ስለተራዘመው የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ውል መግለጫ ተሰጥቷል

👉”በስምምነቱ ላይ በግዴታነት የተቀመጡ ጉዳዮች አሉ…….” – አቶ ባህሩ ጥላሁን

👉”እኛ የምንከፍለው ከሌሎች ሀገራት አንፃር ዝቅተኛ ነው ነገርግን ሀገራችን ካለችበት ሁኔታ አንፃር ከፍተኛ ነው።” – አቶ ባህሩ ጥላሁን

👉”ውጣ ውረዶች ቢኖሩም ጥሩ ነገር ሰርተናል ብዬ አስባለሁ”- አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

👉”ከሀገር ውጭ ያለውን ነገር ትተን በሀገር ውስጥ አንድ ክለብ ብይዝ የማገኘው ነገርን እዚህ ስላገኘው አይደለም የቆየሁት …..”- አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በቅርቡ ስለታደሰው ውላቸው እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለቻን ውድድር ማለፉን አስመልክቶ ዛሬ ቀትር በጁፒተር ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

በሁለቱ አጀንዳዎች ላይ ያተኩራል ተብሎ የተጠራው ነገር በአሰልጣኙ አዲስ የውል ስምምነት ላይ ያተኮረውን ጋዜጣዊ መግለጫ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እና የፌደሬሽኑ የጽ/ቤት ሃላፊ የሆኑት አቶ ባህሩ ጥላሁን በጋራ የሰጡት ነበር።

በቅድሚያ ከአሰልጣኙ ውል ማራዘም ጋር የነበረውን አስተዳደራዊ ሂደት የፌደሬሽኑ የፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን በተከታዩ መልክ አስረድተዋል።

“የአሰልጣኝ ውበቱ ኮንትራቱ መስከረም 14 2015 ይጠናቀቅ እንደነበር ይታወቃል ነበር ይህን ተከትሎ በርካታ ሀሳቦች ይሰጡ ነበር በተለይም በፌደሬሽኑ በኩል ቀኑ ቢቃረብም እንቅስቃሴዎች የሉም የሚል በሚዲያዎች በኩል ሀሳቦች ይሰነዘሩ ነበር እርግጥ በዘመናዊ እግርኳስ ውሎች የማራዘም ሂደት ከመጠናቀቂያ ጊዜያት አስቀድመው እንደሚደረጉ ይታወቃል ፤ ሐምሌ እና ነሀሴ ላይም በአሰልጣኙ በቀረበ ሀሳብ መሰረት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ለመወያየት ሞክሯል ነገር ግን ወቅቱ የምርጫ ሰሞን ስለነበር እና የተለያዩ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች ስለነበሩብን በተወሰነ መልኩ ተወጥረን ነበር በተመሳሳይ አሰልጣኙም ከማሊዊ ጨዋታ በኃላ ወደ አሜሪካ በማቅናታቸው ቁጭ ብሎ ለመነጋገር የተመቸ ሁኔታ አልነበረም።”

“በዚህም መነሻነት በቻን ማጣርያ ከደቡብ ሱዳኑ ጨዋታ መልስ ለመነጋገር በስራ አስፈፃሚው በኩል አቅጣጫ ተቀምጦ ነበር ነገርግን በምርጫ የመወጠር ነገር ስለነበር የተሞላ የስራ አስፈፃሚ አባላትን በተመሳሳይ ወቅት ማግኘት ስላልተቻለ ጉዳዩ ወደዚህኛው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሊንከባለል ችሏል።”

“አዲሱ ስራ አስፈፃሚም በጉዳዩ ዙርያ ሦስት ጊዜ ውይይቶችን አድርጓል ፤ በመጀመሪያው ውይይት ለውሳኔ መነሻ የሚሆኑ የሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎች እንዲቀርቡ እንዲሁም አሁን ላይ ገበያው ለዋና አሰልጣኝ ስንት ይከፍላል የሚለው እና በቆይታው የነበረው ስኬቱ በዝርዝር እንዲቀርብ አቅጣጫ ተቀመጠ በሁለተኛው ውይይት ደግሞ ሌሎች ሀገሮች ለዋና አሰልጣኛቸው ምን ያክል ይከፍላሉ ፤ የሊጉ አሰልጣኞች ምን ያክል የፊርማ ክፍያ ያገኛሉ የሚለው ቀርቧል ከዚህ አንፃር የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ እንደ ሀገር ቦታው ካለው ክብር ውጭ ምን ማግኘት አለበት የሚለው ጉዳይ ጽ/ቤቱ ፣ ፕሬዘዳንቱ እንዲሁም አሰልጣኙ ባለበት ተነጋግረናል። እንደገና ለሦስተኛ ጊዜ በዌቤናር ውይይት አድርገናል ከጅምሩ በማራዘሙ ጉዳይ ላይ በስራ አስፈፃሚው መካከል ልዮነት አልነበረም ከጥቅማጥቅም እና ከደሞዝ ጋር በተገናኘ ነበር ልዮነቶቹ በዚህም መሰረት መግባባት ላይ በመድረስ ባሳለፍነው አርብ ይፋ አድርገናል። በዚህም የውል መጠኑ ለሁለት ዓመት እንዲሆን ተስማምተናል ማለትም ከመስከረም 15/2015 እስከ መስከረም 14/2017 ይሆናል በቆይታቸውም 250,000 የተጣራ ወርሃዊ ደሞዝ እና ሌሎችም ጥቅማጥቅሞች ተነጋግረን እንዲኖራቸው አድርገናል።”

“በስምምነቱ ላይ በግዴታነት የተቀመጡ ጉዳዮች አሉ ፤ በ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ እንዲሁም ደግሞ ለቻን ያለፈው ብሔራዊ ቡድን የተሻለ ከቀደሙት ሁለቱ ተሳትፎዋችን በተሻለ ውጤት ማስመዝገብ በግዴታነት የተቀመጡ ናቸው። ከዚያ ውጭ አሰልጣኙ ራሳቸውን ለማሳደግ የትምህርት እድል ቢያገኙ ወጪያቸውን ፌደሬሽኑ የሚሸፍን ይሆናል።በቀደሙት ጊዜያት አሰልጣኙ የተለያዩ ጉዞዎችን ሲያደርጉ እንደ ማንኛውም መንገደኛ በኢኮኖሚክ ክላስ ነበር ተሳፍረው ይጓዙ የነበሩት በአሁን የውል ስምምነት መሰረት ግን በቢዝነስ ክላስ የሚጓዙ ይሆናል።”ብለዋል።

በማስከተል ስለአዲሱ የውል ስምምነት ደግሞ አሰልጣኝ ውበቱ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል

“በመጀመሪያ የሁለት ዓመት ውል ፈርሜ ቡድኑን ስረከብ ጥሩ ነገር ለማስመዝገብ ፈተና ይገጥመኛል ብዬ አስቤ ነበር ከፈጣሪ ጋር እና አብረውኝ ካሉት የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ጋር በመሆን እዚህ ደርሰናል። ለተጨማሪ ሁለት ዓመት አብረን እንድንቀጥል በፌደሬሽኑ በኩል ሙሉ ፍቃደኝነት ነበር በእኔ በኩልም ከተለያዩ ክለቦች ጥያቄዎች ቢኖሩም በብሔራዊ ቡድን መቆየት ከሚኖረው ሞራላዊ ጥቅም እንዲሁም ወደፊት ለሚኖረኝ የአሰልጣኝነት ህይወት ከሚኖረው አበርክቶ አንፃር በሀላፊነት ለተጨማሪ ሁለት ዓመት ለመቆየት ተስማምቻለሁ በዚህም እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ።”

“ውጣ ውረዶች ቢኖሩም ጥሩ ነገር ሰርተናል ብዬ አስባለሁ በቀጣይም በሚኖረን ቆይታ አብረውኝ ከሚሰሩ አካላት ጋር በመሆን ብሔራዊ ቡድኑ የጀመረውን ነገር እንዲያስቀጥል እና ከዚህም በተሻለ እንዲጓዝ የበኩሌን አደርጋለሁ።”

በመቀጠልም በስፍራው ከታደሙ የመገናኛ ብዙሃን አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በአሰልጣኙ እና በጽ/ቤት ሀላፊው ምላሽ የተሰጠባቸው ሲሆን አንኳር ሀሳቦቹም ቀጥለው ቀርበዋል።

👉የኮንትራቱ ማብቂያ ጊዜ መስከረም 15/2017 መሆኑ ዳግም ወደ ክለብ እግርኳስ ለመመለስ ፈተና አይሆንብህም ወይ?

“ውል መታደስ ያለበት ቢያንስ ስድስት ወር ሲቀር ነው አሁን ካሳለፍነው ሂደት እኔም ፌደሬሽኑም የሆነ የምንወስደው ትምህርት ይኖራል ብዬ አስባለሁ። በአሁኑ የማራዘም ሂደት ላይ ከፌዴሬሽኑ ቀድሞ ጥያቄው ከእኔ ነው የመጣው ፍላጎት ካላችሁ እንነጋገር ካልሆነ ወደ ሌላ አማራጭ ለመመልከት የነበረው ሂደት በአጠቃላይ የዘገየ ነበር ይህ የሆነው ሰኔ አካባቢ ነው ይህ ደግሞ ዝውውሮች የሚጠናቀቁበት ወቅት ነው በአሁኑ ውል መስከረም 2017 ላይ ይጠናቀቅ እንጂ እስከዚያ ድረስ አልቆይም።ከዚያ በፊት ወይ ከፌደሬሽኑ ጋር መቀጠል አለብኝ አለበለዚያ ከሁለት(ሦስት) ወር በፊት ቀጣዩን ማረፊያዮን ማወቅ አለብኝ ስለዚህ ብዙ ችግር አይፈጥርም።”

👉በኮንትራቱ ከተቀመጡት ግዴታዎች አንዱ በቻን የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ነው ፤ አነስተኛ ውጤት ከመጣ ይሰናበታሉ ወይ? ስለአሰልጣኝ ቡድኑ ውልስ?

“ውሉ ላይ በግዴታነት የተቀመጡት ነገሮች ለማሳካት ነው የተቀመጡት ያ ካልሆነ ግን ወደ ሚቀጥለው ነገር እናመራለን ነገርግን አፍሪካ ዋንጫ ካላሳለፍክ ትባረራለህ የሚል ውል የለኝም።እንደ ግዴታ ተቀመጡ እንጂ በሁኔታዎች ላይ ተመስርተን ወደ ቀጣዩ ነገር የምንሄድበትን መንገድ ቁጭ ብለን እንነጋገራለን እንጂ እንዲህ ትሆናለህ በሚል አይደለም። ኮንትራቱ ላይ በተቀመጠው መሰረት በአንድ ወገን ሆነ በጋራ ስምምነት የሚሆኑ ነገሮች ካሉ በምን መልኩ ይታያሉ የሚለው ነገር በግልፅ ስላለ በዛ መልኩ የሚታይ ነው የሚሆነው።”

👉ከዚህ ቀደም በነበረ መግለጫ የተሻለ ክፍያ በክለብ ማግኘት እችላለሁ ብለው ነበር አሁን የተሻለ ክፍያ አግኝተው ወይስ በምን ምክንያት የሀሳብ ለውጥ አድረጉ?

“ከሀገር ውጭ ያለውን ነገር ትተን በሀገር ውስጥ አንድ ክለብ ብይዝ የማገኘው ነገርን እዚህ ስላገኘው አይደለም የቆየሁት ያንን አላገኘሁም ማለት ከሁለት ከሦስት ቦታዎች ንግግሮች ነበሩ እሱ ግልፅ ነው ወደዚያ ለመሄድ ፌደሬሽኑን የጠየኳቸው ጥያቄዎች ነበሩ እነዚያ ጥያቄዎች ሙሉ ለሙሉ እንኳን ባይሆን እዚያ አካባቢ ከሆነ ሌላ ቦታ አገኝ የነበረውን ጥቅም ነገ ላገኘው ስለምችል ለጊዜው ገታ ባደርገው እዚህ ጋር ያለውን ሀገርን የመምራት በዋጋ የማይተመን ነገርን ማሳካት እችላለሁ። ሁለተኛው ነገር እዚህ ጋር ሆኜ በምሰራው መልካም ነገር ዛሬ ያጣሁትን ነገር ነገ በሁለት እጥፍ ማግኘት እችላለሁ የሚል እምነት አለኝ። እዚህ ጋር ቢያንስ በኑሮ የማልጎዳበትን ነገር እያገኘሁ ሀገሬን በማገልገል ቀጣዩን ነገር ማመቻቸት የምችልበትን ዕድል ስላገኘሁ ነው።”

👉በአሰልጣኝ ቡድኑ አባላት ደስተኛ ስለመሆኑ

“ፍፁም ደስተኛ ነኝ ፤ ክለብ ላይ ረጅም አመት ቆይቸሠለሁ ፤ ምናልባት አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከልምድ ባየሁት በሰጠሃቸው ልክ ላታገኝ የምትችልበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል ነገርግን አሁን አብራይቻው የምሰራቸው ባለሙያዎች ግን 100% ከመጀመሪያው ቀን አንስቶ በጣም የሚለፉ ልጆች ነው ያሉት በሙሉ ስታፉ እስከ ሌሊት 6(7) ቁጭ ብለው የሚሰሩበት ጊዜ አለ ስራቸው በጊዜ የተገደበ አይደለም በማንኛውም ሰዓት ደውዬ ብዙ ነገሮችን አብረን እንሰራለን። አብረውኝ እየሰሩት ባሉት በሁሉም ደስተኛ ነኝ ስለራሴ ይሄ ይሄ ቢሆን እንዳልኩት ሁሉ የእነሱን ነገር ከፍ እንዲያደርጉላቸው ጠይቅያለሁ ከእነሱ ጋር በንግግር የሚጨርሱት ነገር ቢሆንም እኔ ደሞዝ ከፍ ስላለ ውጤቶ አይመጣም ውጤት የሚመጣው በጋራ ስራ ነው።”

👉ባለፉት ሁለት ዓመት ያልሰራሁት አሁን እሰራዋለው ብሎ ስለሚያስው ጉዳይ….

“ባለፉት ሁለት ዓመታት ያልሰራናቸው በርካታ ነገሮች አሉ የሰራናቸው ነገሮችንም ደግሞ በቀላሉ መመልከት አልፈልግም በዚህ ጊዜ ውስጥ በዙ ነገር ለመስራት ሞክረናል ፤ ለምሳሌ እንደቀላል የሚነሳው 11 የወዳጅነት ጨዋታዎችን ማድረግ ችለናል ለምሳሌ ሁለቱ ከዛምቢያ ጋር ያደረግናቸው ጨዋታዎች በኮቪድ ሳቢያ እግርኳስ ለ7 ወራት በሀገራችን ከተቋረጠ በኃላ ቡድን ሰብስበን ለ13 ቀን ልምምድ ሰርተን ያደረግነው ነበር። ይህም ውድድር ባልነበረበት በዚህ ፍጥነት ቡድን አደራጅተን መቅረባችን አዲስ ልምድ ነው።”

“ብሔራዊ ቡድኑ ላይ እንዲሆን የምንፈልጋቸውን ነገሮች ለማስቀመጥ ሞክረናል ፤ ቡድኑ ፈታኝ አመት ነው ያሳለፈው ከተጫወትናቸው 19 የነጥብ ጨዋታዎች አራቱን ብቻ ነው በሜዳችን ያደረግነው 15 ጨዋታዎች ከሜዳ ውጭ ማድረግ ቀላል አይደለም በተለይ ከሜዳ ውጭ ያለንን ነገር ታሪክ ከማሻሻል አንፃር ጥሩ ስራዎችን ሰርተናል ፤ በሜዳ ሆነ ከሜዳ ውጭ ስንጫወት ተጫዋቾቻችንን በራስ መተማመመን ለማሳደግ የሰራነው ስራ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።”

“እኛ ቡድኑን ስንረከብ 146ኛ ነበርን ከሰሞኑ የቤልጅየም ብሔራዊ ቡድን በ2010 ከዓለም 62ኛ ነበር አሁን ግን 1ኛ እንዴት መምጣት ቻሉ የሚለውን ለመመልከት ሞክረናል እርግጥ እነሱ ብዙ ነገር በእቅድ ሰርተው ነው እዚህ የደረሱት ስለዚህ እኛም ቢያንስ ከ100 ባነሰ ደረጃ መገኘት የምንችለው የሚለው ነገር ዋነኛ የቤት ስራችን ነው። ባደረግናቸው የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከማሸነፍ እና ውጤት ከማስመዝገብ ባለፈ ቡድናችንን ለመስራት ነው እየተጠቀምንበት ያለነው አሁን ላይ እኛ ለመስራት እየሞከርን ያለነው አዲስ ባህል ለማስፈን ነው ለምሳሌ አፍሪካ ዋንጫ ስናልፍ ለ13 ያክል ቀናት ብቻ ነበር ዝግጅት ያደረግነው እንግዲህ ከዚህ ቀደም ለአህጉራዊ ውድድሮች ያለፉ ቡድኖች ከሀገር ውጭ ለበርካታ ጊዜያት ሲዘጋጁ ተመልክተናል በተመሳሳይ በሳምንቱ መጨረሻ ለምሳሌ ሱዳን እንገጥማለን ግን ተጫዋቾቹን የምናገኘው ነገ ነው ስለዚህ ጥቂት ቀናት ተዘጋጅተን ነው ይህን ጨዋታ የምናደርገው ስለዚህ አዲስ አይነት ልምምድ ወደ እግርኳሱ እያመጣን ነው ብዬ አስባለሁ።

አቶ ባህሩ ጥላሁንም የተወሰኑ አስተዳደራዊ ማብራሪያ በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።

👉የአሰልጣኝ ቡድን አባላትን ውል ከማራዘም ጋር በተያያዘ?

“ከእነሱም ጋር ተነጋግረናል በዚያም ደስተኛ መሆናቸውን ሰምተናል ፤ አንድ አሰልጣኝ ግን ከቤተሰብ ጋር ልነጋገር የሚል ሀሳብ አቅርቧል ከእሱ ጋር ቢሆንም ያን ያህል ሰፊ ልዮነት የለንም የመማከር ጉዳይ ስለሆነ ነው።

👉ስለ ክፍያው

“ይህን ሀላፊነት ወስጄ የነበርኩት እኔ ነበርኩ ከፍተኛ ተከተፋይ ከሆነው የሞሮኮ አሰልጣኝ እስከ ዝቅተኛ ተከፋዮችንም የእነ ሚቾን ጨምሮ ለመመልከት ተሞክሯል ፤ በቅድሚያ ያቀረበው ሀሳብ ምክንያታዊ አይደለም ያልነው የውበቱ ክፍያ ጥሩ ሆኖ አግኝተነዋል። በሊጉ ላይ ያለው የአሰልጣኞች ክፍያ ጤናማ ነው አይደለም የሚለው እንዳለ ሆነ የቀረበው ነገር ምክንያታዊ መሆኑ ላይ ተስማምተናል።”

“እኛ የምንከፍለው ከሌሎች ሀገራት አንፃር ዝቅተኛ ነው ነገርግን ሀገራችን ካለችበት ሁኔታ አንፃር ከፍተኛ ነው።”

በመጨረሻም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ እንደ አጀንዳ ተይዞ በነበረው የቻን አፍሪካ ዋንጫ ዙርያ የድሉን ትርጉም በአህጉራዊ ውድድሮች ከተሳተፉት ቡድኖች አንፃር እና ከሜዳ ውጭ በተደረጉ አራት ጨዋታዎች የተገኘ ከመሆኑ አንፃር በትልቁ ሊታይ ይገባል በሚል በሰጡት አጭር ገለፃ ፍፃሜውን አግኝቷል።