አሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ከነገው ጨዋታ አስቀድሞ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል

ከነገው የኢትዮጵያ ወጣት ቡድን ጨዋታ አስቀድሞ አሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ በጁፒተር ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ የመጀመርያ ዙር የማጣርያ ጨዋታውን ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር ነገ በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ያደርጋል። ከነገው ጨዋታ አስቀድሞ ዛሬ በጁፒተር ሆቴል አሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

15 ደቂቃ በፈጀው እና ጥቂት የሚዲያ አካላት በተገኙበት በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ በመግቢያ ንግግራቸው ከነሐሴ 24 ጀምሮ በሊጉ ውድድሮች ብቃታቸውን በመመልከት ለ35 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዝግጅታቸውን በካፍ የልህቀት ማዕከል መጀመራቸውን አውስተው ከ35 ተጫዋቾች መካከል ወቅታዊ አቋማቸውን በመገምገም ሁለት የአቋም መለኪያ ጨዋታ በማድረግ አስር ተጫዋቾች በመቀነስ 25 ልጆችን በመያዝ ለጨዋታው ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረው። ጥሪ ከተደረገላቸው ተጫዋቾች መካከል ክለቦች በጊዜ ተጫዋቾቻቸውን ባለመልቀቃቸው ምክንያት በዝግጅታቸው ላይ ተፅኖ መፍጠሩን አንስተዋል። ይሄም ቢሆን ለነገው ጨዋታ በበቂ ሁኔታ በታክቲኩም በሥነ ልቦናውም ዝግጅት በማድረግ ጨዋታውን አንደሚያሸንፍ ተናግረዋል።

በማስከተል አሰልጣኝ አጥናፉ በቦታው በሚገኙ የመገናኛ ብዙኀን ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ተከታዮን ምላሽ ሰጥተዋል።


ከሊጉ ሥልጠና ስለመራቃቸው…

“በአጋጣሚ ይህ ለኔ ጥሩ ዕድል ነው። በነፃነት ለመስራት ምቾት ፈጥሮልኛል። በፕሪሚየር ሊጉ በማሰልጠን ላይ ባልገኝም አብዛኛዎቹ በዚህ ብሔራዊ ቡድን ያሉ ወጣቶች በእኔ ያለፉ ናቸው። ብቃታቸውን ያለበትን ደረጃ በየውድድሮቹ በመገኘት ስከታተል ቆይቻለው። ልጆቹ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች በእኔ ስር ስለነበሩ ስከታተላቸው ቆይቻለው። ትልቁም ግቤ እነዚህ ልጆች የነገው ዋናው ብሔራዊ ቡድን ተተኪ እንደመሆናቸው መጠን ምንም ጥርጥር አልነበረኝም እነዚህን ልጆች ስንይዝ። ከዚህ ውጭ ከዋናው ሊግ ውጭ በተለያዩ ከ20 ዓመት በታች ውድድሮች በአሰላ ፣ በባቱ እና በጎንደር ተጫዋቾችን በመመልመል ጥረት አድርገን ዕድል ያላገኙ ልጆች በዚህ ቡድን አካተናል። ስለዚህ ከሊጉ ያን ያህል መራቅ ሳይሆን ለኔ የዕረፍት ጊዜው በነፃነት እንድሰራ ዕድሉን ፈጥሮልኛል።”

ስለተቀነሱ ተጫዋቾች መመዘኛ…

“አንዱ ከአንዱ የሚሻልበትን ብቃት የምንለይበት የተሻለ ዘመን ላይ እንገኛለን። ማንም ሰው ሜዳ ላይ መጥቶ ከእከሌ እከሌ ይሻላል በሚል መምረጥ የሚቻልበት ጊዜ ነው። ወቅታዊ አቋም ለአንድ ተጫዋች ወሳኝ ነው። 35 ልጆችን መልምለናል በሂደት ግን እነዚህን ሁሉ በቦታቸው ዕኩል ብቃት አላቸው ማለት አይደለም። የተለያየ የብቃት ደረጃ ያላቸው ናቸው። አንዱ ትንሽ የገጠመን ችግር እንደሚታወቀው ክለቦች የቅድመ ውድድር ዝግጅት ላይ ናቸው። የዝግጅት ጊዜ አጀማመራቸውም የተራራቀ ነው። በፌዴሬሽኑ ጥሪ እነዚህ ልጆች ሲመጡ ሂደት ባለው መልኩ ነው የመጡት። እኛም የእነዚህን ልጆች ወደ አንድ ለማምጣት ለአምስት ቀን በቀን ሁለቴ ስናሰራ ቆይተን የሚጎላቸውን ነገሮች ሙሉ ለማድረግ እና ወደ አንድ ለማምጣት እንደ ባለሙያ ሞክረናል። ነገር ግን ለዚህ ውድድር ብቁ ያልሆኑ ልጆችን ለመቀነስ ተገደናል። በአንፃሩ ዘግይተው የመጡትንም ለነገ ብሔራዊ ቡድን ተተኪ የሚሆኑ ልጆች፣ እኛም የምናቃቸው ቢመጡ ደግሞ ውጤት የሚቀይሩ ተጫዋቾች በመሆኑ ለመጠቀም ተገደናል።”

ስለነገው ጨዋታ ዝግጅት…

“በዘመናዊ እግርኳስ ወጣቶች በኃላፊነት ስሜት መጫወት እንደሚገባቸው እና ከእነርሱ ብዙ ነገር እንደሚጠበቅባቸው ገልፀንላቸዋል። የነገውን የተሻለ ብሔራዊ ቡድን ለማየት ዛሬ መጠቀም እንዳለባቸው በሥነ ልቦና ባለሙያ ሥልጠና ሰጥተናል። በሜዳ ላይም ልምምድ በራሳቸው ብቃት ያላቸውን ነገር እንዲያደርጉ ቴክኒካል ድጋፍ አድርገናል። በአጠቃላይ የምንችለውን ሁሉ ለነገው ጨዋታ ስንዘጋጅ ቆይተናል። በዚህም ውጤታማ እንሆናለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን። በፌዴሬሽኑም በኩል አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ ተደርጎልናል።”