በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ የምድብ 2ኛ ጨዋታዎች ሞደርን ጋዳፊ እና ወልቂጤ ከተማ ወደ ግማሽ ፍፃሜው ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር በሦስተኛ ቀን ውሎው በሁለቱም ምድቦች ሁለተኛ ጨዋታዎች ተስተናግደውበታል። ከቀትር በፊት ረፋድ 4 ሰዓት ላይ የዩጋንዳው ክለብ ሞደርን ጋዳፊ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊውን ክለብ ድሬዳዋ ከተማን ገጥሞ ድል ቀንቶታል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ጥሩ የግብ ማግባት ዕድሎች ሲፈጠሩበት ተስተውሏል። ገና ጨዋታው እንደተጀመረም ሞደርኖች ኳስ በእጅ በመነካቱ የቅጣት ምት አግኝተው በካሉምባ ብሬን አማካኝነት ሞክረውት የመጀመሪያ ጥቃት ሰንዝረዋል። ለዚህ ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ያልቦዘኑት ድሬዳዋዎች በፈጣን ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ሄደው በአዲሱ ተጫዋቻቸው ያሬድ ታደሰ አማካኝነት ጥሩ አጋጣሚ ፈጥረው ተመልሰዋል።
በአሠልጣኝ ዋስዎ ቦሳ የሚመሩት ሞደርኖች በዋናነት ረጃጅም እና የቆሙ ኳሶችን ለመጠቀም ሲሞክሩ ታይቷል። በ20 እና 21ኛው ደቂቃም ሴረንኩማ ሲሞን በተመሳሳይ የግራ መስመር የተገኙ የቅጣት ምቶችን አሻምቶ ለግብ ቀርበው ነበር። በተለይ ሁለተኛው አጋጣሚ ሻፊቅ ባካኪ በሩቁ ቋሚ ተገኝቶ ቢሞክረውም ለጥቂት ወጥቶበታል። ምንም እንኳን ጫና ቢበዛባቸውም እየተቋቋሙ ወደ ፊት መሄድ የቀጠሉት ድሬዳዋዎች ከውሃ እረፍት መልስ እጅግ ለመሳት የሚከብድ ኳስ አምክነዋል። በዚህም ከግራ መስመር የተሻማውን ኳስ ግብ ጠባቂው መቆጣጠር ሲሳነው ያገኘው አጥቂው ቢኒያም ጌታቸው አጋጣሚውን አምክኖታል።
ጨዋታው 34ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግን ግብ ተስተናግዷል። በዚህም ኳስ በእጅ በመነካቱ ከወደ ቀኝ ካደላ ቦታ የቅጣት ምት ያገኙት ድሬዎች በጋዲሳ መብራቴ አማካኝነት አሻምተውት ቁመታሙ ተከላካይ አሳንቴ ጎድፍሬድ በግንባሩ ግብ አድርጎታል። የድሬዎች መሪነት ግን ከደቂቃ በላይ መቆየት አልቻለም። በዚህም ሙሲጊ ቻርልስ ከቀኝ መስመር የተላከለትን ኳስ በግንባሩ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል። በ41ኛው ደቂቃ ደግሞ ሴረንኩማ ሲሞን ከሳጥኑ ጫፍ ድንቅ የቅጣት ምት ግብ አስቆጥሮ ሞደርን ወደ መሪነት ተሸጋግሯል።
በስድስት ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ግብ ያስተናገዱት ድሬዎች አጋማሹ ሊገባደድ ሲል በመስመር ተከላካያቸው እንየው ካሣሁን አማካኝነት ጥሩ ሙከራ ቢያደርጉም ከግብ ጋር መገናኘት አልቻሉም። በሁለተኛው አጋማሽም በተሻለ ወደ ግብ ለመድረስ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ቀይረው ለማስገባት ሞከረዋል። በተለይ በአምስት ተከላካይ የተዋቀረውን የኋላ መስመር ዘርዘር በማድረግ ወደፊት ለመግፋት እና ጫና ለመፍጠር ወጥነው ነበር። ነገርግን የሚፈልጉትን ያገኙት ሞደርን ጋዳፊዎች ወደ ራሳቸው ሜዳ ወረድ ብለው ለመጫወት ያደረጉትን ጥረት ማስከፈት አልቻሉም። ጨዋታውም በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩት ግቦች ፍፃሜውን አግኝቷል። ውጤቱን ተከትሎ ሞደርን ጋዳፊ ከሁለት ጨዋታዎች 6 ነጥብ በማግኘት ግማሽ ፍፃሜውን መቀላቀሉን አረጋግጧል።
በመርሐ-ግብሩም ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው የሞደርን ጋዳፊው ኦሶንጎ ጆንሰን የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል።
ከጨዋታው በኋላ የድሉ ባለቤት ሞደርን ጋዳፊ አሠልጣኝ ዋስዋ ቦሳ “ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ ጥሩ ተጫውተን አሸንፈናል። ተጋጣሚው ቡድን በጣም ጥሩ ነበር። ተጋጣሚ እንዴት እንደሚጫወት አላውቅንም ነበር ፤ ጨዋታውንም ማረጋጋት ነበረብን። አላማችን ጨዋታዎችን ማሸነፍ እና ዋንጫውን ማንሳት ነው።” የሚል ሀሳባቸውን አጋርተውናል።
አሠልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ በበኩላቸው “ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ የወዳጅነት ጨዋታ ራስህን የምትለካበት ነው ፤ ቢሆንም ግን ማሸነፍ አለብህ። የምንፈልገውን ነገር አግኝተንበታል። ከኢትዮጵያ ውጪ ያለ ክለብም ይሁን የሀገር ውስጥ አንድ ነገር ነው እኛ ያለን። እግርኳስ ጨዋታ ላይ ስህተት ይኖራል ፤ ግን ያ ስህተት ሁሌ መፈጠር የለበትም ፤ ያንተ ስህተት ለነሱ ይጠቅማል። ግብ ጠባቂ እና ተከላካይ መናበብ አለባቸው ስህተት መፈጠር የለበትም። የእነሱ ስህተት ዋጋ ሊያስከፍልህ ይችላል። የተቆጠረብን ግብም በዛ ምክንያት ነው። እነዚህን ስህተቶች በልምምድም ተጫዋቾቹን በመንገርም ማስተካከል አለብን። እቅዳችን በያዝነው ነገር ስህተቶችን አርመን ማሸነፍ ነው ፤ ነገ ከባሕርዳር ጋር ላለብን ጨዋታ ዛሬ የተጫወቱትን ተጫዋቾች አሳርፈን ላልተጫወቱት ቅድሚያ እንሰጣለን። ፕሪሚየር ሊጉን በዚህ መልክ ነው እንቀርባለን ብለን ያሰብነው።” በማለት የድህረ-ጨዋታ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የሆነው የቡል እና ወልቂጤ ከተማ መርሐ-ግብር ደግሞ በሁለቱ አጋማሾች በተቆጠሩት ሁለት ግቦች በአቻ ውጤት ተገባዷል።
በሳምንቱ መጨረሻ የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የመልስ ጨዋታ የነበረባቸው ቡሎች በትናንትናው ዕለት ወደ ባህር ዳር መግባታቸው ይታወቃል። ቡድኑ ቀትር ላይ ባህር ዳር ከገባ በኋላ አመሻሽ ላይ ቀለል ያለ ልምምድ አድርጎ ለዛሬው ጨዋታ መቅረቡ ትንሽ እንዳዳከመው መመልከት ተችሏል። ወልቂጤ ከተማዎችም በትናንትናው ዕለት የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አከናውነው ባለው የመርሐ-ግብር መጣበብ ዛሬ ጨዋታቸውን ማድረጋቸው ትንሽ ፈተና ቢሆንባቸውም የተጫዋቾች ለውጦችን አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ፈጣን ሽግግሮች የነበሩበት ይህ ጨዋታ የመጀመሪያውን ሙከራ ያስተናገደው በ10ኛው ደቂቃ ነበር። በዚህም ካላንሳ ፍራንክ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ሳጥን ውስጥ ያገኘውን ኳስ ሞክሮ አግዳሚውን ታኮ ወጥቶበታል። ከዘጠኝ ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ወልቂጤ ከተማዎች ከቀኝ መስመር የተሻማን ኳስ ሳሌም አ/ሰላም በግንባሩ በሞከረው ኳስ የቡልን የግብ ክልል ፈትሸው ተመልሰዋል። በላይኛው ሜዳ ተጭኖ ለመጫወት የሞከሩት ቡሎች በ23ኛው ደቂቃ የወልቂጤ ተከላካዮች የሰሩትን የቅብብል ስህተት ተጠቅመው ያገኙትን አጋጣሚ ካላንሳ ፍራንክ ቢሞክረውም ዒላማውን ስቶበታል።
እስከ 39ኛው ደቂቃ ድረስ ፍልሚያው ኳስ እና መረብ ሳይገናኝበት ቢቀጥልም በ40ኛው ደቂቃ ግብ አስተናግዷል። በተጠቀሰው ደቂቃም መነሻውን ከመሐል ሜዳ ያደረገው ኳስ አቡበከር ሳኒ በጥሩ ሽግግር ወደ ቀኝ መስመር ከሳሙኤል አስፈሪ ተቀብሎ ነፃ አቋቋም ላይ ለሚገኘው አንዋር ዱላ አሻግሮለት አኑዋር በግንባሩ በመግጨት የመጀመርያውን ጎል ለሠራተኞቹ አስቆጥሯል።
ቡድኖቹ ከዕረፍት እንደተመለሱ በ47ኛው ደቂቃ ሳይጠበቅ በጥሩ የኳስ ንክኪ ወደ ሳጥን የደረሱት ቡሎች በድንቅ አጨራረስ አጥቂው ከሪም ንዶግዋ የአቻነት ጎል በማስቆጠር ወደ ጨዋታው እንዲመለሱ አስችሏቸዋል።
የአቻነቱ ጎል ከተቆጠረ በኋላ ጨዋታው ወደ ጥሩ ፉክክር ያመራል ቢባልም እየተቀዛቀዘ ሄዶ ወደ ጨዋታው መገባደጃ አስር ደቂቃዎች ሲቀረው በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል የመድረስ ጥረቶች ተመልክተናል። በተለይ ሠራተኞቹ ከማዕዘን ምት የተሻገሩትን የቡል ግብጠባቂ ኳሱን መቆጣጠር አቅቶት የተፋውን አግኝተው ወደ ጎል ሲመቱት በተከላካዮች ተደረቦ ሲመለስ ዋሀቡ አዳምስ ተገልብጦ ወደ ጎል ሞክሮት በግቡ አናት የወጣው በጨዋታው የተመለከትነው ተጠቃሽ ሙከራ ነበር።
በተጨማሪ ደቂቃ የወልቂጤው አማካኝ ተስፋዬ መላኩ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የጨዋታው ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በቀጥታ የቀይ ካርድ ከሜዳ አስወግደውታል። ጨዋታውም አንድ አቻ ተጠናቋል። በውጤቱ መሠረት ወልቂጤ ከተማ 4 ነጥቦችን በመያዝ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል።
የወልቂጤ ከተማው ተከላካይ ሳሙኤል አስፈሪ የጨዋታው ኮከብ በመባል ተመርጦ ሽልማቱን ተረክቧል።
አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ከፍልሚያው መገባደድ በኋላ “ትናንት ዘጠና ደቂቃ ለተጫወተ ቡድን ዛሬ በድጋሚ መጫወት በጣም ከባድ ነው። ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ እንቅስቃሴውም በምንፈልገው መንገድ እየሄደልን ነው። ቡድናችን ይሄንን ውድድር ማግኘቱ ለፕሪሚየር ሊጉ ከፍተኛ እገዛ እያደረገልን ነው። የአፍሪካ ቡድኖች ከመስመር እንደሚጫወቱ እናውቅ ነበር ፤ ስለዚህ ያን የመስመር ቦታ በመዝጋት በራሳችን የጨዋታ መንገድ ለመሄድ ነበር የፈለግነው ፤ ለዛም ጥሩ ተጫውተናል። የተቆጠረብን ግብም ከዕረፍት እንደገባን የተጫዋቾቼ ትኩረት ማጣት ነው። ተጫዋቾችን እስከ 70 ሜትር ማድረስ ነው የኔ ሥራ ከዛ በኋላ የእነሱ ስራ ነው። ውድድሩ በጣም ይጠቅማል። ተጫዋቾች ወደ ጨዋታ ስሜት እንዲገቡ ለማድረግ ፣ የምንጫወትበትን አካባቢ አየር ለመልመድ እና ተጫዋቾች እንዲዋሃዱም ይረዳናል። ስለዚህ ይሄንን ውድድር በማግኘታችን ዕድለኞች ነን።” ሲሉ ተደምጠዋል።
የቡል አሠልጣኝ አሌክስ ኢሳቢሪዬ “ጨዋታው ጥሩ ነበር ፤ አቻ አልቋል። ድካም አለብን ያለፈው ቅዳሜ ፈታኝ ጨዋታ ነበር የተጫወትነው። 10 ተጫዋቾች ለ 70 ደቂቃ ያህል ተጫውተዋል እና በቀጥታም ወደዚህ መጓዝ ነበረብን። ድካም አለው ተጫዋቾች በቂ ዕረፍት አላደረጉም። የእሱ ተፅዕኖ እንዳናሸንፍ አድርጎናል። ተጫዋቾች ካለባቸው ድካም እና ሜዳ ላይ ካሳዩት ነገር አንጻር አቻ ውጤት በቂያችን ነው። ጨዋታው በጣም ጠቃሚ ነው። ተጫዋቾቼ በድካም ውስጥ ሲሆኑ እንዴት እንደሚጫወቱ ለማየት ችያለሁ ፤ ሌላኛው ጥቅም ተከታታይ ጨዋታዎችን ከተጫወትን ረዥም ጊዜ ስለሆነን ለሊጋችን በጣም ይጠቅመናል።” በማለት ሀሳባቸውን አጋርተውናል።