በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ የፍጻሜ ተፋላሚዎች ተለይተዋል

ከቀትር በኋላ በተደረጉ ሁለት የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ቡል እና ወልቂጤ ከተማ የፍፃሜ ተፋላሚ መሆናቸው ታውቋል።

7፡00 ላይ የቡል እና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ በግብ ሙከራ ያልታጀበ እና መጠነኛ ፉክክር ብቻ የታየበት ነበር። በተደጋጋሚ ሲከሰቱ በነበሩ አካላዊ ንክኪዎች አሰልች የነበረው የጨዋታው ጅማሮ 12ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዳዋ ከተማው ቢንያም ጌታቸው ከግራ መስመር ያደረገው ኃይል ያልነበረው እና ግብ ጠባቂው በቀላሉ የያዘው የግብ ሙከራ የጨዋታው የመጀመሪያው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር። ቡሎች የመጀመሪያውን የተሻለ ሙከራ ያደረጉት 24ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ንዱግዋ ከሪም ከሳጥን ውጪ ከቀኝ መስመር ወደግብ የሞከረው ኳስ የግቡን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶበታል።

ከውሀ ዕረፍት መልስ የተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉት ቡሎች ከቀኝ መስመር ተጫዋቹ ኦኔክ ሂላሪ በሚነሱ ኳሶች የተለያዩ የግብ ዕድሎች መፍጠር ችለዋል። በተለይም 29ኛው ደቂቃ ላይ ኦኔክ ሂላሪ ከቀኝ መስመር ያሻማውና ኦኬች ሲሞን በግንባሩ ገጭቶት የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ሙከራ በቡሎች በኩል አስቆጪ አጋጣሚ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ተጭነው የተጫወቱት ድሬዳዋ ከተማዎች 43ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር የነበረው አብዱለጢፍ መሀመድ ከአድናን መቲ የተቀበለውን ኳስ ሲያሻማ ታሆሜራ ቤኖን ኳስ በእጁ በመንካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ዮሴፍ ዮሐንስ አስቆጥሮ የመጀመሪያውን አጋማሽ 1-0 በሆነ ውጤት መርተው ሊወጡ ችለዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው መቅረብ የቻሉት ቡሎች በመጀመሪያዎቹ ሁለት ደቂቃዎች የአቻነት ግብ ማስቆጠር ችለዋል። ግቧንም በቀኝ መስመር የተሰጠውን የማዕዘን ምት ኦኔክ ሂላሪ ሲያሻማ ንዱግዋ ከሪም በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል። ድሬዳዋ ከተማዎች የኋላ ክፍላቸውን ቢያጠናክሩም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ታይቷል ፤ ጋዲሳ መብራቴ የተሻሉ ሁለት የግብ ሙከራዎች ቢያደርግም ዒላማዎችን መጠበቅ አልቻለም።

77ኛው ደቃቃ ላይ ኦኔክ ሂላሪ ከቀኝ መስመር በተመሳሳይ ሁኔታ ያሻማውን ኳስ ኦኬች ሲሞን በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ቡሎችን መሪ ማድረግ ችሏል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ኦኔክ ሂላሪ ከረጅም ርቀት ድንቅ የግብ ማግባት ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው ሊያስወጣበት ችሏል። ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር የግብ ዕድል ለመፍጠር የተቸገሩት ድሬዳዋ ከተማዎች ከዕረፍት መልስ የተሻለውን ሙከራ ያደረጉት 83ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ዮሴፍ ዮሐንስ ከረጅም ርቀት ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው አድኖበታል። ቡሎችም ጨዋታውን በማረጋጋት የሚፈልጉትን ውጤት ይዘው መውጣት ችለዋል። ውጤቱን ተከትሎም ቡል ኤፍ ሲ ከነገ በስቲያ ቅዳሜ ለሚደረገው የፍጻሜ ጨዋታ ማለፉን አረጋግጧል።

በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የቡሉ ካሊዮዋ ሬጋን የጨዋታው ኮከብ በመሆን ተመርጧል።

እጅግ ሞቃታማ በሆነ የአየር ሁኔታ የተደረገው የሞደርን ጋዳፊ እና የወልቂጤ ከተማ ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ የተቀዛቀዘ ፉክክር የታየበት እና አንድ ብቻ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ የተደረገበት ነበር። የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ 9ኛው ደቂቃ ላይ በሞደርኖች ሲደረግ በተጠቀሰው ደቂቃም ካኮዛ ማሃድ አመቻችቶ ባቀበለው ኳስ ሙሲጌ ቻርልስ ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ ቢፈጥርም የወልቂጤ ከተማ ተከላካዮች ተደርበው ሊያስወጡበት ችለዋል። በኳስ ቁጥጥሩ በኩል ወልቂጤዎች የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ የቻሉት ግን ሞደርኖች ነበሩ።

15ኛው ደቂቃ ላይ ካሶዚ ኒኮላስ ከረጅም ርቀት ወደ ግብ የሞከረው ኳስ የግራውን ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። በወልቂጤ ከተማዎች በኩል ከግራ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት ተመስገን በጅሮንድ ወደግብ ሞክሮት ግብጠባቂው የያዘው ኳስ በመጀመሪያው አጋማሽ ብቸኛው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር። ተጫዋቾች የሜዳው የመሀል ክፍል ላይ ተጠጋግተው ሲጫወቱ የግብ ዕድልም ለመፍጠር ይበልጥ እየተቸገሩ ሄደዋል። 39ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አንዋር ዱላ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ በግቡ የግራ አንግል ጥግ የነበረው ብርሃኑ ቦጋለ አግኝቶት ወደግብ ቢሞክርም የላይኛውን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶበታል። በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ የአየር ሁኔታው ለጨዋታ ምቹ እየሆነ ሲሄድ ጨዋታውም ለተመልካች አዝናኝ ነበር። በተለይም በወልቂጤ ከተማዎች በኩል ብዙ የተሳኩ የኳስ ቅብብሎች እና የተሻሉ የግብ ዕድሎችን መመልከት ችለናል። 60ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን በጅሮንድ ከግቡ በግራ በኩል ከሳጥኑ ጫፍ አስገራሚ ግብ አስቆጥሮ ወልቂጤን መሪ ሲያደርግ የተጫዋቾቹን የጨዋታ መንፈስ የቀየረ አጋጣሚም ነበር።

66ኛው ደቂቃ ላይ ወልቂጤ ከተማዎች በጥሩ ቅብብል የወሰዱትና ብዙዓየሁ ሠይፈ ከአሥራት መገርሳ ተቀብሎ ከሳጥን ውጪ ወደግብ በግሩም ሁኔታ ሞክሮት የግራውን ቋሚ ገጭቶ የተመለሰው ኳስ እጅግ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ወደፊት ተጭነው ለመጫወት የሞከሩት ሞደርኖች 78ኛው ደቂቃ ላይ አቻ የሚሆኑበት ዕድል አግኝተው ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም ሙሊሚ ፍራንክ ወደግብ የሞከረውን ኳስ የወልቂጤው ተከላካይ ዋሃብ አዳምስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ሙሲጌ ቻርልስ ሲመታ ዒላማውን ባለመጠበቁ ትልቅ የግብ ዕድል አባክኖ ሞደርኖችን አስቆጭቷል።

ጨዋታው 88ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የሞደርኑ ካሶዚ ኒኮላስ ለዳኛ ያልተገባ ባሕርይ በማሳየቱ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ የባከኑ ደቂቃዎች ሲቀሩ አፈወርቅ ኃይሉ ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው አድኖበታል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት አፈወርቅ ኃይሉ ያሻገረውን ኳስ ፋሲል አበባዓየሁ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ቺፕ አድርጎ ግሩም ሙከራ ቢያደርግም ኪዬምባ ኢብራሂም በፍጥነት ደርሶ መልሷታል። ይሄም የጨዋታው የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በወልቂጤ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ወልቂጤ ከተማ ከቡል ኤፍ ሲ ጋር በዕለተ ቅዳሜ የፋጻሜ ጨዋታውን ያደርጋል።

በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው አሥራት መገርሣ የጨዋታው ኮከብ በመሆን ተመርጧል።

ያጋሩ