“ግብ ያለማስቆጠራችን አንዱ ደካማ ጎናችን ነው” አሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ

የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዲ.ሪ ኮንጎ ጋር ያለግብ ስለተጠናቀቀው ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል።

ስለጨዋታው እና ስለውጤቱ…

“ቡድኑ የምንችለውን ሁሉ አድርጓል። ተጋጣሚያችንም ጥሩ ነው ምክንያቱም ከሜዳ ውጪ ያለውን ውድድር በሙሉ ያለውን ዕድል ተጠቅመው እዚህ ዘግቶ ለመሄድ የመጣ ነው። በዚህ አደረጃጀት የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ተጭነው ለመጫወት ወይም የአየር ንብረታችንን ከፍታ ተጠቅመው በጣም ተጭነውን ለመጫወት ሞክረዋል ፤ ያንንም ተቋቁመን ተጫውተናል። በዚህ አጋጣሚ የተለያዩ ዕድሎችን ፈጥሯል ጥሩ ሆኖ ለማቀናጀት ችሏል። በእንቅስቃሴው መሠረት እንግዲህ ሁለተኛው አጋማሽ ላይ ባሉብን ክፍተቶች ሁሉ ተጫዋቾቹን በበለጠ ዕይታ ኖሯቸው ወደፊት እንዲጫወቱ በማድረጋችን ብዙ ዕድሎችን ፈጥረናል ፤ ግን ግብ ማስቆጠር አልቻልንም ፤ የሚፈጠር ነው። በተሻለ እንቅስቃሴ በሁለተኛውን አጋማሽ ቡድኑን እንቅስቃሴ ውስጥ በመክተት ከሜዳ ውጪ ዘግቶ የመጫወት ዕድላቸውን  በማስከፈት የተለያዩ ሙከራዎችን አድርገናል። እንዳያችሁት ግብ ያለማስቆጠራችን አንዱ ደካማ ጎናችን ነው። ከዚህ አንጻር ለሚቀጥለው ባሉን ድክመቶች ዙሪያ ሰርተን የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ጥሩ መልስ ሆኖናል እንቅስቃሴው። ተጫዋቾች ነገ ለዋናው ብሔራዊ ቡድን የሚሆኑ ተስፋ የሚጣልባቸው ናቸው ፤ ከዚህ አንጻር ተወዳዳሪ ቡድን ነው።”

ስለተጫዋቾች አጠቃቀም…

“ትልቁ ነገር ቡድኑ አስቦ ሊመጣ የሚችለው ከሜዳ ውጪ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመክተት ኳስ ይዘው የሚጫወቱ ልጆችን በቦታው ላይ ተጠቅመናል። ይሄ ለምንድነው የነሱን የጫና መጠን ለመቀነስ ኳስ ችለው የሚጫወቱ ልጆች እዛ ቦታ ላይ አስፈላጊ ናቸው። ያም ሆኖ ተጠቅመናል። በሁለተኛው ባደረግነው እንቅስቃሴ ለምሳሌ ከኋላ ያሉትን ይበልጥ ዕድሉን ለመጠቀም ፤ ጫና ፈጥረን መጫወት ስላለብን በሦስት ተከላካይ አድርገን የበለጠ ተጫዋቾች ከኛ ሜዳ ወጥተው የግብ ዕድል እንዲፈጥሩ የመጨረሻ አሥራአምስት ደቂቃዎች ላይ ተጠቅመናል። ይሄን ማድረግ ስላለብን ነው ምክንያቱም በማጥቃት ሂደት ውስጥ የሚፈጠሩ ዕድሎችን ለመጠቀም በጥሩ መልኩ እንቅስቃሴውን ገፍተውታል። ይሄም እንደታየው ተጫዋቾቻንም ወደፊት ሄዶ የመጫወት ዕድሉን ሰፊ አድርገውታል። የተፈጠሩ ዕድሎች ደግሞ ሜዳ ላይ የታዩ ናቸው። እንቅስቃሴው የበለጠ ጫና ፈጥረን ለመጫወት ቁጥሩን ኳሱን ተቆጣጥረው በሚጫወቱ ተጫዋቾች እንዲካሄድ ይሄንን አድርጌያለሁ።”

በመጨረሻ ሰዓት ስለተቀነሱ ተጫዋቾች…

“በቡድኑ የመጀመሪያውን ሥራ የሰራነው በነዚህ ተጫዋቾች ነው። ይሄ የሆነው እንግዲህ በፊፋ ወይም በካፍ ለኦሎምፒክ ቡድኑ የመጨረሻ ላይ ፈረንሳይ ላይ ለሚዘጋጀው ዕድሜያቸው ከአንድ ዓመት በኋላ ውድድሩ ሲካሄድ ከ 23 ዓመት በታች መሆን አለባቸው። በኦሎምፒክ አካሄድ ከ23 ዓመት በታች ብለውት ነው። በዛው መልክ ሌሊት ስድስት ሰዓት አካባቢ በኢሜይል የልጆቹ ተገቢነት በካፍ ስለተቀነሰ ይሄ ከአቅማችን በላይ ነው ምንም ማድረግ አንችልም። ይሁንና ያሉት ተጫዋቾች እነሱን መተካት የሚችሉ ናቸው። የመጀመሪያ ዕቅድ ሲኖርህ የሚቀጥለውን ዕቅድህን ደግሞ ታያለህ ያን ያህል ብዙም የጎላም ባይሆን የተወሰነ ተፅዕኖ ቢፈጥርም ተጫዋቾቼ ይሄንን ተጠቅመው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አድርገዋል።”

የአየር ሁኔታው ተጋጣሚ ላይ ስለነበረው ተፅዕኖ…

“በዚህ ዘመን የአየር ሁኔታን ሰበብ የምናደርግበት ጊዜ አልፏል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምናያቸው የአየር ሁኔታዎች ሁሉ ምክንያት አይሆኑም። ጥሩ ዝግጅት አድርገው ነው የሚመጡት እና ያን  እንደልዩነት የሚጠቀሙበት ጊዜ አልፏል። ምክንያት ለዚህ ዝግጁ ሆነው ነው የሚመጡት ፤ ቡድናቸው ጠንካራ ነው። በተሻለ ታክቲክ የነሱን ቡድን ሰብረን ጥሩ እንቅስቃሴ አድርገናል። በርግጥ እኛ ጋር የሚጎሉ አንዳንድ እንደ ስህተት ያየናቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ። እነዚህ ተጫዋቾች ያላቸው የቡድን ልምድ ያን ያህል ነው። ከ 20 ዓመት በታች ያመጣናቸው ለምሳሌ ከአርባምንጭ ያመጣነው ቡጠቃ ለነገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተስፋ የሚሆን ነው። ልምዱን እያዳበሩ ቢሄዱ እነዚሁ ሁሉ ለነገ ብሔራዊ ቡድን ተስፋ ሰጪ ናቸው። የልምድ ዕጥረቱ በተወሰነ ደረጃ ጫና አሳድሯል።”

ስለ መሐመድኑር ቅያሪ…

“በቦታው ለወደፊት ተስፋ የምንጥልበት አንዱ ተጫዋች መሐመድኑር ነው። ጉልበቱ ጋ ያለው ግጭት ገና አለየለትም ፤ ለሚቀጥለው ጨዋታ እንዲደርስ ተስፋ እናደርጋለን። የሕክምና ዶክተራችን አይቶ የሚነግረን ይሆናል።”

ስለአለልኝ ብቃት…

“የመከላከል አደረጃጀታችን ሁልጊዜ ጎሎቻችንን እያዩ እንደ ኮንጎ ፈጣን የሆነ ቡድን የምዕራብ አፍሪካ ኳስ የታወቀ ነው ኳስ በረጅሙ መትቶ ያን ተከትሎ ማጥቃት ይፈልጋሉ። የቅጣት ምት እና የማዕዘን ምቶችን ለማስቆጠርም የግድ ከተከላካያችን ፊት ቆሞ ያንን እየሸፈነ የሚጫወት ተጫዋች ያስፈልገናል። አለልኝን በዛ ቦታ መጠቀማችን ለኛ ትልቅ ጥቅም ሰጥቷል። ምክንያቱም ተክለ ሰውነቱ ፈቅዷል። የመሃል ተካላካዮቻችንን እንዳያጠቁ ሽፋን ሰጥቷል። የልምድ ማነስ ካልሆነ ወደፊት ተስፋ የሚጣልበት ተጫዋች ነው። ባለው ነገር ሞልቶ ትልቅ ተጫዋች ማድረግ የባለሙያው ተግባር ነው።”

ያጋሩ