወደ አምስት ተጫዋቾች በብሔራዊ ቡድን እና በጉዳት የሉም ፤ እነሱ በሁሉም ነገር ሜዳ ላይ ከኛ የተሻሉ ናቸው። ሜዳው ለአዳዲስ ተጫዋቾች አዲስ ነው ፤ የመጀመሪያ ግብ ሲቆጠር የመውረድ ነገር ይኖራል። በሁለተኛው አጋማሽ ለውጥ አይተናል። ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ነበር። ዋናው አላማችን ዋንጫውን ለማሸነፍ ሳይሆን ቡድን ለመሥራት እና የጨዋታ ዝግጁነታቸንን ለማምጣት ነው።” የሚል ሀሳባቸውን አጋርተውናል።