ሲዳማ ቡና አሰልጣኙን በይፋ ሾሟል

ከወራት በፊት አሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመን ለመሾም ስምምነት ፈፅሞ የነበረው ሲዳማ ቡና ለአሰልጣኙ የሁለት ዓመት ኮንትራት ሲሰጥ ሦስት ተጫዋቾችን ከታዳጊ ቡድኑ አሳድጓል፡፡

ለ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በሀዋሳ ታደሰ እንጆሪ ማረፊያውን አድርጎ ዝግጅቱን እየከወነ የሚገኘው ሲዳማ ቡና ከወራት በፊት አሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመን ለመሾም ቅድመ ስምምነት የፈፀመ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ በይፋ አሰልጣኙ ለቀጣዮቹ ሁለት የውድድር ዓመታት ክለቡን በዋና አሰልጣኝነት እንዲመሩ ኃላፊነት ሰጥቷል፡፡ አሰልጣኙ ክለቡን ከዚህ ቀደም በተጫዋችነት እና ከ20 ዓመት በታች አሰልጣኝነት ያገለገሉ ሲሆን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ረዳትነት እንዲሁም በባሕር ዳር የተደረጉ ጨዋታዎችን በጊዜያዊ አሰልጣኝነት መርተው ክለቡ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ እስካሁን ስምንት አዳዲስ ተጫዋቾች ያስፈረመው ሲዳማ ቡና በቀጣዩቹ ቀናት በሙከራ ተመልክቶ ከሚጨምረው አንድ ተጫዋች ውጪ ተጨማሪ ተጫዋች የማያካትት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በክለቡ ከ20 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ጥሩ ግልጋሎት ሲሰጡ የነበሩ ሦስት ታዳጊ ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን ስለማሳደጉ ሶከር ኢትዮጵያ አውቃለች፡፡ በፍቅር ግዛቸው (አጥቂ) ፣ ይስሀቅ ከኖ (የመስመር ተከላካይ) ፣ በላይ በልጉዳ (የተከላካይ አማካይ) በአሰልጣኝ ወንድማገኝ ይሁንታ አግኝተው ያደጉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡