ብርቱካናማዎቹ አጥቂ ለማስፈረም ከጫፍ ደርሰዋል

በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው አጥቂ ድሬዳዋ ከተማን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሷል።

ባሳለፍነው የውድድር ዓመት 13ኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ድሬዳዋ ከተማ ክረምት ላይ አሠልጣኝ ዮርዳኖስ አባይን ከሾመ በኋላ በርከት ያሉ ተጫዋቾችን በማስፈረም ቡድኑን እያጠናከረ እንደሚገኝ ይታወቃል። በሀረማያ ዩኒቨርስቲ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሲሰራ የሰነበተው ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ባህር ዳር ከተማ ከተጓዘ በኋላ በአሁኑ ሰዓት በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።

የፊት መስመር ችግር ያለበት የሚመስለው ክለቡም በዚሁ ውድድር ላይ እየተሳተፈ ከሚገኘው ሞደርን ጋዳፊ አጥቂ ለማስፈረም እየተነጋገረ እንደሆነና በድርድሩም አዎንታዊ ውጤቶች እየተገኙ እንደሆነ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ የምድብ 2 ጨዋታዎች ሦስት ግቦችን ያስቆጠረው ሙሲጊ ቻርልስ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በኤክስፕረስ ካሳለፈ በኋላ በሞደርን ጋዳፊን የእግርኳስ ህይወቱን ለመቀጠል ፊርማውን ቢያኖርም የድሬዳዋን ጥያቄ ተከትሎ ከክለቡ ጋር በመነጋገር ተለያይቶ ብርቱካናማዎቹን ለመቀላቀል ወስኗል። ለዩጋንዳ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የተጫወተው ቻርልስ ከክለቦቹ ጋር የሚያደርገው ንግግር ተገባዶ የወረቀት ጉዳዮች መስመር ከያዙ በኋላ ዝውውሩ ይፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።

ያጋሩ