የአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ረዳቶች ውላቸው ተራዘመ

የዋልያዎቹ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ረዳት አሰልጣኝ በመሆን ያለፉትን ሁለት ዓመታት ያገለገሉት ሦስት አሰልጣኞች በዛሬው ዕለት ውላቸው በይፋ ተራዝሞላቸዋል፡፡

የወቅቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ላለፉት ሁለት ዓመታት የሀገራችንን ብሔራዊ ቡድን በኃላፊነት መንበር እየመሩ ቡድኑን ለአፍሪካ ዋንጫ ያበቁ ሲሆን በቅርቡም በሀገር ውስጥ ተጫዋቾች ብቻ ለሚከወነው ቻን ላይ ኢትዮጵያ ተሳታፊ መሆን እንድትችል ማድረግ መቻላቸው ይታወሳል፡፡ ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር የነበራቸው ውል በቅርቡ መጠናቀቁን ተከትሎ ከሰሞኑ የሁለት ዓመት ተጨማሪ ኮንትራት ከተሻሻለ የደመወዝ ክፍያ ጋር የተራዘመላቸው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በዛሬው ዕለት ደግሞ በተመሳሳይ ከአሰልጣኙ ጋር ያለፉትን ሁለት ዓመታት አብረው መዝለቅ የቻሉ ሦስት ረዳት አሰልጣኞች ውላቸው ስለመራዘሙ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችሁ መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህም መሠረት በረዳት አሰልጣኝነት ከአሰልጣኙ ጋር አብረው ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኝ አንዋር ያሲን እና አስራት አባተ እንዲሁም ደግሞ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ የሆነው ደሳለኝ ወልደጊዮርጊስ ልክ እንደ ውበቱ አባተ ሁሉ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የደመወዝ ማሻሻያ ተደርጎላቸው ውላቸው ተራዝሞላቸዋል፡፡

ያጋሩ