የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከኮንጎ አቻው ያለግብ ተለያይቷል


በአበበ ቢቂላ ስታዲየም የተደረገው የኢትዮጵያ እና የኮንጎ ዲ.ሪፐብሊክ የ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ቀዝቀዝ ብሎ በጀመረው ጨዋታ ላይ የዲሞክራቲክ ኮንጎ የኋላ የመከላከል አቅም የተደራጀ በመሆኑ የኢትዮጵያ ቤሔራዊ ቡድን ሰብሮ መግባት ተቸግሮ ተስተውሏል። በሙከራ ደረጃ በ7ኛው ደቂቃ መስፍን ታፈሰ ከእጅ ውርወራ የተገኘ ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። ከዚህ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች ወደ ግብ መድረስ የቻሉት ከበርካታ ደቂቃዎች በኋላ ነበር። 32ኛው ደቂቃ ላይ የዲሞክራቲክ ኮንጎ ምፓንዙ ዓሊ ከሳጥን ውጪ እክርሮ የመታው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ሲቀር በድጋሚ 34ኛው ደቂቃ ላይ ራሱ ዔሊ በግራ ሳጥን ጠርዝ ግብ አክርሮ የመታው ኳስም ወደ ውጪ ወጥቷል።

በኢትዮጵያ በኩል 35ኛው ደቂቃ ላይ አለልኝ ከርቀት ጥሩ ሙከራ ሲያደርግ ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ ከመሀል እንዳልካቸው መስፍን ወደ ግራ ጠርዝ ለመስፍን ታፈሰ ያሸገረውን ኳስ መስፍን ከብሩክ ጋር በመቀባበል የሞከረው ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቷል።

የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የተሻለ በነበረበት ሁለተኛ አጋማሽ በተደጋጋሚ ሙከራዎችን ቢያገኙም መጠቀም አልቻሉም። በሙከራ ደረጃ ቀዳሚ የነበሩት ዲሞክራቲክ ኮንጎዎች 56ኛው በግራ መስመር ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የተስተዋለው ምፓንዙ ዔሊ አክርሮ ሞክሮ ሲስት ከሦስት ደቂቃ በኋላ ደግሞ በኢትዮጵያዊያኑ በኩል ከወንድማገኝ የተሻገረለትን ኳስ መስፍን ታፈሰ ሰጥን ውስጥ አክርሮ መትቶ በተከላካዮች ተጨርፎ ወጥቶበታል። በቀጣይ ደቂቃዎችም አለልኝ ከቅጣት ምት ሞክሮ በግቡ ቋሚ የተመለሰበት እንዲሁም ተከላካዮች የአብዲሳን ሙከራ ያዳኑባቸው አጋጣሚዎችም በባለሜዳዎቹ በኩል ተጠቃሽ ነበሩ።

በቀሪ ደቂቃዎችም የተሻለ ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ መድረስ የቻሉት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች ቢሆኑም ከዕረፍት መልስም ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ከማድረግ ባለፈ ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። ይልቁኑም ጨዋታው ወደ ማብቂያው ሲደርስ ኮንጎዎች 86ኛው ደቂቃ ላይ በምፓንዙ ኤሊ እንዲሁም 88ኛው ደቂቃ ላይ በኪንኬላ ጆናታን አማካይነት አደገኛ ሙከራዎች ማድረግ ችለው ነበር። ጨዋታው በኢትዮጵያ በኩል አብዲሳ ጀማል ባደረገው ሙከራ መቋጫውን አግኝቷል።

ሁለቱ ሀገራት የማጣሪያውን የመልስ ጨዋታ በመጪው ማክሰኞ ኮንጎ ላይ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ያጋሩ