ጣና ዋንጫ | ወልቂጤ ከተማ ኮልፌ ተስፋን በአራት ጎል ልዩነት አሸነፈ

በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ የሁለተኛ ቀን ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ በሰዒድ ኪያር የሚመራውን ኮልፌ ተስፋ ቡድን አራት ለምንም አሸንፏል።

በትናንትናው ዕለት ጅማሮውን ያደረገው አንደኛው የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር የምድብ ሁለት የመጀመሪያ ጨዋታን ደግሞ በዛሬው ዕለት አስተናግዷል። በዚህም የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ ክለብ የሆነው ወልቂጤ ከተማ በራሱ የጨዋታ መንገድ እንደመጣ የሚገልፀው ኮልፌ ተስፋን ገጥሟል።

ኳስን ተቆጣጥሮ መጫወት የሚፈልጉ ሁለት ቡድኖች ያደረጉት ይህ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች እምብዛም የግብ ሙከራዎ አልተስተናገዱበትም። ከሁሉም በላይ በሰዒድ ኪያር እና ፈቀደ ትጋ የሚመራው ኮልፌ ተስፋ ቡድን ግብ ጠባቂን እንደተጨማሪ አማራጭ ወደ ፊት ገፍቶ የመጫወት ፍላጎት በብዙዎች ዘንድ አተገባበሩ ሲጠበቅ ነበር። አብዛኞች በተረዱት መጠን የቡድኑ ግብ ጠባቂ ቶማስ ትዕግስቱ በኳስ ቁጥጥር ወቅት ክልሉን ለቆ ባይወጣም ከፍ ብለው የሚጫወቱት ተከላካዮች ጀርባ ያለውን ሰፊ ቦታ ለማጥበብ ወደፊት ተጠግቶ ሲጫወት አስተውለናል። በዚህ የጨዋታ መንገድ ወልቂጤዎች በፍጥነት ከተከላካይ ጀርባ ለመገኘት እየጣሩ ግብ ለማስቆጠር ሞክረዋል።

ጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ አካፋይ ሰዓት ላይ ሲደርስ ወደ ግብ በመድረስ ረገድ የተሻሉት ወልቂጤዎች መሪ ሆነዋል። በዚህም የኋላሸት ሠለሞን ከተከላካይ ጋር ታግሎ ያገኘውን ኳስ በግራ እግሩ ከመረብ ጋር አዋህዶታል። ከኳስ ጋር ዘለግ ያለ ጊዜ ማሳለፍን የመረጡት ኮልፌዎች በ33ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተነሳን ኳስ በሩቁ ቋሚ የነበረው ኤሊያስ መንግስቱ ለአንዋር በድሩ አመቻችቶለት አንዋር የሞከረው ኳስ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታኮ ወጥቷል። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ግን የወልቂጤን ጫና መቋቋም ሳይችሉ በሰሩት ስህተት ግብ አስተናግደዋል። በዚህም ብዙዓየሁ ሰይፈ አብዱ መሐመድን ተጭኖ የተቀበለውን ኳስ በቀጥታ ለኋላሸት አቀብሎት ፈጣኑ አጥቂ በተመሳሳይ በግራ እግሩ ግብ አድርጎት አጋማሹ በወልቂጤ ሁለት ለምንም መሪነት ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽም ጠንከር ብለው የቀረቡት መሪዎቹ ወልቂጤዎች በአቡበከር ሳኒ አማካኝነት ፈጣን ጥቃት ሰንዝረው መሪነታቸውን ለማስፋት ጥረዋል። በተቃራኒው በአሠልጣኝ ሰዒድ ኪያር የሚመሩት ኮልፌዎች እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ኳሱን ባያንሸራሽሩትም ወደ ግብ በመድረድ ረገድ ግን በመጠኑ እድገት አሳይተዋል። ይህ ቢሆንም ግን ገና አጋማሹ በተጀመረ በ6ኛው ደቂቃ ግብ አስተናግደው ጨዋታው ከእጃቸው የወጣባቸው መስሏል። በተጠቀሰው ደቂቃም ለአጥቂ መስመሩ ተጠግቶ ሲጫወት የነበረው ብዙዓየሁ ሰይፈ ከተከላካዮች አፈትልኮ በመውጣት ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ኳሱን በአናቱ በመላክ ግብ አስቆጥሯል።

63ኛው ደቂቃ ላይ በቁጥር በዝተው ያጠቁት የኮልፌ ተጫዋቾች ወልቂጤ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ቢደርሱም አጋጣሚውን መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። ከደቂቃዎች በኋላም ሌላ ጥሩ ኳስ ከወደ ግራ ካደላ ቦታ አግኝተው ሞክረው ዒላማውን ስቶባቸዋል። ወልቂጤዎች በዚህ አጋማሽም በአቡበከር ሳኒ እና ተቀይሮ ወደ ሜዳ በገባው አንዋር ዱላ አማካኝነት ሌላ ሙከራ አድርገው ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቢቀሩም ሙሉ 90 ደቂቃው ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ምንተስኖት ዮሴፍ የማሳረጊያዋን አራተኛ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በወልቂጤ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ማቲያስ ወልደአረጋይ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጦ ሽልማቱን ተረክቧል።

የአሸናፊው ቡድን አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ከጨዋታ በኋላ “ጨዋታው ጥሩ ነው። እኛ በፈለግነው መንገድ ለመሄድ ነው የተንቀሳቀስነው። ይህንን በተቻለ መጠን ለማድረግ ሞክረናል ፤ ግን ይቀረናል። ይህ የመጀመሪያ ጨዋታ ነው። ወደ እዚህ ውድድር ስንመጣ ዕቅዳችን የጨዋታ መንገዳችንን ለማሳደግ ነው። ተከታታይ ጨዋታ ስናደርግ ደግሞ እድገቱ ይመጣል። ይህ ጨዋታ እንደ መጀመሪያ ጨዋታ ጥሩ ነው። በጨዋታው ተጋጣሚያችን ስህተት እየሰራ ነው ያስቆጠርነው። ግን እንዲሳሳቱ ያደረገው የእኛ ጫና ነው። እኛ ከሌለን አይሳሳቱም ነበር። እኛ ተጭነናቸው መጫወቻ ቦታ ስንነፍጋቸው ነው ስህተቶችን ያገኘነው። በአጠቃላይ ተጋጣሚ ፈትኖናል ማለት አልችልም ፤ ግን እንደ ቡድን የነበራቸው ነገር ጥሩ ነው። ሀሳባቸውን ለማከናወን ብዙ ነገር ይፈልጋል። እኛ አዳዲስ ተጫዋቾቻችንን ለማየት ሞክረናል። የቡድኑን ውህደት ለማምጣትን ነው ጨዋታውን የተጠቀምነው።” በማለት ሀሳባቸውን አጋርተውናል።

የኮልፌ ተስፋ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ሰዒድ ኪያር በበኩሉ “ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ ሁለቱም አጋማሾች የተለያዩ ነበሩ። በሜዳ ላይ በመጀመሪያው አጋማሽ የእነሱ ግብጠባቂ እና ተከላካይ ኳስ እንዲጫወቱ ፈቅደን ነበር። የኳስ ቅብብሎች ስህተት እንሠራ ነበር። ያ ደግሞ ግብ እንዲቆጠርብን ምክንያት ሆኗል። በጨዋታ እንቅስቃሴ ብዙ ተጫዋቾች አብረው የተጫወቱ  አይደሉም። አንዳንዱ ከትንሽ ቀን በፊት የመጣ አንዳንዱ አብሮ የቆየ ነው። ስለዚህ በዛ መካከል ክፍተቶች ነበሩ። በጨዋታው በጣም ደስተኞች ነን። የተቆጠሩብን ኳሶች የሚታረሙ ስህተቶች ነው። ተከላካዮቻችን ሲቀባበሉ ስህተት ሲሠሩ በዛ መንገድ ነው። ጨዋታው ጥሩ ነው ፤ ለክለቦች መዘጋጃ እንደሆነው ሁሉ ለኛ ደግሞ ማያ ነው ማለት ነው። በሰመር ካፕ ጨዋታ አበበ ቢቂላ ላይ ተጫውተን ነበር። እዛ ከዚህ የተሻሉ ፈታኝ ቡድኖች ነበሩ ፤ ከዛ አንጻር የራሳችን ስህተት ነው እንጂ በምንፈልገው ደረጃ ብንጫወት ከዚህ የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ እንችል ነበር። በሳምንት ሁለት ቀን ነው ልምምድ የምንሠራው። ስለዚህ በእነዚህ ጊዜያቶች ስህተቶቻችንን እያረምን እንሄዳለን። ከ አሥራ አንዱ ሦስቱ ሁለት ልምምድ ነው የሠሩት ፤ ከቡድኑ ጋር ስድስቱም በክለብ ደረጃ ተጫውተው አያውቁም። እነዚህ ተጫዋቾች ዛሬ በነጻነት ይሄንን መግለጽ ከቻሉ በየቀኑ ልምምድ ቢሠሩ በክለብ ደረጃ ቢያዙ ሁሉም ቢሟላላቸው የተሻለ ነገር ያደርጋሉ። የመጀመሪያውን አላማችንን አሳክተናል ፤ ተጫዋቾች እድል ቢያገኙ መጫወት እንደሚችሉ በኔ በኩል አይቻለሁ። በጨዋታ መንገዳችንም አንድ ሦስተኛውን አልተገበርንም። በብዙ ምክንያቶች እነሱን ስናስተካክል ጥሩ ቡድን ይሆናል። ግብ ጠባቂ ግብ አስቆጣሪ የሚሆንበት ሂደት የዚህ ሂደት የመጨረሻው አካል ነው ፤ መጀመሪያ መግባባት አለባቸው። 90 ደቂቃው ትምህርት ሚሰጥ ነው።” በማለት የድህረ-ጨዋታ አስተያየቱን ሰጥቶናል።