ኢትዮጵያ ቡና የመስመር ተከላካይ አስፈርሟል

ከአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ጋር በደቡብ ፖሊስ መስራት የቻለው የመስመር ተጫዋች ወደ ኢትዮጵያ ቡና አምርቷል።

ራሱን በበርካታ ዝውውሮች እያጠናከረ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና ከኦሮሚያ ትምህርት ቤቶች ውድድር ከተገኘ በኋላ በገላን ከተማ ፣ ነገሌ ቦረና ፣ ደቡብ ፖሊስ እና ሀዋሳ ከተማ የተጫወተው ዘነበ ከድርን ወደ ቡድኑ መቀላቀል ችሏል።

2012 ላይ በደቡብ ፖሊስ ከአሰልጣኝ ተመስገን ዳና ጋር የመስራት አጋጣሚን አግኝቶ የነበረው ተጫዋቹ በወቅቱ ኢትዮጵያ ቡናን ለመቀላቀል ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ከውል አለመጠናቀቅ ጋር በተገናኘ ሳይሳካለት ቀርቶ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ቡና ለቀናቶች የተሰጠውን የሙከራ ዕድል በአግባቡ መጠቀሙን ተከትሎ በሁለት ዓመት ውል አዲሱ የቡናማዎቹ ፈራሚ ሆኗል፡፡

ከክለቡ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ በሙከራ ላይ የነበረው ኬኒያዊው ግብ ጠባቂ ጃኮብ ሆሳኖ አሰልጣኝ ተመስገን ዳናን ማሳመን ባለመቻሉ ወደ ሀገሩ ሲመለስ በአሰልጣኝ ከማል አህመድ አካዳሚ ያለፉትን ስድስት ዓመታት ሲሰለጥን የነበረው ወጣቱ አማካይ መላኩ አየለ ቡናማዎቹን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሷል፡፡

ያጋሩ