ክርስቲያን ጎርኩፍ እና አልጄሪያ ተለያይተዋል 

ፈረንሳዊው አሰልጣኝ ክርስቲያን ጎርኩፍ ራሳቸውን ከአልጄሪያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነታቸው ዛሬ በገዛ ፍቃዳቸው አንስተዋል፡፡

የ60 ዓመቱ አሰልጣኝ ከአልጄሪያ ሚዲያዎች እንዲለቁ ከፍተኛጫና የደረሰባቸው ሲሆን ዛሬ ከአልጄሪያ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት መሃመድ ራውራው ጋር ባደረጉት ውይይት የአልጄሪያ ብሄራዊ ብድንን ለቀዋል፡፡ ውይይቱም ጥቂት ደቂቃዎችን ብቻ የፈጀ ነበር፡፡

ባሳለፍነው ማክሰኞ አዲስ አበባ ላይ አልጄሪያ ከኢትዮጵያ 3-3 ስትለያይ ብሄራዊ ቡድኑን የመሩት ጎርከፍ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ በአሰልጣኝነታቸው መቀጠል እንደሚፈልጉ የገለፁ ቢሆንም ከቀናት ልዩነት በኃላ ስራቸውን ሊለቁ ችለዋል፡፡

የሚመርጡት የ4-4-2 አሰላለፍ እና በአልጄሪያ ሊግ ሞቢሊስ የሚጫወቱ ተጫዋቾችን ለብሄራዊ ቡድን አለመምረጣቸው በከፍተኛ ሁኔታ ሲያስወቅሳቸው ነበር፡፡ አብዛኛውን ግዜያቸውን በፈረንሳይ ያሳልፉ የነበሩት ጎርኩፍ የአልጄሪያ የውስጥ ሊግ የመከታተል ዕድል እንዳልነበራቸው ዘገባዎች ጠቁመዋል፡፡

የአልጄሪያ የውስጥ ሊግ ላይ የሚጫወቱ ተጫዋቾች በአፍሪካ መድረክ ከ2014 ጀምሮ ስኬታማ ጉዞ ላይ ቢገኙም ጎርኩፍ አሁንም አውሮፓ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ላይ ትኩረት አድርገዋል፡፡ ከፌድሬሽኑ ፕሬዝደንት ራውራው ጋርም የነበራቸው ቅራኔ ጎርኩፍ ወደ መውጫው በር እንዲመለከቱ ሳያደርጋቸው እንዳልቀረ ተገልጿል፡፡

በ2014 የብራዚል ዓለም ዋንጫ መጠናቀቅ በኃላ ቦሲኒዊውን ቫሊድ ሃሊልሆዚችን ተክተው ወደ ሰሜን አፍሪዊቷ ሃገር የመጡት ጎርከፍ አልጄሪያ በ2015 የአፍሪካ ዋንጫ ሩብ ፍጻሜ ሲያደርሱ ለ2017 የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ 10 አናት ላይ አልጄሪያ እንድትቀመጥ አድርገዋል፡፡ እንደ አልጄሪያ እግርኳስ ፌድሬሽን ገለፃ ከሆነ ፌድሬሽኑ ጎርኩፍ ላፈረሱት ውል ምንም ዓይነት ማካካሻ ክፍያ አይቀበልም፡፡

ፌድሬሽኑ ቀጣዩን የአልጄሪያ አሰልጣኝ ቪክቶሪያ ላይ ከሲሸልስ ጋር ከሚደረገው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በፊት ያሳውቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ካልተቻለም ነግሂዝ እና መንሱሪ በግዜዊነት የአሰልጣኝ መንበሩን ይቆናጠቱታል፡፡

በምድብ 10 ከኢትዮጵያ ጋር የተደለደሉት ሶስቱም ሃገራት አልጄሪያ፣ ሲሸልስ እና ሌሴቶ ማጣሪያው ከመጠናቀቁ በፊት አሰልጣኞቻቸውን ለውጠዋል፡፡ ሌሴቶ በህዳር ወር ሰፊፊ ማቴቴን በሞሰስ ሲያን እንዲሁም ሲሸልስ ብሩኖ ሳኢንዲኒን በራልፍ ጅያን ሊዊ ተክተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *