ሉቺያኖ ቫሳሎ በአሥራት ኃይሌ አንደበት

– “እርሱ የሚያይህ እንደ ልጁ ነው። የሚቆጣጠርህም እንደ አስተማሪ ነው።”

– ” ሉቻኖ አንበሳ ያደርግሃል። ፈሪ የነበርክ ብትሆን እንኳ ሉቻኖ ደፋር ያደርግሃል። “

– ” ተጫዋቾቹ ኢትዮጵያውያን ልጆቼ ናቸው። የአገሬ ልጆች መሞት የለባቸውም። የተከለከለ ነገር የሚወስዱበት ምክንያት የለም።” ይል ነበር። ያ ሁሉ የደረሰበት ይህንን ስላወጣና ስላጋለጠ ነው። በጊዜው እኛ ስለመዳኒቱ ምንም አናውቅም ነበር።”

– “. . .  ውክልና ለእኔ ሰጠኝ። ዶክመንቶቹ እስካሁን ድረስ ቤቴ አሉ። . . . “

– “ጣልያን እንደሄደ ባለቤቱ አረፈች፤ ልጁም አረፈበት። በዚያ ላይ በጣም ሃብታም የነበረ ሰው በአንዴ ንብረቱን ሁሉ አጥቶ ባዶ ቀረ። . . . ” 

– ” እነ አቶ ይድነቃቸው ፣ መንግሥቱ፣ ሉቻኖ … እነዚህ ሰዎች የኢትዮጵያ ትልቅ ባለውለታ የነበሩ ሰዎች ናቸው። እነርሱ ካልተከበሩ ማን ሊከበር ነው? “

– “. . . እንዲህ አይነት የአገር ፍቅር ያለውን፣ ታሪክ የሰራን ባለውለታ ምናለበት ከንጉሱ ዋንጫ ሲቀበል የተነሳው ፎቶ እንኳ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ውስጥ በትልቁ ቢቀመጥ?


በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ከምርጦቹ ረድፍ የሚሰለፈው ሉቺያኖ ቫሳሎ መስከረም 6 ቀን 2014 ዓ.ም በ87 ዓመቱ ኑሮውን ባደረገባት ጣልያን ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቶናል። የታሪካዊው እና ብቸኛው የአፍሪካ ዋንጫ ድላችን ፊት አውራሪ የነበረውና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በርካታ ጨዋታ ካደረጉ ታላላቅ ተጫዋቾች መካከል ግንባር ቀደም የነበረው ሉቻኖ ቫሳሎ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ የነበረው አበርክቶ እና አጠቃላይ የእግር ኳስ ህይወቱ በአግባቡ ለትውልድ ሳይተላለፍ እና የሚገባው ክብር ሳይቸረው በሞት ብናጣውም በቅርበት ከሚያውቁት የእግር ኳስ ግለሰቦች አንደበት በተከታታይ ፅሁፎች እንዘክረዋለን። በዛሬው ዝግጅትም በሉቺያኖ ቫሳሎ ስር በአሰልጣኝነት እና በቡድን አጋርነት በጥጥ ማህበር ተጫውቶ ያሳለፈው አንጋፋው አሰልጣኝ እና የቀድሞ ተጫዋች አሥራት ኃይሌ ”እንደ አባቴ የማየው” ስለሚለው ሉቺያኖ ቫሳሎ ይህን አጋርቶናል።  

የሉቻኖና የአንተ ትውውቅ ከየት ይጀምራል?

ሉቻኖ በወጣትነቴ ያገኘሁት ሰው ስለሆነ አሰልጣኜም ፤ አባቴ ነው ማለት ይቻላል። የተጫዋችነት ህይወቴን የቀየረና በእግርኳስ እዚህ ደረጃ እንድደርስ ያደረገኝ ሉቻኖ ነው። “መወለድ ቋንቋ ነው።” አይደል የሚባለው? እንደ አሳዳጊዬም፣ እንደ አባቴም ነው የማየው። ለእርሱ ትልቅ አክብሮትና ፍቅር አለኝ። እኔና ሉቻኖ የተገናኘነው በ1963 ዓ.ም. ነው። ያን ጊዜ የ22-23 ዓመት ወጣት ነበርኩ። ከአዲስ አበባ ተጫዋቾች ሊወስድ ለምርጫ ሲመጣ አስራት ዳፍላን ያገኛል። ከአስራት ዳፍላ ጋር አንድ ሰፈር ነበርን። በእርግጥ አስራት የእኛ ሲኒየር ነበር። ቀደም ብሎም ለመብራት ኃይል ተጫውቷል። ሉቻኖ እርሱን ያገኝና ” ተጫዋቾች እፈልጋለሁ። በአንተ ምልከታ ጥሩ-ጥሩ ወጣት ተጫዋቾች የምትላቸውን ጥቆማ አድርግልኝ።” ሲለው አስራት ካሳሁን ተካንና እኔን ይጠቁመናል። ያኔ ካሳሁን ጠመንጃ ያዥ ፥ እኔ ደግሞ ዳርማር ነበር የምንጫወተው። ሉቻኖ መጀመሪያ ካሳሁንን ነው የወሰደው። እኔን ዳርማር “ታስፈልገናለህ፤ አንለቅህም” አሉኝ። ያኔ ኮንትራት የለም። አንዴ ላይሰንስ ላይ ከፈረምክ የምትወጣው በእነርሱ (በቡድኑ ኃላፊዎች) ፈቃድ ብቻ ነበር። የመልቀቂያ ፈቃድ ካልተሰጠህ የትም መንቀሳቀስ አትችልም። በአስራት ዳፍላ ጥቆማ መሠረት ካሳሁንና እኔ ነበር የተመረጥነው። ካሳሁን ቀድሞኝ ሄደ። እኔ ልዑል መኮንን ት/ቤት እየተማርኩ ነበር ዳርማር የምጫወተው። በአጋጣሚ የተማሪዎች ግርግር ይነሳና ትምህርት ይዘጋል። እኔ ወደ ጨዋታው አተኮርኩ። ዳርማሮች ወደ መጨረሻው ዓመት ላይ የዓመቱ ውድድር ካለቀ በኋላ በመከራ መልቀቂያ ሰጡኝ። ሉቻኖ በሰው ስልክ እየደወለ ያገኘኝ ነበር። እኔም ‘ከዳርማሮች ጋር ጨርሻለሁ።’ ስለው ” በቃ በቀጥታ ና!” አለኝ። በዚያን ጊዜ በባቡር ነበር የሚኬደው። በ10 ብር ከ20 ሳንቲም ድሬዳዋ ገባሁ። በሉቻኖ በመፈለጌ ደስታ ስለሰጠኝ ቶሎ መሄድን ብቻ ነው ያሰብኩት እንጂ በኪሴ የያዝኩት 25 ብር አካባቢ ነበር። ድሬዳዋ ስደርስ ሆቴል ይዞልኝ። ለገሃር ባቡር ጣቢያ ጠበቀኝ። በጠዋት ሉቻኖ፣ አስራትና ካሳሁን ከባቡር ጣቢያ ተቀበሉኝ። ድሬዳዋ ውስጥ ኦጋዴን ሆቴል የሚባል ነበር። እዚያ አሳረፉኝ። ሆቴል ሳርፍ የመጀመሪያ ጊዜዬ ነበር። ከቤትም ወጥቼ ርቄ አላውቅም። በማግስቱ ወደ ልምምድ እንድመጣ አዘዘኝ። ከዚያም ልምምድ ላይ አየኝ። የኮተን ወጣቱ ቡድን ለፍጻሜ ጨዋታ ደርሶ ነበር። ሉቻኖ እኔን ለወጣት ቡድኑ አስመዘገበኝና በጨዋታው አሰለፈኝ። እርሱ ሊያየኝ ፈልጓል። እኔም የዋንጫው ጨዋታ ላይ ተሰለፍኩ። ቀደም ሲል ብዙ ጊዜ ሻምፒዮን የሚሆነው ሲሜንታሪያ (ሲሚንቶ) ነበር። አጋጣሚ ሆኖ እኔ በተጫወትኩበት ጨዋታ 3-1 አሸነፍንና ዋንጫውን ወሰድን። እኔም ጥሩ ተጫወትኩ። በፊት መሃል ላይ ነበር የምጫወተው። ሉቻኖ በልምምድ ላይ ካየኝ በኋላ የኋላ መስመር ተጫዋች አደረገኝ። ” እዚህ ቦታ ብትጫወት ይሻልሃል።” ብሎ ተከላካይ አደረገኝ። ያን ጊዜ የአሰልጣኝህን ትዕዛዝ እጅጉን ታከብራለህ። መጫወቱን እንጂ የትም ቦታ ቢያጫውትህ ትቀበላለህ። ጨዋታውን ጨርሰን ስንወጣ አቀፈኝ፤ አበረታታኝ። ” ከዚህ በኋላ በዋናው ቡድን ውስጥ ነው ልምምድ የምትሰራው።” አለኝ።

ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ ሄዶ ለኮተን ለመጫወት ያነሳሳህ የቡድኑ አሰልጣኝ ሉቻኖ መሆኑ ነበር?

አዎ! ሉቻኖ ስለነበር ነው። ሌላ አሰልጣኝ ቢሆን አልሄድም ነበር። ከልጅነቴ ጀምሬ ሉቻኖ ሲጫወት ስለማየውና ስለማደንቀው ልዩ ፍቅር ነበረኝ። ልጆች ሆነን እንኳ ሰፈር ውስጥ ስንጫወት ” እኔ ሉቻኖ ነኝ፤ እኔ አዋድ ነኝ፤ እኔ ይህደጎ ነኝ፤ እኔ እገሌ….።” እያልን ነው የምንጫወተው። ለኢትዮጵያ ሻምፒዮና ሲመጡ እኔ የጥጥ ማህበር ደጋፊ ነበርኩ። በዚያ ላይ ሉቻኖ በጣም ጎበዝ ተጫዋች ነበር። የሚያገባቸው ጎሎች፣ የሚያቀብላቸው ኳሶች የሚያስገርሙ ነበሩ። ለሉቻኖ ከፍተኛ አድናቆት ስለነበረኝ፣ ከሰፈራችን የወሰዳቸው ጓደኞቼም (እነ አስራትና ካሳሁን) ስለ እርሱ በጣም ጥሩ ነገር ስለሚነግሩኝ መሄድ አለብኝ ብዬ ወሰንኩ። ድሮ አዲስ አበባ ትልልቅ ክለቦች ውስጥ ቶሎ ቦታ አታገኝም። በጣም ጎበዝ ጎበዝ ተጫዋቾች ነበሩ። ሉቻኖ ሲጠራኝ ምንም አላንገራገርኩም። እኔ ሉቻኖን ሳገኝ ገና ወጣት ነኝ። እርሱ ነው ያሳደገኝ። ቤታችንን ያያል፤ ይቆጣጠረናል፤ ይከታተለናል፤ ያበረታታናል። አባት ነበር ሉቻኖ። የምንኖርበትን ሰፈር ይቃኛል። አንዳንዴ ምግብ በደንብ እንድንመገብ ከራሱ ገንዘብ አውጥቶ ይጋብዘናል። ክለቡን አስገድዶም ኦሜድላ ሆቴል የአንድ ወር ምግብ እንዲከፈልልን ያደርጋል። ኦሜድላ ከዚራ ውስጥ የሚገኝ የጣልያኖች ምግብ ቤት ነበር። ምርጥ-ምርጥ ምግቦች ነበር የሚያቀርቡት። ጥራት ያላቸው ገንቢ ምግቦች የምናገኘው እዚያ ነበር።

የሉቻኖ የአሰልጣኝነት ሥራው ምን ይመስል ነበር?

ሉቻኖ የሚሰጣቸው ልምምዶች በጣም ጠንካሮች ነበሩ። ልምምዶቹን መቋቋም፣ እርሱ የሚልህን ነገር ማዳመጥና መስራት ይኖርብሃል። ልምምዱን በተግባር ሲያሳይ ሲሪየስ ሆነህ እንድትከታተለው ይፈልጋል። እርሱ የሚሰራቸው ልምምዶች የሚገርሙ ነበሩ። ሉቻኖ በትዕዛዝ ብቻ አልነበረም የሚያሰራው። እራሱ ሰርቶ ነው የሚያሰራው። እርሱ ካሰራን ሥራ በተጨማሪ እኔ ቤቴ እሰራለሁ። በዚህ ምክንያት ዋናውን ቡድን ስቀላቀል እንደ ነባር ተጫዋች ሆንኩ። በኮተን የኋላ ተከላካይ የነበረው ጌታቸው ገ/ማርያም ነበር። ከዚያ እኔ ተተካሁ። እኔን ሉቻኖ ባያገኘኝ ፣ እርሱ ባያሰለጥነኝና ባያሰራኝ ኖሮ እዚህ ደረጃ አልደርስም ነበር። እኔ ባህሪዬ አስቸጋሪ ነበር። አዲስ አበባም እያለሁ አስቸጋሪ ነበርኩ። እንደ ሉቻኖ ባይሆን ኖሮ እዚህ ደረጃ ላይ እደርሳለሁ ብዬ አላስብም ነበር። እርሱ የሚያይህ እንደ ልጁ ነው። የሚቆጣጠርህም እንደ አስተማሪ ነው። በስንት ሰዓት ወጥተህ በስንት ሰዓት እንደምትገባ በየአካባቢህ እየመጣ ቼክ ያደርጋል። ከተማ ውስጥ ትልልቅ መዝናኛ ቤቶች ነበሩ። የእኛ ተጫዋቾች ስለምንታወቅ ” ማን ገባ? ማን ወጣ? ማን አመሸ?” መረጃ የሚነግሩት ሰዎች ይኖሩታል። ለምሳሌ – አምሽተህ ገብተህ በማግስቱ ልምምድ ላይ ሲያገኝህ ” አንተ ማታ እነዚህኞቹ መዝናኛ ቤቶች ነበርክ። ጠጥተሃል። እንደዚህ ሆነህ ልምምድ አትሰራም። ስለዚህ ሂድና ዶ/ር አብዱራህማን ጋ ታይ ብሎ ይልክሃል። ዶ/ር አብዱራህማን ጋ ሄደህ ዶ/ሩ ” ብቁ ነው፤ ደህና ነው።” ካላለ በስተቀር ልምምድ አትሰራም። ቁጥጥሩ ጥብቅ ስለነበር አንዳችንም ጋር የማምሸት ባህርይ አልነበረም። ድሬዳዋ አነስ ያለች ከተማ ስለሆነች የትም ብትሄድ በቀላሉ መረጃ ይደርሰዋል። በቃ ከስራ ስንወጣ ቀጥታ ወደ ቤት ነው የምንሄደው።

አንተ ሉቻኖን ያገኘኸው የእርሱ የተጫዋችነት ዘመን ካበቃ በኋላ ነው? ወይስ አብረኸው የመጫወት ዕድሉ ነበረህ?

እኔ ኮተን ስገባ ሉቻኖ የተጫዋች – አሰልጣኝ ነበር። እየተጫወተም ፥ እያሰለጠነም ነበር ያገኘሁት። የተጫዋች አሰልጣኝ ሲሆን በጣልያን አገር ለስድስት ወራት የቆየ የአሰልጣኝነት ኮርስ ወስዷል። በጣም ጎበዝ አሰልጣኝ ነበር። የአሰልጣኝነት ትምህርቱን ሲከታተል በትልቅ ደረጃ የተመረቀ፣ ለሰልጣኞች ምሳሌ ሆኖ የቀረበ አሰልጣኝ ነበር። ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ለተጫዋቾች ሲያሳይ ነበር። በጨዋታ ላይ ትንሽ ደከም ስንል ይገባል፤ ቡድኑን አስተካክሎ ይወጣል። ወይ ደግሞ የመጀመሪያ ተሰላፊ ይሆንና ቡድኑን አስተካክሎ ይወጣል። በዚህ መልኩ እየተጫወተም ፤ እያሰለጠነም ነበር ያገኘሁት። ቀስ በቀስ መጫወቱን አቁሞ ወደ ስልጠናው አተኮረ። ሁለት ዓመታት ያህል አብሬው ተጫውቻለሁ። እኔ በዳርማር ብዙ ቦታዎች ላይ ተጫውቻለሁ። እኔ መደበኛ ተከላካይ ተጫዋች እንድሆን የወሰነው ሉቻኖ ነው። ያለህን ብቃት ካየ በኋላ የት ቦታ መጫወት እንዳለብህ ያውቃል። ሉቻኖ ያንተን ችሎታ አይቶ የሚመጥንህን ሚና የመስጠት ትልቅ ብቃት አለው። ጨዋታ የማንበብ ብቃቱ አስገራሚ ነው። በዚያ ላይ ፊትለፊት ተናጋሪ ነው። ደካማ ከሆንክ ” አንተ ቀሽም ተጫዋች ነህ።” ይልሃል። አሪፍ ከሆንክ ደግሞ ” ጎበዝ ነህ። ግን ጎበዝ ነህ ስላልኩህ እንዳትኮራ!” ይልሃል። ሲያበረታታህም አስጠንቅቆህ ነው። ትዕዛዙን ተቀብለህ በአግባቡ የምትሰራ ከሆነ እስከመጨረሻ ይታገልልሃል። እርሱ ከሚፈልገው መስመር ወጣ ካልክ ግን ያበቃልሃል። እርሱ ጋ በዲሲፕሊን ጉዳይ ቀልድ የለም። ” እኔ ጎበዝ ተጫዋች ነኝ። ሰው ይወደኛል።” ብሎ ማለት እርሱ ጋ አይሰራም። በቃ ሉቻኖ የሚያምነው በስራ ነው። በወቅታዊ ብቃት በጣም ያምናል።

በድሬዳዋ የኮተን ተፎካካሪ ቡድን ሲመንት ብቻ ነበር?

በዋናነት ሲመንተሪያ (ሲመንቶ) ነበር። በተለይ ከአስመራ ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾች ያመጡ ነበር። በዚያን ጊዜ ከአስመራ የሚመጡ ልጆች ድሬዳዋ ይመቻቸው ነበር። ኮተን ውስጥ ነበሩ። አብዛኞቹ ግን ሲመንተሪያ (ሲመንቶ) ነበሩ። ኋላ ላይ በተፎካካሪነት ባቡር መጣ።

የሉቻኖና የጥጥ ማህበር መጨረሻ በምን ተቋጨ?

ሉቻኖ ጥጥ ማህበርን ለቀቀ። ያው ከኮሚቴ ሰዎች ጋር አለመስማማት ውስጥ ገብቶ ነበር። እርሱ ቡድኑን ለቆ ከወጣ በኋላ የመጡት አሰልጣኞች የእርሱን ያህል ሊሆኑ አልቻሉም። እኔም መቆየቱ ብዙ አልተመቸኝም። ሉቻኖ አዲስ አበባ መጥቶ ቅዱስ ጊዮርጊስን ያዘ። እኔ ስመጣም ቅዱስ ጊዮርጊስ ነበር። ነገር ግን እኔ ልገባ ስል እርሱ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቀቀ። በጊዮርጊስም ሉቻኖ ተጫዋችም-አሰልጣኝም ሆኖ ነበር። እኔ ግን በቅዱስ ጊዮርጊስ አላገኘሁትም። እኔ ስደርስ እርሱ ወጣ። ሆኖም ሉቻኖ እኔ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንድገባ አበረታቶኛል።

አሰልጣኙ ሉቻኖ ምን አይነት ስብዕና ነበረው?

ድሬዳዋ ህዝቡ ሰላማዊ ነው። ውድድሮች ያለአንዳች ረብሻ ይጠናቀቃሉ። ሉቻኖ በጣም ይፈራል፤ ይከበራል። ከተናደደ በጣም ኃይለኛ ተደባዳቢና ጉልበተኛ ነበር። አንዴ በቴስታ ከመታህ መሬት ወድቀህ መነሳት የለም። ሁሉም ቡድኖች ሉቻኖን ይፈሩታል። እርሱ ሲናደድ ሁሉም ነው ገለል የሚለው። ሉቻኖ ራሱን ያስከበረ በመሆኑ እኛንም የተከበርን አድርጎን ነበር። አንድ ጊዜ ሁለቱ ጠንካራ ተፎካካሪዎች ሲሚንቶና ጥጥ ማህበር ሲጫወቱ መጠነኛ ረብሻ ተነሳ። አሁን ስሙን የዘነጋሁት የሲሚንቶ በረኛ ሜዳ ላይ ተጫዋች ተማቶ እየሮጠ ወደ መልበሻ ቤት ይገባል። ሉቻኖ ተከትሎት ገብቶ በረኛው የነበረበትን ክፍል በር በቴስታ ሰብሮ ገባ። ጥንካሬው ያን ያህል ነው። በረኛውን ይዞ ሲመታው አንድም ሰው ሊገላግል አልደፈረም። የሲመንት ተጫዋቾች እንኳ ቆመው ነው ያዩት እንጂ ረብሻ ሊፈጥር የሞከረ የለም። ፖሊሶች እንኳ በጸባይ ነው የያዙት። እኛም ” በቃ ሉቾ ተው። እባክህ!” ብለን ለምነነው ይዘነው ወጣን። መኪናውን አስነስቶ ወደ ቤቱ ሄደ። በዚያ ላይ ሉቻኖ መካኒክ ነበር። በእጁ ከያዘህ ከእጁ ውስጥ አትወጣም። ሰውነቱ ትልቅ ነው። ጠንካራ ነው። ኑሮው ከስፖርት ጋር የተያያዘ ነው። ሥራው ከብረት ጋር መታገል ስለነበር በጣም ጠንካራ አድርጎታል። ስለዚህ ሁሉም ይፈሩታል።

ኃይለኝነቱ ተላልፎብሃል ጋሽ አስራት?

አዎ! በእርግጥ ልጅ ሆነን ፤ ሰፈርም እያለን እኔ አስቸጋሪ ነበርኩ። አባቴ ኃይለኛ ነበር። አልቅሼ ካገኘኝ ይመታኛል። ስለዚህ አባቴ ተመትቼ ወይም አልቅሼ እንዳያየኝ እያልኩ ከመቱኝ መልሼ መምታት የሚለው ነገር አእምሮዬ ውስጥ አደገ። በዚያው ሰፈር ውስጥ ረብሸኛና ተደባዳቢ ሆንኩ። ጥጥ ማህበር ከሄድኩ በኋላ ደግሞ ሉቻኖ አንበሳ ያደርግሃል። ፈሪ የነበርክ ብትሆን እንኳ ሉቻኖ ደፋር ያደርግሃል። የሚሰጥህ ሞራል ምንም እንድታደርግ ያነሳሳሃል። ከፍተኛ የማነሳሳት አቅም አለው።

 

ብሔራዊ ቡድን የመረጠህ ሉቻኖ ነው?

እኔ ስመረጥ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት አቶ አዳሙ አለሙ ነበሩ። ድሮ ለብሔራዊ ቡድን መመረጥ ከባድ ነበር። ያኔ ኤርትራ፣ ሸዋና ሐረርጌ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ወኪል አላቸው። አቶ ይድነቃቸው ተሰማ – አዲስ አበባ።፣ አቶ ጸሃይ ባህረ – ኤርትራ፣ አቶ አዳሙ አለሙ – ድሬዳዋ አሉ። በብሔራዊ ቡድን ለመጫወት ለሶስቱም መራጭ አካላት ጥሩ ሆነህ መገኘት አለብህ። ኤርትራ ሄደን ከእምባይሶራ፣ ሐማሴን፣ ቴሌ፣ ….፣ አዲስ አበባ መጥተን ከቅዱስ ጊዮርጊስ፣ መብራት ኃይል፣ አየር መንገድ፣ …. ቡድኖች ጋር በምናደርጋቸው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና ጨዋታዎች በምናሳየው ብቃት ነው ምርጫ ውስጥ የምንገባው። በዚህ ሒደት ሶስቱ ትልልቅ የእግርኳስ ሰዎች ከመረጡህ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች ትሆናለህ። አንደኛው ካልፈለገህ አትመረጥም። ያኔ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አዳሙ አለሙ ነበር። በአዳሙ ጊዜ ተመረጥኩ። ከዚያ ሉቻኖ ቡድኑን ከአዳሙ ሲረከብም የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች እንደሆንኩ ቀጠልኩ። ሉቻኖ ሁሌም ተጫዋቾችን የማሳደግ ዓላማ ነበረው። ጊዜው ፕሮፌሽናሊዝምን ቢፈቅድ ኖሮ ሉቻኖ ተጫዋቾችን እዚያም ደረጃ ለማድረስ ይተጋ ነበር። እኔ እንኳ ጥጥ ማህበር፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሐረርጌ ምርጥ፣ ሸዋ ምርጥ፣ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች እንድሆን ያስቻለኝ ሉቻኖ ነው። ‘ ኳስ ሳቆም የሉቻኖን ፈለግ መከተል አለብኝ። እንደ እርሱ መሆን አለብኝ።’ የሚል ዓላማ የያዝኩት በሉቻኖ ትልቅ ስብዕና ሳቢያ ነው። አልፎ አልፎ ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ እያገኘኝ ወደ ስልጠና ዓለም ከገባሁ በኋላም ” በአሰልጣኝነት የምትተካኝ አንተ ነህ።” እያለ ያበረታታኝ ነበር። ” በርታ፤ ቀጥልበት!” በማለት ሀሳብና ምክር ይሰጠኝ ነበር።

አንተና ካሳሁን ተካ በጥጥ ማህበር፣ ስዪም አባተና በቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ገዛኸኝ ማንያዘዋል በብሔራዊ ቡድን በሉቻኖ ሥር ሰልጥናችሁ ትልልቅ አሰልጣኞች ሆናችኋል። ሌሎችም አሉ። ትልቅ የአሰልጣኝነት ደረጃ ላይ እንድትደርሱ በሉቻኖ መሰልጠንና መመራት የሰጣችሁ የተለየ ነገር ምንድን ነው?

እንዴ ሉቻኖ እኮ ትልቅ ትምህርት ቤት ነው። በእርሱ ስር ከሰለጠንክ ትልቅ ቦታ ትደርሳለህ። እርሱ የሚልህን ከተከተልክ፣ የሚያዝህን ካደረክ በተጫዋችነት ትልቅ ቦታ ትደርሳለህ። አሰልጣኝ ስትሆንም ጥሩ ስብዕና፣ ጠንካራ የስራ አቅም ይኖርሃል። ሉቻኖ ብዙ አዳዲስ ነገሮችን ያስተምራል። በተግባር ያሳያል። ለምሳሌ – ኳሱን እግሩ ሥር ይዞ ፥ አይኑ ሌላ አቅጣጫ ላይ ሆኖ ኳሷን ደግሞ ወደ ሌላ አቅጣጫ ማቀበል ያሳየን ነበር። በተግባር። አሁን “ባላየ ማቀበል” መሠለኝ የሚባለው። ራሱ የሚፈጥራቸው የልምምድ መርኃ ግብሮች ሁሉ ነበሩ። የጊዜውን አዳዲስ ነገሮች እያመጣ ያሰራል። ጋሽ ይድነቃቸውም በጣም ትልቅ አክብሮትና አድናቆት የሚሰጠው ለሉቻኖ ነበር። ” ኳስ መጫወት እንደ ሉቻኖ ነው።” ይል ነበር ጋሽ ይድነቃቸው። ምሳሌ የሚያደርገውም ሉቻኖን ነበር። ለኳስ የተፈጠረ ሰው ነበር ማለት ይቻላል።

በ1960ዎቹ መጨረሻ የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች በጀርመናዊው አሰልጣኝ ፒተር ሽንግተር ትዕዛዝ እንዲወስዱ ስለሚደረገው እንክብል (Amphetamine Captagon) ካጋለጠ በኋላ ብዙ ችግሮች ደርሰውበታል። ስለዚህ ጉዳይ አጫውተን።

መድሃኒቱን ከሚወስዱት የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች አንዱ ነበር። ከልምምድ መልስ ወደ ጨዋታ ልንገባ ስንል አሰልጣኙ ይሰጠናል። ” ቫይታሚን ነው። ጉልበት የሚሰጥ ነገር ነው።” እያለ ነበር የሚሰጠን። ካልሺየም ሳንዶዝ – ቫይታሚን ሲ በሚባል በውሃ የሚበጠበጥ ጭማቂ መሳይ መጠጥ ውስጥ እንክብሎቹን ይከታል። ትዝ ይለኛል ፥ ሁለት ክኒኖች ነበር የሚከተው። ይሰጠናል፤ እንጠጣለን። ምንም አንደክምም። ጀርመናዊው አሰልጣኝ እየደበቀ ነበር የሚሰጠን። ሉቻኖ በምክትል አሰልጣኝነት አብሮን ስለነበር የእንክብሏን ማስቀመጫ ፓኬት ያያል። እርሱ ብዙ ስለሚያነብ መድሃኒቱ ከፍተኛ ጉዳት እንዳለው ገባው። በተለይ ተጫዋቾች ጨዋታ ካቆሙ በኋላ ጉዳቱ ስለሚበዛ ” ለምን ትሰጣቸዋለህ?” ብሎ ከፒተር ጋር ጸብ ይጀምራል። ጀርመናዊው አሰልጣኝ በእርዳታ መልክ የመጣ ስለሆነ በፌዴሬሽኑ ሰዎች ድጋፍ ነበረው። ፒተር ድርጊቱ የተሳሳተ እንደሆነ ስለሚያውቅ፣ ክኒኑ የተከለከለ ስለነበርና ገሃድ መውጣቱ ችግር እንደሚያስከትል ስለገባው ሉቻኖን ” አላሰራ አለኝ።” በሚል ቀድሞ ይከሰው ጀመር። ሉቻኖ ደግሞ ” ተጫዋቾቹ ኢትዮጵያውያን ልጆቼ ናቸው። የአገሬ ልጆች መሞት የለባቸውም። የተከለከለ ነገር የሚወስዱበት ምክንያት የለም።” የሚል መልስ ሰጠ። ክርክሩ ጦዘ። ጸቡም ከረረ። ኋላ ላይ “ምርመራ ይካሄድ!” የሚል ሐሳብ መጣ። ማን ማን እንደሚወስድ ይታወቅ ስለነበር ሐኪሞቹ ለተጫዋቾቹ ቃለ መጠይቅ አደረጉ። ውጤቱ ግን
” አገሪቱን ሊያስቀጣ ነው።” በሚል ሰበብ ሉቻኖን ማገድ ሆነ። ያ ሁሉ የደረሰበት ያንን ስላወጣና ስላጋለጠ ነው። በጊዜው እኛ ስለመዳኒቱ ምንም አናውቅም ነበር። በኋላ ነው ነገሩ የገባን። እኛ ሉቻኖን በጣም ስለምናከብረውና ስለምንወደው ” ምንድነው ችግሩ?” ብለን ስንጠይቀው ነው ያስረዳን። ስለ ሁኔታው ስንሰማ ደነገጥን። ከዚያ በኋላ ” የሉቻኖ ልጆች” እየተባለ መጥፎ አመለካከት የመጣበትም ጊዜ ነበር።

ሉቻኖ ከዚያ ምን ሆነ?

በኋላማ ከብሔራዊ ቡድኑ ተገለለ። ከዚያ ጥይት ፋብራካ ሴፌሪያን አካባቢ ትልቅ ጋራዥ ነበረ። ሉቻኖ በጣም ጎበዝ መካኒክ ነበር። ሌሎች መካኒኮች መኪና ውስጥ ገብተው፣ አስነስተው፣ ምናምን ነው አይደል የሚያዳምጡት እርሱ ግን መኪናው ምኑ እንደተበላሸ፣ ምኑ ጋ ችግር እንዳለ በድምጽ ነው ለይቶ የሚናገረው። ከብሔራዊ ቡድኑ ከተገለለ በኋላ እዚያ ጋራዥ ይሰራ ጀመር። ዘመናዊ Audi ነበረችው። ኢትዮጵያ የገባችው የመጀመሪያዋ Audi የሉቻኖ ነበረች። አዲሷን ብራንድ መኪና ይይዝ ነበር። ሌሎችም ጥሩ ጥሩ መኪኖች ነበሩት። ሉቻኖ ከሴፌሪያን ካምፓኒ ጋር በሽርክና ይሰራ ነበር። ጊዜው ከባድ ስለነበር ጫና መጣበት። የዘመኑ ሰዎች ንብረቱንም ሊወርሱበት ፈለጉ። “መኪናህን ካልሰጠኸን!” በሚል ወጥረው ያዙት። በዚህ ሰዓት ሞራሉና ስሜቱ እየተነካ መጣ። በመጨረሻ ” መኪናህን አምጣ፤ ለጋራዥህም አለአግባብ ትልቅ ቦታ ይዘሃል። ስለዚህ ይወረሳል።” እያሉ ያስቸግሩት ያዙ፤ ያስፈራሩትም ጀመር። በወቅቱ ደግሞ አሰብ የሚካሄድ ” የእናት አገር ጥሪ ” የተሰኘ ጨዋታ ነበር። ለጨዋታው ጥሪ የተደረገው ለቅዱስ ጊዮርጊስና መብራት ኃይል ሆነ። ሉቻኖ በስድስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ ስለተመሰጠ እርሱም በጨዋታው ላይ እንዲገኝ ተጋበዘ። ኮከብ በተሰኘበት የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የለበሰው መለያ ለጨረታ እንዲቀርብ ስለሚፈለግ ” መለያውን ይዘህ ና!” ተብሎ ታዘዘ። ያን ጊዜ የይለፍ ወረቀት ካልያዙ መንገድ መሄድ አስቸጋሪ ነበር። ጥበቃው ከባድ ስለነበር ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መዘዋወር ያዳግታል። በዚህ ምክንያት ሉቻኖ የይለፍ ደብዳቤውን አጻፈ። ነገ ሊሄድ እንደዛሬ ማታውኑ ተገናኘን።

” ከእኛ ጋር በመኪና ትሄዳለህ ወይ?” ሲል ጠየቀኝ። ” አይ ሉቾ መንገዱ ሩቅ ስለሆነ እኔ በአውሮፕላን ነው የምሄደው።” ብዬ መለስኩለት። ” ኧረ ባክህ ተው ከእኛ ጋር ሂድ።” አለኝ። እኔ ፍጹም ይጠፋል ብዬ አላሰብኩም። እስከ ማታ 12፡00 ድረስ አብረን ቆየን። ከዚያ ወደየቤታችን ሄድን። እኛ በጠዋት በወታደሮች አንቶኖቭ አውሮፕላን ሄድን። እርሱ በጥሩ አውዲ መኪናው ተነሳ። እኛ ቶሎ ደረስን። ሉቻኖን መጠበቅ ያዝን። እርሱ ግን አይመጣም። ” መንገድ ላይ ይሆናል። ለዛ ነው ያልገባው። …..” እያልን እንጠብቃለን። በቀጣዮቹ ቀናትም አልመጣም። አሁን ሐሳብ ያዘን። ” ምን ሆኖ ይሆን?” ብለን ጨነቀን። ” አደጋ ደርሶበት ይሆን?” እያልን እንጠያይቃለን። ኋላ ላይ አዘጋጆቹ ” እኛም ምንም ልናውቅ አልቻልንም። አድራሻውንም አላገኘንም።” ብለው መልስ ሰጡን። እኛም ጨዋታውን ተጫወትን። በማግስቱ ወደ አዲስ አበባ ተመለስን። ከዚያ እኔ በቀጥታ የእርሱ ወደ ነበረውና ሜክሲኮ ወደ ሚገኘው ቤንዚን ማደያ ሄድኩ። ” አሰብ እሄዳለሁ ብሎ’ኮ ወደ አሰብ ነው የሄደው።” አሉኝ። በቃ ይሄ ሰውዬ ጠፍቷል ማለት ነው ብዬ ጠረጠርኩ። ከጊዜያት በኋላ መጥፋቱ እርግጥ ሆነ። ይህን ሁሉ እንግዲህ ከስንት ዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ሲነግረኝ የተረዳሁት ነው። እንዳጫወተኝ መጀመሪያ የሄደው ወደ አሰብ ነበር። ዱብቲ ሲደርስ እዚያ መኪናውን አቁሞ በቀጥታ በእግሩ ጅቡቲ ገባ። ጅቡቲ ጠረፍ ላይ ፖሊሶች ያዙት። ድሮ አብሮት ኮተን የተጫወተ ደራጎን የተባለ የፖሊስ አዛዥ እንደሚጸልግ ነገራቸው። አዛዡ በፍጥነት መጥቶ ሉቻኖን አገኘው። የጥንት ጓደኛውን ይዞ ወደ መሃል ከተማ ይገባል። ይኸው አዛዥ በቀጥታ ሆቴል ያሳርፈዋል። ጅቡቲ ጥቂት ቀናት ተቀመጠ። ከዚያ ግብጽ ሄደ። ከዚያ በቀጥታ ጣልያን ገባ። መገናኘት የጀመርነው እርሱ ጣልያን ገብቶ መኖር ከጀመረ በኋላ በስልክ ሆነ።

ከዚያ በኋላ በአካል አገኘኸው? መቼ?

አዎ! ከመንግስት ለውጥ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጣ። ደወለልኝ። ያረፈው ኡራኤል ወረድ ብሎና ድልድዩን ተሻግሮ አሁን ሥሙን የዘነጋሁት የቆየ ሆቴል ነበር። እዚያ አስጠራኝ። ሄጄ አገኘሁት። አወራን። አሰልጣኝ ሆኝ እየሰራሁ እንደሆነ ነገርኩት። በጣም ደስ አለው። እንደነገረኝ የኢትዮጵያን ስፖርት ይከታተል ነበር። እኔ ስለ ሰራሁት ሥራና ስላስመዘገብኩት ውጤት ይሰማ ስለነበርም በደንብ አበረታታኝ። ያለሁበትን ደረጃ ነገርኩት። በዚሁ መቀጠል አለብህ ብሎ አበረታታኝ። ” ባህሪህ እንዳይቀየር! በዚሁ ቀጥል!” ብሎ መከረኝ። ከዚያ በኋላ የተወረሱ ንብረቶቹን ለማስመለስ ጥረት ማድረግ ጀመረ። ወንድሙ ኢታሎ እዚሁ አዲስ አበባ ይኖር ነበር። ይሁን እንጂ ውክልና ለእኔ ሰጠኝ። ዶክመንቶቹ እስካሁን ድረስ ቤቴ አሉ። እኔም ብዙ ጣርኩ። ካርታውንና ሌሎች ብዙ ሰነዶችን ማግኘት ሳይችል ነበር ከአገር የወጣው። እኔ በብዙ ጥረት የተወሰኑትን አገኘሁ። የምችለውን ያህል ባደርግም ንብረቶቹን ለማስመለስ ብዙ ተንከራተትኩ። ግን አልተሳካም። እኔ ያገኘኋቸውን ሰነዶች ኮፒ አድርጌ አስቀረሁና ለሉቻኖ አስረከብኩ። እርሱም በተገኙት ሰነዶች ብዙ መከራከር ጀመረ። ይሁን እንጂ ቦታው ቁልፍ ቦታ ስለነበር፣ የነበሩት ትላልቅ ማሽኖች ከጣልያን አገር ያስመጣቸውና በቀላሉ የሚገኙ ስላልነበሩ ሊመልሱለት አልፈለጉም። ሁለታችንም ብዙ ለፋን፤ ሉቻኖም ብዙ ተሟገተ። ነገር ግን ሊሆንለት አልቻለም። በቀጠሮ ወደዚያ-ወደዚህ ሲያንከራትቱት መጨረሻ ላይ ሰለቸው። በቃ ተወው። ሁኔታዎች ተስፋ የሚያስቆርጡ ሆኑበት ተወላቸው። በዚህ የተነሳ ብስጭት አደረበት። ጣልያን እንደሄደ ባለቤቱ አረፈች፤ ልጁም አረፈበት። በዚያ ላይ በጣም ሃብታም የነበረ ሰው በአንዴ ንብረቱን ሁሉ አጥቶ ባዶ ቀረ። እነዚህን የመሳሰሉ ፈተናዎች በህይወቱ ገጥመውታል ሉቻኖ። አንድ ቀን እኔ ጋር ያሉ ሰነዶቹን ለልጁ እሰጣታለሁ። ሴት ልጁ አለች። እርሷ ነበረች ስትንከባከበው የቆየችው።

ከቤተሰቦቹ ጋር ያለህ ግንኙነት እንደቀጠለ ነው ?

አዎ! ከልጆቹ ጋር አስተዋውቆኛል። እዚህ የነበረ ጊዜም ቤቱ ይወስደኝ ነበር።

በመጨረሻ ያገኘኸው መቼ ነበር ?

በስልክ በደንብ እንገናኝ ነበር። ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኘነው ከአራት ዓመት በፊት ነበር። ከአራት ዓመት ወዲህ መዘንጋት ጀመረ። ስደውል እንኳ “ማን ነህ?” ነበር የሚለኝ። ‘ አስራት ነኝ።’ ስለው ይረሳል። በስንት መከራ ነበር አስታውሶ የሚያወራኝ። ልጁ ስ ሁኔታው ታስረዳኛለች። ወደ መጨረሻ አካባቢ ደግሞ ማነጋገርም አልቻለም። ቤተሰቦቹ ፎቶግራፉን ይልኩልኛል። ኢታሎንም አገኘው ነበር። አብሮ አደግ ጓደኛዬም ጣልያን ይኖራል። እርሱ የሉቻኖና የእኔን ግንኙነት ስለሚያውቅ እያንዳንዱን ነገር እየተከታተለ መረጃ ያደርሰኛል። ሲደውልልኝም ስለ ሉቻኖ ሁኔታ እጠይቀዋለሁ። ” አዎ አገኘዋለሁ። ቤቱ እየሄድኩ እጠይቀዋለሁ። እኛ የምንነግረውን ብዙም አያስታውስም።” ይለኝ ነበር።

ውለታቸው በቀላሉ ሊመለስ የማይችልና በአግባቡ እንኳ ያላከበርናቸው የእግርኳስ ምልክቶቻችን ቀስ በቀስ እያለፉ ስናጣቸው ምን ይሰማሃል?

የሚሰማኝ በጣም ትልቅ ሃዘን ነው። እኛ የተነሳነው እነርሱን አይተን ነው። መነሻዎቻችን እነርሱ ናቸው። ለኢትዮጵያ እግርኳስ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። እነርሱ ካልተከበሩና ካልተወደሱ የትም መድረስ አይቻልም። ለእነዚህ ሰዎች አንዲት ነገር አለመደረጉና አለመሰራቱ ሁሌም እንድቆጭ ያደርገኛል። በሌላው ዓለም እንደእነዚህ አይነት ታላላቅ ሰዎች ቅርስ ናቸው። ዘላለም የሚታወሱበት ሐውልት ይኖራቸዋል። አቶ ይድነቃቸው ፣ መንግስቱ፣ ሉቻኖ፣ … እነዚህ ሰዎች የኢትዮጵያ ትልቅ ባለውለታ የነበሩ ሰዎች ናቸው። እነርሱ ካልተከበሩ ማን ሊከበር ነው? ሌላው እንኳ ቢቀር አሁን እግርኳሱ ላይ ያሉ ሰዎች እነዚህን ታላላቅ ባለውለቶች በስም ያውቋቸዋል። ስለዚህ አንድ ማስታወሻ ሊቀመጥላቸው ይገባል። እነዚህ እኮ ታሪክ ሰርተው ያለፉ ናቸው። ነገር ግን ሥማቸው እንዲነሳ አይፈለግም። እግርኳሱ አካባቢ ያሉ አመራሮች እነዚህን ታሪከኞች ማስታወስ አይፈልጉም። ምክንያቱም የእነርሱን ያህል አይደለም ጥቂቱን መስራት አይችሉማ! በዚያ ላይ ታሪክ አያነቡም፤ ታሪክ አያውቁም። የታሪከኞቹን ስማቸውን እኝጂ ሥራቸውን አያውቁም። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ የግሩፕ ነገር ነው። የሚያወራልህ ግሩፕ። አሁን ለምሳሌ- ስለ ሉቻኖ ማንም ሰው ማውራት አይፈልግም። ሉቻኖ ትልቅ ሰው ነው። ትልቅ ሥራ ሰርቷል። ግን ማንም አያወራለትም። እኔ በየሄድኩበት ቦታ ሉቻኖ እላለሁ። እርሱ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ሰው ነው። ታሪካዊ ሰው ነው። ስለዚህ ይህን ሰው መዘንጋት የለብኝም። የእኔ መነሻዬና አይከኔ እርሱ ነው። ይህን ታላቅ ሰው ካስታወስኩ ነገ እኔም ልታወስ እችላለሁ ብዬ አስባለሁ። በስፖርቱ አካባቢ ያሉ ሰዎች ስለእነዚህ ታሪክ ሰሪዎች አንድ ነገር ሊያደርጉ ይገባል። በስማቸው አንድ ነገር መደረግ መቻል አለበት። ሉቻኖ ለኢትዮጵያ የነበረው ፍቅር የሚገርም ነው። “ክልስ” ስትለው በጣም ነበር የሚናደደው። ” እኔ ንጹህ ኢትዮጵያዊ ነኝ።” ነው የሚልህ። እንዲህ አይነት የአገር ፍቅር ያለውን፣ ታሪክ የሰራን ባለውለታ ምናለበት ከንጉሱ ዋንጫ ሲቀበል የተነሳውን ፎቶ እንኳ ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ውስጥ በትልቁ ቢቀመጥ? የአፍሪካ እግርኳስ አባት የተባለውን የአቶ ይድነቃቸውን ፎቶ ምናለበት እንዲሁ በማስታወሻነት በትልቁ ተሰርቶ በጽ/ቤቱ ውስጥ ቢቀመጥ? እንደነዚህ አይኘቶቹ ነገሮች አለመደረጋቸው በጣም ይቆጨኛል። ቢያንስ ማውራቱ ጥሩ ነው። አሁን እኔ ሳወራ የሚሰማኝን ተንፍሻለሁ። ስሜቴን ተናግሬያለሁ። ፍላጎቴን ገልጫለሁ። ነገ ይደረግ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

ያጋሩ