ዛሬ በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ የምድብ ሀ ሁለት ጨዋታዎች ተከናውነው ውድድሩ ወደ ግማሽ ፍፃሜ አምርቷል።
ቡል 14-0 ኮልፌ ተስፋ
በፀሐያማ እና ሞቃታማ የአየር ሁኔታ በተደረገው የቀኑ የመጀመሪያ ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 11 ደቂቃዎች ሦስት ግቦች የተስተናገዱበት ነበር። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ ለመንቀሳቀስ የሞከሩት ኮልፌዎች 8ኛው ደቂቃ ላይ እስማኤል ኢብራም ለአብዲ ሁሴን ሰጥቶት ግብ ማስቆጠር ቢችልም ጎሉ ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሯል።
ኮልፌዎች ከሜዳቸው ኳስ መስርቶ ለመውጣት መቸገራቸውን ተከትሎ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ምቹ አጋጣሚ ያገኙት ቡሎች በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ሦስት ግብ አስቆጥረዋል። የመጀመሪያውን ግብ 9ኛ ደቂቃ ላይ ማርቲን አፕሬም ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ከሳጥኑ ጫፍ ላይ የነበረው ኦኬቼ ሲሞን በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ወደ ቀኙ የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ላይ ማያና አንቶኒ ቺፕ ያደረገውን ኳስ ካላንዳ ፍራንክ በቀላሉ አስቆጥራል። በድጋሚ የኮልፌዎችን አለመረጋጋት ተከትሎ በአንድ ደቂቃ ልዩነት ግብ የማስቆጠር አጋጣሚ ያገኘው ንሲምቤ ኢብራህ የቡድኑን መሪነት ወደ ሦስት ግብ ልዩነት ማሳደግ ችሏል።
ኮልፌዎች በተጋጋሚ ኳስ መስርተው በመውጣት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም የመጨረሻ ኳሳቸው ውጤታማ አልነበረም። 19ኛው ደቂቃ ላይ ኦኬች ሲሞን ለራሱ ሁለተኛውን ለክለቡ አራተኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ማርቲን አፕሬም ከቀኝ መስመር ያቀበለውን ኳስ ካላንዳ ፍራንክ ማስቆጠር ችሏል። ኮልፌዎች የመጀመሪያውን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉት 25ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን አብዲ ሁሴን ድንቅ የቅጣት ምት ከግራ መስመር ቢሞክርም ግብ ጠባቂው አድኖታል።
ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር የቡሎች የበላይነት እየቀጠለ የሄደ ሲሆን 35ኛው ደቂቃ ላይ ማርቲን አፕሬም ተካላካዮችንና ግብ ጠባቂውን በማለፍ በድንቅ አጨራረስ ለቡል 6ኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ኮልፌዎች በኤልያስ መንግሥቱ ግብ ለመፍጠር ቢሞክሩም ውጤታማ መሆን አልቻሉም። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ማርቲን አፕሬም በ42ኛው እና 45ኛ ደቂቃ ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ የመጀመሪያው አጋማሽ 8-0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ በሁለት ደቂቃዎች ውስጥ ማርቲን አፕሬም ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ማያና አንቶኒ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል። በአምስት ደቂቃዎች ልዩነት ኦኬች ሲሞን ከ ካላንዳ ፍራንክ በተቀበለው ኳስ ግብ ጠባቂውን በማለፍ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ 10-ዐ ማስፋት ችሏል። 59ኛው ደቂቃ ላይ ወደፊት ተጠግቶ ከራሱ ግብ ወጥቶ የነበረውን የኮልፌ ግብ ጠባቂ መውጣት የተመለከተው ንሲምቤ ኢብራህ ከማርቲን አፕሬም የተቀበለውን ኳስ ከረጅም ርቀት ማስቆጠር ችሏል። 66ኛው ደቂቃ ላይ ኑዱግዋ ከሪም በተመሳሳይ ሁኔታ ከመሃል ሜዳ ማስቆጠር ሲችል በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ማያና አንቶኒ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ካላንዳ ፍራንክ በቀላሉ አስቆጥሮ ሐትሪክ ሠርቷል።
ኮልፌዎች ከዕረፍት መልስ የተሻለ ወደተጋጣሚ የግብ ክልል ተጠግተው የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ 74ኛው ደቂቃ የተሻለውን ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በዚህም ኢዮብ በቀለ ባቀበለው ኳስ ከግቡ በግራ መስመር የነበረው ትንሣኤ ድንቅ የግብ ማግባት ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው አድኖበታል። 84ኛው ደቂቃ ላይ ንዱግዋ ከሪም ለቡል ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 14-0 በሆነ ሰፊ በሆነ ውጤት ጨዋታው ተጠናቋል። በውጤቱም መሠረት ከምድብ 2 ቡል ኤፍ ሲ እና ወልቂጤ ከተማ ወደ ግማሽ ፍጻሜ አልፈዋል።
በጨዋታው ሦስት ጎሎችን ያስቆጠረው እና አራት ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ያቀበለው ማርቲን አፕሬም የጨዋታው ኮከብ በመባል ተመርጧል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የቡሉ አሰልጣኝ አሌክስ ኢሳቢሪዬ የሚከተለውን የድኀረ ጨዋታ አስተያየት አጋርተውናል።
“ጨዋታው ጥሩ ነበር አሸንፈናል ፤ ግን አሁንም ተጫዋቾቼ ከሰውነታቸው ጋ ልክ አይደሉም እየታገሉ ነው። ማስተካከል እና ማገገም አለብን። ቀጣይ ጨዋታ ቀላል የሚሆንልን አይመስለኝም ምክንያቱም በቂ ዕረፍት አላደረግንም ፤ ዕረፍት ማድረግ ይኖርብናል። ውጤቱ በጣም ጥሩ ነው 14 ለ 0 አሸንፈናል ይሄ ማለት በአዕምሮ ዝግጅት ጥሩ ነን ማለት ነው ፤ ግን ሰውነታችን ልክ አይደለም። ማለት የምችለው ተጋጣሚው ቡድን ጥሩ ነበር ፤ እኛም የመጀመሪያችን ነው ከሀገር ውጪ እንደዚህ ዓይነት ጨዋታ ስንጫወት። ሞቃቱ አየርም ተመችቶኛል በሊጋችን ለምናደርጋቸው ውድድሮች ይጠቅሙናል። ስለ ተጋጣሚ አጨዋወት መንገድ ምን ማለት አልችልም ፤ ሥራዬ የራሴን ቡድን መመልከት ነው ፤ ለማድረግ ያሰቡት ነገርም ይኖራል ግን አላወቅኩም ፤ አስተያየት መስጠት አልችልም። ፍላጎታችን ጨዋታዎችን አሸንፎ ዋንጫ ማንሳት ነው።”
ባሕር ዳር ከተማ 0-0 ድሬዳዋ ከተማ
ምቹ በሆነ የአየር ሁኔታ በተደረገው የባሕር ዳር ከተማ እና በድሬዳዋ ከተማ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ መጠነኛ ፉክክር የታየበት ነበር። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ድሬዳዋ ከተማዎች በጫላ በንቲ እና በሙኸዲን ሙሳ የተለያዩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። የመጀመሪያው አደገኛ ሙከራ የተሞከረው 14ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን በተጠቀሰው ደቂቃም ጫላ በንቲ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ከግራ መስመር ጥሩ ሙከራ ወደ ግብ ቢሞክርም ግብ ጠባቂው ወደ ማዕዘን ሊያስወጣው ችሏል። የመጀመሪያ አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ወደፊት ተጭነው የተጫወቱት ባሕርዳር ከተማዎች በፍፁም ጥላሁን ፣ በኦሴ ማውሊ እና በተስፋዬ ታምራት የተለያዩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም ውጤታማ አልነበሩም።
ከዕረፍት መልስ ተቀዛቅዞ በቀጠለው ጨዋታ የተሻለ የግብ ማግባት አጋጣሚ የተፈጠረው 55ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን በተጠቀሰው ደቂቃም ኦሴ ማውሊ ቻርለስ ሪባኑ አመቻችቶ ባቀበለው ኳስ ግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ሳይጠቀምበት ቀርቶ ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል። በ4 ደቂቃዎች ልዩነት ከቀኝ መስመር መሳይ አገኘሁ ከማዕዘን ቢያሻማም ግብ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው ተስፋዬ ታምራት ያደረገው ሙከራ ኢላማውን የጠበቀ አልነበረም። 67ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ አገኘሁ በግራ መስመር ከተሰጠ የቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ ፍጹም ጥላሁን ኳሱን በግንባሩ በትክክል ባለማግኘቱ ያባከነው የግብ ዕድልም የሚያስቆጭ ነበር።
በድሬዳዋ በኩል ከዕረፍት መልስ የመጀመሪያው የተሻለ ሙከራ የተደረገው 73ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን በተጠቀሰው ደቂቃም ቢንያም ጌታቸው ወደግብ የሞከረው ኳስ በግብ ጠባቂው ሲመለስ ከሳጥን ውጪ ያገኘው እንየው ካሳሁን ወደ ግብ ቢሞክርም ኳሱ የቀኙን ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። 85ኛው ደቂቃ ላይ ተስፋዬ ታምራት ከቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ ይሄነው የማታ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ግብ ቢሞክርም ኢላማውን የጠበቀ አልነበረም። የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ላይ የድሬዳዋው ቢንያም ጌታቸው ተከላካዮችን አታሎ ማለፍ ቢችልም ኃይል ባልነበረው ሙከራ የግብ ማስቆጠር ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ይሄም የጨዋታው የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎ ከምድብ 1 ሞደርን ጋዳፊ እና ድሬዳዋ ከተማ ወደ ግማሽ ፍጻሜው አልፈዋል።
የባህር ዳሩ አማካይ ቻርለስ ሪባኑ የጨዋታው ኮከብ በመሆን ተምርጧል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አሰልጠኞች የድኅረ ጨዋታ አስተያየት ሲሰጡ
የድሬዳዋ ከተማው አሠልጣኝ ዮርዳኖስ አባይ “በመጀመሪያውም ሆነ በዛሬው ጨዋታ አንድ ዓይነት አጨዋወት ነው የተከተልነው። ጨዋታውን ለማሸነፍ ነበር ወደ ሜዳ የገባነው። ለማሸነፍ ደግሞ ግብ ማስቆጠር ያስፈልጋል። ዞሮ ዞሮ ወጣት ተጫዋቾችን ለመጠቀም ሞክረናል። በእነርሱም ጥሩ ነገር አይተናል። ውጤት የምናመጣው በህብረት ነው። በህብረት ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈናል ፤ በማለፋችን ደግሞ አንድ ተጨማሪ ጨዋታ አግኝተናል። ያንን ካሸነፍን ደግሞ ለፍፃሜ እንደርሳለን። ከዋናው ውድድር በፊት ጨዋታዎችን ማግኘታችን ደግሞ ለእኛ ጥሩ ነው። በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ውጤቱን ለማስጠበቅ ያደረግነው ነገር ጥሩ ነው። ምክንያቱም ሊጉ ላይም እንደዚህ ዓይነት ነገር ስለሚያጋጥም። ቡድኑ ላይ ያለው የአጨራረስ ችግሩ መቀረፉ አይቀርም። ውድድሩ ላይ በእርግጠኝነት ግብ የሚያስቆጥር ቡድን ይኖረናል። ያሉት አዳዲስ ተጫዋቾችም ሆነ ወጣቶቹ ጥሩ ናቸው። ይህ ውድድር ያሉ ክፍተቶችን ለማየት ስለሆነ ይህንን እናስተካክላለን። በተለይ ፊት አካባቢ ያሉ ነገሮችን በሂደት እያስተካከልን እንሄዳለን።” የሚል ሀሳቡን አጋርተውናል።
በዚህ ውድድር ቡድኑን ሲመሩ የነበሩት ምክትል አሠልጣኙ ደረጄ መንግሥቱ በበኩላቸው “ከመጀመሪያው ጨዋታ ዛሬ የተሻለ ለመንቀሳቀስ ሞክረናል። ቶሎ ቶሎም ወደ ጎል ለመድረስ ጥረናል። ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ደግሞ አለመረጋጋት ነበር። ማሸነፍ ግዴታችን ስለነበር ትንሽ መረጋጋት አልቻልንም። እንደዚህ ዓይነት ጨዋታዎች የሚጠቅሙን እንደዚህ ዓይነት ስህተቶችን ለማየት ነው። የሊጉ ጨዋታዎች ከመጀመራቸው በፊትም ያሉብንን ክፍተቶች ለማሻሻል እንሰራለን። ከባዱ ነገር ጎል ላይ መድረስ ነው። ዛሬም ብዙ ወደ ጎል ሄደን ነበር። ቀላሉ ነገር መጨረስ ነበር። ይህ አልሆነም። ግን እነ አደም አባስ እና ፍፁም ከጉዳት ነው የመጡት። ሙሉ ስብስባችንንም አላገኘንም። በመከላከሉ ረገድ ግን ከመጀመሪያው ጨዋታ ለውጦች አሉ። ዋነኛ ተጫዋቾቻችን እነ ፈቱዲን እና ያረለድ የሉም። እነሱ ሲመጡ የተሻለ ይሆናል።” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
የውድድሩ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ነገ የሚደረጉ ሲሆን 7:30 ላይ ድሬዳዋ ከተማ ከ ቡል እንዲሁም 09:30 ላይ ወልቂጤ ከተማ ከ ሞደርን ጋዳፊ ይገናኛሉ።