ከዛሬው ጨዋታ በኋላ ከአሠልጣኝ ሰዒድ ኪያር ጋር የተደረገ ቆይታ

👉”በአንድ ጨዋታ ብዙ ጎል ስለተቆጠረ የሚፈጠር ነገር የለም ፤ እኛም በተመሳሳይ መንገድ ብናሸንፍ የሚፈጠር ነገር የለም”

👉”…ብዙ ጎሎች ገብተዋል ፤ በእኔ እሳቤ ግን በጣም ትንሽ ነው የሚል ነው”

👉”ክለቦች እኛን አሸንፈው ደስተኛ የሚሆኑ ከሆነ እነሱ ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል”

👉”40 ቢገባም 14 ቢገባም እንዲሁም ብናሸንፍም እኛው ነን ሀኃላፊነቱን የምንወስደው”

👉”በ90 ደቂቃ የሚገነባም ሆነ የሚፈርስ ሀሳብ የለም ሁሉም በሂደት ነው”

ከዩጋንዳው ክለብ ቡል ጋር ያደረጋችሁት ጨዋታ እንዴት ነበር ?

“ጨዋታው በጣም አሪፍ ነበር ፤ ምናልባት ብዙ ጎሎች ገብተዋል ፤ በእኔ እሳቤ ግን በጣም ትንሽ ነው የሚል ነው። ምክንያቱም እኛ እዚህ ጋር መጥተን ልንሞክረው የምንፈልገው ነገር ከቁጥሮች ጋር የሚገናኝ ነገር አይደለም። 45 ቢገባ 14 ቢገባ እኛ ባሉን ልጆች ሀላፊነቱን የምንወስደው እኛ ነን። ግን ደግሞ በተበታተነ መንገድ የመጡ ልጆች ናቸው በእነሱ ማድረግ የምንችለው ነገር ነው። በጣም ጥሩ ነገር ነው ያየነው። መስተካከል የሚችሉ ነገሮች ተስተካክለው በዚህ መንገድ ጥሩ ነገር መስራት እንደሚቻል አይተናል ፤ በአንድ ጨዋታ ብዙ ጎል ስለተቆጠረ የሚፈጠር ነገር የለም እኛም በተመሳሳይ መንገድ ብናሸንፍ የሚፈጠር ነገር የለም እና ብዙ ጥሩ ነገር ያየንበት ጨዋታ ነበር።”

በጨዋታው የተመለከታችሁት ጥሩ ነገሮች ምን ነበሩ ?

“የእኛ ድክመት ነው ግቡ እንዲበዛ ያደረገው። ምክንያቱም የሚጣሉ ኳሶች አሉ። ለምሳሌ አራቱ ተከላካዮች ለመጀመሪያ ጊዜ አብረው ተሰልፈዋል አይግባቡም በዚህ ደረጃ አብሮ የቆየ ቡድን ለመግጠም ፈታኝ ነው። ግን ደግሞ አብሮ ቢግባቡ የሚቀረፉ ነገሮች ነበሩ እነሱን መቅረፍ ይቻላል ነበር። ከ16 ዓመት እስከ ክለብ ተጫዋች ነው የያዝነው በየቀኑ ልምምድ አይሰሩም፣ ምንም በጀት የላቸውም፣ ምንም የሚደረግላቸው ነገር የለም፣ በሳምንት ሁለት ቀን ሜዳ ከተገኘ እየሰሩ የመጡ ልጆች ናቸው። ስለዚህ እኛ በዚህ ደረጃ የምንሞክርበት ቡድን ስለሆነ ለየትኛውም ነገር ሀላፊነት እንወስዳለን ለተጫዋቾቹም። በጣም ደስ የሚለው ነገር በዚህ ሂደት ውስጥ ተጫዋቾች የሰሩትን ስህተት ያውቃሉ ማስተካከል እንደሚቻል ያውቃሉ። በብዙ ጎሎች የሚፈጠር ምንም ነገር እንደሌለ ያውቃሉ በዚህ እኛ ደስተኞች ነን።”

ግቦቹ እንዲበዙ ያደረገውስ ምክንያት ምንድን ነው ?

“በጣም አሪፉ ነገር በተጫዋቾቹ ውስጥ የጨዋታው እምነት እንዳለ በየትኛውም የጨዋታ ደቂቃ ጎሎቹም እየተቆጠሩ ማድረግ የምንፈልገው ነገር ያንን ነው። እየደጋገምን ማድረግ የምንፈልገው የሚቆጠርብን ከጀርባ እያጠቃን ሳለ በሚቆረጡ ኳሶች ነው። ያንን ማቆም ስንችል ሁሉን ማቆም እንደምንችል ይገባናል። ግን ደግሞ እስከመጨረሻው በዛ ውስጥ ሄደናል። ታዳጊዎች አሉ ልምድ ያላቸው ትንሽ አሉ አብረው። ምንም ዝግጅት አላደረጉም። ምናልባት ክለቦች እኛን አሸንፈው ደስተኛ የሚሆኑ ከሆነ እነሱ ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል። ለምን እነሱ በጀት የቆረጠላቸው ወሩን ሙሉ የሚዘጋጁ ሁሉን ነገር ያደረገላቸው አካል አለ። ይሄ የእኛ ቡድን ነው ፤ የምንፈልገውን ነገር የምንሞክርበት የራሳችን ቡድን። ስለዚህ ይሄ 40 ቢገባም ሀላፊነቱን እኛ ነን የምንወስደው ፤ 14 ቢገባም እኛው ነን ሀላፊነት የምንወስደው ፤ ብናሸንፍም እኛው ነን ሁሉን ነገር የምንወስደው። ስለዚህ ያየሁት ጥሩ ነገር በተጫዋቾቹ አዕምሮ ውስጥ ያለው ነገር ያ ነው። ይሄ አማተር ቡድን ነው። እንደእነሱ ፕሮፌሽናል አይደለም። ከተለያየ ቦታ ነው የተሰባሰቡት። ከሀረር፣ ከድሬዳዋ፣ ከጅቡቲ፣ ከአዲስ አበባ እና ከኮረም መጥተው ተሰባስበው ነው ያስገባናቸው። በዚህ አጋጣሚ ጎፈሬን ለማመስገን እወዳለሁ። ምንም እንኳን ውጤቱ ሰፊ ቢሆንም ጎፈፌ ይህ እድል ሰጥቶናል ነገ ከነገ ወዲያ ለሚፈጠረው ጥሩ ነገር ዛሬ መነሻ ነው። ዛሬ ጨዋታው እና ሂደቱ በጣም ደስ ያለና ለውጥ ማምጣት እንደምንችል የምናስብበት ጨዋታ ነው ያየነው።”

ይህ መነሻ ከሆነ ሀሳቡን በደንብ ለማውረድ ምን ያክል ጊዜ ይፈልጋል ?

“በነገራችን ላይ በ90 ደቂቃ የሚገነባም ሆነ የሚፈርስ ሀሳብ የለም ሁሉም በሂደት ነው። በተገቢው ሁኔታ በተገቢው ቦታ ተገቢው ተጫዋቾች ሲገኙ እንደገና ደግሞ በየቀኑ ልምምድ ስትሰራ ቡድን ስትሆን ማለት ነው ሀሳቡ ተደምሮ በየትኛውም ቡድን ላይ ያለምንም ጥርጥር ለውጥ መፍጠር ይችላል። አሁን እኛ እዚህ ጋር የምንሞክረው ተያይተው የማይተዋወቁ ተጫዋቾች ሜዳ ውስጥ አስገብተን የምንሞክርበት ምክንያት ሙከራ በራሱ አንድ ነገር ስለሆነ ነው። ስትሞክር ስትወድቅ ነው። እነዚህን ልጆች ይዘን ባንሞክርስ ባንመጣስ ምንም የምንማረው ነገር አይኖርም። በሚቀጥለው ደግሞ የሚግባቡ የሚተዋወቁ የሁል ጊዜ ስራቸው የሆኑ እንድ ቡድን የሆኑ ልጆች ስናጫውት ጥሩ ነገር ይሆናል። በትንሽ ጊዜ ውስጥ ይሆናል። ካሶተኒ ለምነን ነው የተጫወትነው። ማልያም ጠይቀን ነው። የትራንስፖርት ሰዎች አግዘውን ነው። ይህ የራሳችን ቡድን ነው። ይሄ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የምንፈልገውን እንድንመለከት የሚያደርገን ነው ፤ በትዕግሥት የተመለከቱንን ተመልካቾች እና ጎፈሬን እናመሰግናለን። በተገቢው ቦታ እና ትክክለኛው ተጫዋቾች ሲገኙ በክለብ ደረጃ ሆነ በሌላ በትልቅ ደረጃ ቢሆን ምንም ጥያቄ የለውም እርግጠኛ እንደሚሆን በእነዚህ ሁለት ጨዋታዎች ተማምነናል።”