ጌታቸው ገብረማርያም ስለ ሉቺያኖ ቫሳሎ

– “እንዴት ብዬ ላስረዳህ? ሉቻኖ የተለየ ፍጥረት ነው።”

– “. . . ሉቻኖ እጅግ ደስ አለው። ያልተነካ ፤ አዲስ ቱታ ሰጠኝ።”

– ” እሱ ከስፖርት ውጪ ምንም ውስጥ አልነበረም።”

– “ድሬዳዋ ውስጥ ማንኛውም የተቸገረ ሰው በእሱ ያልተረዳ ያለ አይመስለኝም።”

– “. . . ሌላ ሰው ቢሆን ጠጅ፣ ጠላ፣ አረቄ፣ ሥጋ ይጋብዝሃል። እርሱ የስፖርት ትጥቅ ነው የሚሰጥህ።”

– “ሉቻኖ – በቃ-ንጹህ የስፖርት ሰው ነበር።”


አቶ ጌታቸው ገብረማርያም ሥመ-ጥር የእግርኳስ ዳኛ ናቸው። ለግማሽ-ምዕት ዓመት ያህል የሚታወቁትም በእግርኳስ ዳኝነት፣ ኮሚሽነርነት እና ተያያዥ በሆኑ ኃላፊነቶች ነው። ከዚያ ቀደም ለአስራ ሁለት ዓመታት ያህል በተጫዋችነት አሳልፈዋል። ከ1952–56 የጥንት-የጠዋቱ ኦሜድላ አይበገሬ ተከላካይ ነበሩ። የወታደራዊ ቡድኖች ህልውና እንዲያከትም ከተወሰነ በኋላ ደግሞ ወደ ድሬዳዋ አምርተው ለጨርቃጨርቅ (ኮተን) ከ1959–64 መጫወት ችለዋል። አዲስ አበባ በነበሩበት ጊዜም ለአዲስ አበባ ምርጥ፤ በድሬዳዋ ሳሉ ደግሞ ለሐረርጌ ምርጥ ተጫውተዋል። ኢትዮጵያ ባስተናገደችውና ብቸኛ አህጉራዊ ድል በተጎናጸፈችበት ሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይም ለብሔራዊ ቡድን ጥሪ ተደርጎላቸው ለአንድ ወር ያህል በጀነራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ሲዘጋጁ ከርመው በመጨረሻ ተቀንሰዋል። የያኔው ወጣት ተከላካይ -ጌታቸው- የአንጋፎቹንና ልምደኞቹን ጎይቶም በርሔና ሌሎችንም ጠንካራ ተከላካዮች ቦታ የሚገዳደሩ አልነበሩምና ውሳኔውን በጸጋ ተቀብለዋል። “ በወቅቱ ከእኔ የሚበልጡ ተጫዋቾች የነበሩ በመሆኑ ያለምንም ቅሬታ ተቀንሻለሁ።” ሲሉ ያስታውሳሉ። በ1964 እግርኳስ መጫወት ሲያቆሙ ለቀጣዩ ግማሽ ክፍለ-ዘመን አያሌ የህይወት ውጣ-ውረዶች የሚያዩበትን የእግርኳስ ዳኝነት ሞያዬ ብለው ያዙ። የዳኝነቱን ሥራ የመረጡላቸው ክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ስለመሆናቸው ይናገራሉ። “ አንተ ዳኛ እንጂ አሰልጣኝ መሆን አትችልም።” የሚለውን የአቶ ይድነቃቸው ምክር ተቀብለው የተለያዩ የእግርኳስ ዳኝነት ስልጠናዎች በመውሰድ ወደ ዳኝነቱን ዓለም ተቀላቀሉ። ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩትና በአዛውንትነትም በጠንካራ አቋም ሥራ ላይ የሚገኙት አቶ ጌታቸው ገ/ማርያም የሉቻኖ ዘመን-ተጋሪ ተጫዋች ነበሩ። ኋለም በኮተን በእርሱ ሥር በተጫዋችነት አልፈዋል። ዛሬ አቶ ጌታቸው መስከረም 6 በሞት ስላጣነው ታላቁ ሉቻኖ ቫሳሎ የሚሉን ይኖራል።


በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ውስጥ በይበልጥ (ዋነኝነት) የምትነሳው በዳኝነቱ ቢሆንም ቀደም ሲል በተጫዋችነት አስር ዓመታት ያህል አሳልፈሃል። ከታላላቆቹ የአገሪቱ እግርኳስ ተጫዋቾች ጋርም ተጫውተሃል። ከሉቻኖ ጋር የነበረህ ትውውቅ ከየት ይጀምራል?

ሉቻኖን የማውቀው እንግዲህ – ካልተሳሳትኩ – የሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከተዘጋጀበት ጊዜ (1954) ጀምሮ ነው። ያኔ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተመረጡት ተጫዋቾች አንዱ ነበርኩ። በመጀመሪያው ምርጫ የተካተትነው ከሃምሳ እስከ ስድሳ የምንደርስ ተጫዋቾች የነበርን ይመስለኛል። ልምምድ የምናደርገው በጀነራል ዊንጌት ት/ቤት ነበር። ለብሔራዊ ቡድኑ ሃያ አምስት ወይም ሃያ ስድስት ተጫዋቾች ሲቀሩ (በመጨረሻው ምርጫ) እኔ ተቀነስኩ። ማረፊያችን እቴጌ ጣይቱ ሆቴል ነበር። በወቅቱ በመቀነሴ ምንም አይነት ቅሬታ አላደረብኝም፤ ምንም አልተሰማኝም። የሚበልጡኝ ነበሩ። ከኤርትራ- ጎይቶም በርሄ፣ ከአዲስ አበባ- አዋድ መሃመድን የመሳሰሉ ተጫዋቾች ነበሩ። አምኜበት ነው የተቀነስኩት። ቀድሞ መመረጤ (በቅድመ-ምርጫ ስብስቡ መካተቴ) በራሱ ለእኔ ትልቅ ነገር ነበር። ያኔ በስምና ዝና ብቻ ብሔራዊ ቡድን እንደማይገባ አምኛለሁ። የሚገርመኝና የሚደንቀኝ ፊት ለፊት ያገኘሁት ሰው የለም (ስለ መቀነሴ ሊነግረኝ የመጣ)። ከልምምድ መልስ ታጥቤ ወደ መኝታዬ ስሄድ ራስጌዬ ላይ በፖስታ ታሽጎ “250 ብር” እና ” ወደፊት ዕድልህን ሞክር!” የሚል ደስ የሚል መልዕክት የያዘ ደብዳቤ እንጂ ጋሽ ይድነቃቸው ወይም አቶ አዳሙ ወይም ሌሎች በቀጥታ መጥተው ” ተቀንሰሃል!” ያለኝ የለም። አካሄዳቸው ደስ የሚል ነበር። በስንብቴ ያሳዩት ክብር ደስ የሚያሰኝ ነው። ሞራሌ ተጠብቆ ከብሔራዊ ቡድኑ ተለየሁ። ሉቻኖን የማውቀው በዚያን ጊዜ ነው ማለት ነው። ያኔ ትውውቃችን በጥልቀት ሳይሆን በርቀት ነበር። እስከ 1956 ድረስ የወታደር ቡድኖች በውድድር ላይ ተሳታፊዎች ነበሩ። በ1956 ነበር ቡድኖቹ የተገለሉት። በዚያን ጊዜ ሉቻኖን የማየው እንደ ጓደኛ ወይም አሰልጣኝ ሳይሆን እንደ እግርኳስ ባላጋራ ነበር – አለ አይደል እንደ ተጋጣሚ ቡድን ተጫዋች። እኔ የኦሜድላ ተጫዋች ነበርኩ። በ1656 ” የወታደር በድኖች ይገለሉ!” ሲባል አብዛኞቹ ተጫዋቾች ወታደራዊ ቡድኖቹን ለቀቁ። እነ አዋድ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገቡ። እነ ኃይሉም እንደዚሁ ወደ ሌሎች ቡድኖች ሄዱ። አብዛኞቹ ወደ አንድነት፣ ሶዶ ምንጭ፣ መብራት ኃይል ገቡ። እኔም ወጣት ስለነበርኩ ከቤተሰብ መራቅ ባለመፈለጌ ኦሜድላን ከለቀቅኩ በኋላ የባለሃብት ቡድኖች በሆኑት አንድነት እና ሶዶ ምንጭ ተጫውቻለሁ። ሁለቱን ዓመታት እነዚህ ቡድኖች ጋር አሳለፍኩ።

በ1950ዎቹ መጨረሻ ሉቻኖ የጥጥ ማህበር ተጫዋች ነበር። ጋሽ አዳሙ ነበር የቡድኑ አሰልጣኝ። ሉቻኖ እዚህ ስለሚያውቀኝ ለጋሽ አዳሙ ጠቆመኝ። ገና ወደ ድሬዳዋ ከመሄዴ በፊት በ1958 በዘውድ በዓል ይመስለኛል ሉቻኖ ከቡድኑ (ጥጥ ማህበር) ጋር መጣ። ይዞኝ ለመሄድ ከባድ ትግል ገጠምን። “ሂድ ፥ አልሄድም!” ተከራከርን። ከዚያ ያው ወደ ድሬዳዋ ሄድኩ። ያኔ እርሱ አሰልጣኝ አልሆነም፤ ተጫዋች ነበር። ያን ያህልም የመወሰን መብት አልነበረውም። ድሬዳዋ ውስጥ ጣልያኖች ነበሩ። ጣልያውያኑ በእነርሱ አጠራር ” ዲዲ” የሚሉት ቡድን ነበራቸው። ለአንድ ዓመት እዚያ እንድጫወት አስቀጠረኝ። 700 ብር ደመወዝ ይከፈለኛል፤ ያን ጊዜ ሰባት ሺህ ብር ያህል ነው። ሉቻኖ ነበር ” ደመወዝህ ነው።” እያለ እያመጣ የሚሰጠኝ። እንዳልኩት ቡድኑ የጣልያኖች ነው። በድሬዳዋ ትልልቆቹ ቡድኖች ሲመንትና ኮተን ነበሩ። ለአንድ ዓመት ለዲዲ ስጫወት ሰውነቴን ጠብቄ፣ ለውድድር ስዘጋጅ ስለሚያዩኝ ሁለቱ ቡድኖች እኔን ለመውሰድ ሽሚያ ውስጥ ገቡ። እዚያ ሉቻኖን እንደ ጓደኛ፣ እንደ ወንድም፣ እንደ አባት ነበር የማየው። በሉቻኖ ምክንያት ጥጥ ማህበርን መረጥኩ። ሉቻኖ እኔ ጥጥ ማህበር ገብቼ ብዙም ሳልቆይ – አንድ ዓመትም የተጫወተ አይመስለኝም – ወደ ጣልያን አገር ለአሰልጣኝነት-ሥልጠና ሄደ። ስድስት ወራት ያህል ተምሮ መጣ። አሰልጣኛችን የነበረው አቶ አዳሙ ኮተንን ለቀቀ። ከዚያ ሉቻኖ አሰልጣኝ ሆነ። የመሃል ተከላካይነቱን ኃላፊነት ለእኔ ሰጠኝ። እኔም ጥሩ ሆንኩ፤ እንዳጋጣሚ በዚያው ጊዜ የኢትዮጵያ ሻምፒዮናን አሸነፍን። ከዚያ በኋላ እኔ ለእርሱ ያለኝ አክብሮት፣ እርሱም በእኔ ላይ የነበረው ዕምነት አደገ።

የሉቻኖ ውለታ በአንደበት ብቻ፣ በቃላትም ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ወጣትነት ከባድ ነው። ድሬዳዋ ሞቃት ነው። እኔ ራሴን በአግባቡ እጠብቃለሁ። ሉቻኖ እያንዳንዷን ነገር ያውቃል፤ በዚያ ላይ ጠባብ ከተማ ነች፤ ሰው ያውቅሃል፤ አላስፈላጊ ነገር አድርገህ የትም መደበቅ አትችልም። ለሉቻኖ ሚስጥር መሆን አትችልም። ሆኖም ሉቻኖ እኔን የትም መጥፎ ቦታ አያገኘኝም። የሉቻኖ ክትትል ቀላል አልነበረም። አመጋገባችንን ሳይቀር ይቆጣጠራል። ሌላው ቀርቶ ጥሬ ስጋ እንኳ መብላት የምንችለው ተደብቀን ነው። ለስፖርት ዕድገት ሲባል አመጋገባችን ላይ ጥንቃቄ እንድናደርግ ይፈልጋል። ከፍተኛ ሞራል ይሰጠናል፤ ያበረታታናል። ሉቻኖ ለስፖርት ያለው ፍቅር የሚገርም ነበር። ስፖርተኞችን ይወዳል። በዚያ ላይ ሰው አክባሪ ነው። እንኳን ከእርሱ ጋር የተጫወተውን ቀርቶ መንገድ ላይ የሚያገኘውን ሁሉ ቆሞ ሳያነጋግር፣ ሳያጫውት አያልፍም። ይስቃል፤ ይጫወታል። ሰው ይረዳል – ትጥቅም ይሁን ሌላ ይረዳል። ወጣቶችን ያሳድጋል። 1962 – ካሳሁንን፣ 1963 – አስራትን ከአዲስ አበባ በወጣትነት አምጥቷቸው የኮተን ተጫዋቾች አድርጓቸዋል። ያን ጊዜ እኔ በእድሜም ጉዳይ፣ በፍላጎትም ማነስ የተነሳ ጨዋታ ወደ ማቆሚያዬ ደረስኩ። ከዚያ በፊት ወደ ጣልያን የሄደ ጊዜ የቡድኑን ኃላፊነት ለእኔ ጥሎ ሄዶ ነበር። በእድሜ ገፋ ያልኩ ስለነበርኩ፣ ተጫዋቾቹም ስለሚቀበሉኝ፣ በኃላፊነት መደበኝ። ልጆቹም እግዜር ይስጣቸው! በጣም ያከብሩኝ ነበር። የቡድኑ አንጋፋም ነበርኩ። ኦሜድላ ስለተጫወትኩም እንደ ፖሊስ ነበር የሚቆጥሩኝ። የወታደር ዲሲፕሊን ነበረኝ። ለአንድ – አስራ አምስት ይሁን ሃያ ቀናት የኮተን አሰልጣኝ ሆኜ ጠበኩት። አዲስ አበባ የአሰልጣኝነትና የዳኝነት ኮርስ እንደሚሰጥ መረጃ መጣ። ሉቻኖም ” ሂድ የአሰልጣኝነት ኮርስ ወስደህ ና!” ብሎ ፈቀደልኝ። በባቡር አንደኛ ማዕረግ ይዤ አዲስ አበባ ገባሁ። እንደማስታውሰው ኮርሱ የሚሰጠው ኮሜርስ የንግድ ሥራ ት/ቤት ነበር። የአሰልጣኝነት ኮርሱ አንዱ ክፍል ውስጥ፣ የዳኝነት ኮርሱ ደግሞ ሌላ ክፍል ውስጥ ነበር የሚሰጠው። ኮርሱን የሚሰጡት ከፊፋ የተላኩ ሰዎች ነበሩ። ነፍሱን ይማረውና አቶ ይድነቃቸው በጣም ይወደኝ ነበር። ድሮ ድሮ ኦሜድላና ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲገናኙ ፍልሚያው ግድያ ነበር። የክለቦቹ አመራር አባላት ፍቅር አልነበራቸውም። ተጫዋቾቹ ግን ፍቅር ነበራቸው። ኮሎኔል አድማሱ፣ ጀነራል ጽጌ ዲቦ ራሳቸው ” በአምስት ሳንቲም ተማሪዎች ሰብስቦ የሚጫወት ቡድን እንዴት ያሸንፋችኋል?” እያሉ ይፎክሩብን ነበር። የሰራዊቱ አባላት ባላቸው የስፖርት ፍቅር እንጂ ሌላ ተንኮል ኖሮ አይደለም። በጊዮርጊስ ስንሸነፍ ” እንዴት?” ብለው ይቆጡናል። ከአቶ ይድነቃቸው ጋር ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እንተዋወቃለንና የአሰልጣኝነት ኮርሱን ልወስድ ስዘጋጅ እኔ ፣ መንግስቱ ወርቁ፣ ሌሎችም ነበርን። ቁጭ ብለን ሳሱ አቶ ይድነቃቸው መጡና ” አንተ ዳኝነትን እንጂ አሰልጣኝነትን አዕምሮህ አይቀበለውም።” ብለው ዳኝነቱን እንድመርጥ መሩኝ። ለእርሳቸው ትልቅ ክብር ነበረኝ። የአቶ ይድነቃቸውን ምርጫ ተቀብዬ ዳኝነቱን ተቀበልኩ። እስካሁንም ቢሆን ይገርመኛል ፥ ለህዝቡ ብጠቅምም – ባልጠቅምም በዚህ ሞያ ስሜቴን ተወጥቻለሁ፤ አገልግያለሁ። አንቀጹን ባላስታውሰውም ያኔ የፊፋ መስፈርት ዳኛ ለመሆን የሚፈልግ ቀደም ብሎ ኳስ የተጫወተ ቢሆን የሚል አንቀጽ ነበረው። ” ተጫዋች ከሆነ ደግሞ ም ተከላካይ ቢሆን ይመረጣል።” ይል ነበር። ሌሎቹ ለስላሶች ናቸው። ዳኝነት ራስህን ጠብቀህ የምትሰራው ሥራ ነው። ከዚህ አንጻር ሊሆን ይችላል አቶ ይድነቃቸው ዳኛ እንድሆን የወሰነው።


ሉቻኖ ለአሰልጣኝነት ልኮህ ዳኛ ሆነህ ስትመለስ ምን አለህ?

ሳቀ እሱ። በጣም ገረመው። ” ፖሊስ ስለ ሆንክ ነው!” ብሎ ቀለደብኝ። ” ጋሽ ይድነቃቸው ጎበዝ ነው። ጭንቅላት አለው። ፓሊስ ስለሆንክ ለዳኝነት የመረጠህ።” አለኝ። ኮሎኔል ገበየሁ ዱቤ፣ አየለ ተሰማ፣ ወታደሮች የነበሩ ናቸው። መቻል ነበሩ። ተስፋዬ ገብረየሱስ ብቻ እኮ ነው ሲቪል የነበረው። አብዛኞቹ ዳኞች ወታደሮች ነበሩ። እነ ሃይለማርያምም ሁሉ ወታደሮች ነበሩ። ሉቻኖም ውሳኔዬን ተቀበለ፤ አመነበት። ከሉቻኖ ወንድምም ጋር ቅርበቱ ነበረኝ። ኢታሎ ቫሳሎ። ኢታሎን ” አንቺ” ነበር የምንላት።

ሉቻኖ የት ሊሄድ እንደነበር ትዝ አይለኝም ግን እርሱም አዲስ አበባ መጥቶ ነበር። እኔ ደግሞ በአዲስ አበባ ስታዲየም ኢታሎ የመብራት ኃይል ተጫዋች ሆኖ የሚካሄደውን ጨዋታው እመራለሁ። ሉቻኖ ስታዲየም ቁጭ ብሎ ጨዋታውን ያያል። ኢታሎ በተጋጣሚ ግብ አካባቢ ኳስ በእጇ ይነካል። አውቆ ነበር የነካው። እኔም ማስጠንቀቂያ አውጥቼ ቢጫ ካርድ አሳያለዋለሁ። ኢታሎም ቀረብ ብሎ ” ቆይ ለሉቻኖ ነው የምነግረው!” ይለኛል። ” ሂድ! ያውልህ፤ ንገረው!” እለዋለሁ። ኢታሎ ወንድሙ ስታዲየም መሆኑን አላወቀም፤ አላየውም። በዚሁ ተሳሳቅን። መቼም የማልረሳው አጋጣሚ ነው። ከሉቻኖ ጋር ያለኝ ቅርበት በጣም ጥብቅ ነበር። ጠባም ፥ በጣም! ብዙ ነገር አልፏል። ትዝታዬን ቀሰቀስክብኝ።


ከዳኝነቱ ኮርስ በኋላ ወደ ድሬዳዋ ተመለስክ?

አዎ! ወዲያው ተመለስኩ። ከሶስት ወር በኋላ ዳኝነቱን ጀመርኩ። ያን ጊዜ ውድድሮች በሶስቱ ጠቅላይ ግዛቶች በመዘዋወር የሚካሄዱት። በኤርትራ፣ በሐረረጌ፣ በሸዋ። ከዚህ ቀደም በሌላ ሚዲያም ተነግሯል። አንድ ዳኛ ኢንተርናሽናል የዳኝነት ደረጃ ላይ ለመድረስ አንድ ዳኛ – አንደኛ ደረጃ፣ ሁለተኛ ደረጃ፣ ፌደራል ደረጃን ማለፍ ይጠበቅበታል። እነዚህን አራት እርከኖች አልፎ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለመባል ከአስር እስከ አስራ አምስት ዓመታት ይፈጅበታል። እኔ ግን ሶስት ዓመታት ብቻ ነው የበቃኝ። ማንም ይስማው። እኔ የሆነውን ነው የምናገረው።


ምስጢሩ ምንድን ነው?

ምስጢሩ ጠንክሮ መስራት ነው። መጀመሪያ ክረምት ላይ የታዳጊዎችን ጨዋታ መራሁ። እንደ አጋጣሚ አቶ ይድነቃቸው ነበር። ምን እንዳዘዛቸው አላውቅም ፥ ለሚቀጥለው አንደኛ ደረጃ ሆንኩ። ከዚያ ፌደራል ሆንኩ። ከዚያ ኢንተርናሽናል ደረጃ ደረስኩ።


በከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆነህ ጨዋታዎች ስትመራ የሉቻኖ አስተያየት እንዴት ያለ ነበር?

ወደ ኋላ ልመልስህና ብዙ ውዝግብ የፈጠረ ጨዋታ በኤርትራ መርቻለሁ። በሚያዝያ – 1966 – ሐማሴን ከመብራት ኃይል። ከዚያ ጨዋታ አንድ ሳምንት በፊት ሐማሴን ድሬዳዋ መጥቶ ከሲመንት መጫወት ነበረበት። ያኔ ሐሙስ-ሐሙስ ማታ “እገሌ” የተባለው ዳኛ ይኸን ጨዋታ ይመራል ተብሎ ቀድሞ ይነገራል። ለካ ድሬዳዋ ሲመጡ ቀጣዩን የእነርሱ (ከመብራት ጋር ያለባቸውን) ጨዋታ በአስመራ እኔ እንደምመራ ያውቁ ኖሯል። አመሃጽዮን የተባለ ተጫዋቻቸው ሉቻኖን ስለ እኔ ይጠይቀዋል። ሉቻኖ መኪና ነበረችው። ወዲያው እሷን አሰነስቶ ወደ እኔ ጋ ይመጣል። ” ጌቾ ከአንድም ሰው ጋር እንዳትገናኝ! አስመራዎች ይፈልጉሃል። ይመስለኛል በቀጣዩ ሳምንት የእነርሱን ጨዋታ እንድትመራ ተመድበሃል። ስለዚህ ማንንም እንዳትገናኝ።” አለኝ። እነርሱ እሁድ ተጫውተው ሰኞ ይሄዳሉ። ፈለጉኝ፤ አላገኙኝም። ሉቻኖ በብዙ መንገዶች ይጠብቀኝ ነበር። ቀድሞ – በተጫዋችነት እንዲሳካልኝ። ኋላ ላይ ደግሞ- በዳኝነት እንዲሳካልኝ። አደጋ እንዳይደርስብኝ ፤ ጥቃት እንዳይፈጸምብኝ። ቤቴ ድረስ መጥቶ – አንኳክቶ “ይፈልጉሃል። ከማንም ጋር እንዳትገናኝ!” ያለኝ። የሚገርመው አመሃጽዮን የሚባለው ተጫዋች እስከ ማክሰኞ ድረስ ቆይቶ ፈልጎ ሲያጣኝ ሄደ። እዚህ እንኳ ለማጫወት ስመጣ ” ይህን ሰው አትቅረበው፤ ይህን ሰው አታናግረው፤ እገሌን እንዳትገናኝ፤…..” እያለ ይመክረኛል፤ ያስጠነቅቀኛል። አጫውቼ ወደ ድሬዳዋ ስመለስም በደስታ ነው የሚቀበለኝ። (አቶ ጌታቸው – ይህን እየተናገሩ እምባቸው በአይናቸው ግጥም ብሎ እየሞላ ለጥቂት ደቂቃዎች ዝምታ ሰፈነ። የሉቻኖን ውለታ ለማውራት ብዙ ቢሹም ሀዘኑ የሚፈልጉትን እንዲናገሩ አላስቻላቸውም። ወደ ሌሎች ጥያቄዎች መሻገር የተሻለ ነበር።)


በድሬዳዋ የምትኖሩት አንድ አካባቢ ነበር?

እርሱ የሚኖረው ከዚራ በሚባለው ጣልያኖች በሚበዙበት የሃብታሞች ሰፈር ነበር። እኔ ደቻቱ ነበር የምኖረው።


ሉቻኖ የሚያሰለጥነውን አልያም የሚጫወትለትን ቡድን ጨዋታ መርተህ ታውቃለህ?

አዎ! አጋጥሞኛል።


ምን ገጠመህ? ምን ሆነ?

እንዴት ብዬ ላስረዳህ? ሉቻኖ የተለየ ፍጥረት ነው። ምን እንደምትልለት መግለጽ አትችልም። (የሉቻኖ ነገር አሁንም ሆዳቸውን እያባባ አስቸገራቸው – በቂ ምላሽ ሳላገኝ ወደ ሌላ ጥያቄ መሄድ ኖረብኝ።)


ሜዳ ላይ በውሳኔህ ያለመደሰት ስሜት አሳይቶህ፣ ተናግሮህ ወይም ተቃውሞህ ያውቃል?

ፍጹም! ፍጹም! ፍጹም! ሰላምታ ብቻ ነው የሚያቀርበው። ምንም አይነት መጥፎ ነገር አያሳይም። እንዴት ብዬ ልግለጸው?


ሉቻኖ የት የት ሲጫወት አንተ በዳኝነት መራህ?

ሉቻኖ ኮተን ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ድሬዳዋ (ዲዲ) በሚባሉ ቡድኖች ሲጫወት አጫውቼያለሁ። ዲዲ ከሲመንት ከባድ ጨዋታ ነበር። ያን ጨዋታ ስመራ ሰላምታ ሰጠኝ፤ ወደ ጨዋታ ሄደ። እንዳጋጣሚ እነ ሉቻኖ ያን ጨዋታ 1-0 አሸነፉ። ፔናሊቲ የለ። ምን የለ።


የቀድሞ ተጫዋቹ ሆነህ ከርመህ ከዓመታት በኋላ ደግሞ ዳኛ ስትሆን ያሳደረብህ ተጽዕኖ አልነበረም?

ሰዉም ያምንብሃል። ያኔ ሌብነት የለ፤ አሉባልታ የለ። ሞያህን ያከብራል። በሞያህ ነው ሁሉም። በዚያ ላይ ከተማዋ ጠባብ ነች። ማንም አይለቅህም። አንተም ተከብረህ መኖር ነው የምትፈልገው። ስትሳሳትም ያውቃሉ። ለምሳሌ፦ ሉቻኖ ዲዲ ሳለ እኔ የመራሁትንና ከሲመንት ጋር የተደረገውን ከባድ ጨዋታ አሸንፎ ሉቻኖ እኔን ለስምንት ወይም ለአስር ቀናት አላገኘኝም፤ አላነጋገረኝም። ሰሞኔላ የሚባል ባቡር ጣቢያው አጠገብ የሚገኝ ስፖርተኞች የሚሄዱበት ካፌ ነበር። ስፖርተኛውን በሙሉ የምታገኘው እዚያ ነው። ከአዲስ አበባም የመጣ፣ ከአስመራም የመጣ ሰሞኔላ ነው የሚገኘው። ጠጅ ቤት አይደለም፤ ጠላ ቤት አይደለም፤ ሻይ ቡና ብቻ የምትባባልበት የጣልያን ቤት ነው። ፊት ለፊቱ ፖስታ ቤት ነው። አካባቢው በቃ እንደ አውቶቢስ ተራ ያለ ነው። እዚያ ስንቀመጥ ከአንድም ስፖርተኛ የሉቻኖን ጉዳይ በሚመለከት ሐሜት ወይም አሉባልታ አልሰማሁም። እኔም ሞያዬን አላስደፍርም። እንኳን ሉቻኖ የእናቴም ልጅ ቢሆን በተጽዕኖ ሥር የመሆን ስሜትም የለኝም። አልዋሽም – አሁን ቢሆን- ምናልባት ልፈራ እችላለሁ። እኔ ስብዕናዬም አይፈቅድልኝም። አንዱ እንደውም ምን አለኝ – ” ትቆጣለህ! ለምንድን ነው?” አለኝ። የውስጥ ስሜቴ እንጂ ሌላ ነገር የለኝም። ሉቻኖም እግዜር ይስጠው! አልተጠጋኝም፤ ምንም አላለኝም። በእኔ ደስተኛ ነው።


በርካታ ዓመታት የሚሹ የዳኝነት እርከኖችን በቶሎ አልፈህ ኢንተርናሽናል ዳኛ ለመሆን ጥቂት ዓመታት ብቻ ሲበቁህ ሉቻኖ ምን ተሰማው?

ሉቻኖ እጅግ ደስ አለው። ያልተነካ ፤ አዲስ ቱታ ሰጠኝ። እንደ ሽልማትና ማበረታቻ ማለት ነው። አሁን ከባድ ምስጢር ልታወጣብኝ ነው። ንጉሱ ሁልጊዜ በነሐሴ ለፍልሰታ ወደ ድሬዳዋ እንደሚሄዱ ጋሽ ይድነቃቸውም ቅዱስ ጊዮርጊሶችም ድሬዳዋ ይመጣሉ። አንድ ቀን ሰሞኔላ ተቀምጠን ሳለ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ይሁን ደጋፊ አላወኩም – ቱታ ለብሷል። ሉቻኖም – “ስማ ጋሽ ይድነቃቸው! ይህን ቱታ እኮ አረከስከው።” አለው። ” ማንም እየለበሰው ነው። ለምን ማንም ይለብሰዋል?” ብሎ ጠየቀው። ከዚያ በኋላ ነው “ETHIOPIA” ወይም “adidas” የሚል ምልክት ያለበት እንጂ ሌላ እንዳይለብሱ የሚል ትዕዛዝ የወጣው። “ስፖርተኞች ከሌላው ሰው በምን ይለያሉ?” ነው የሱ ጥያቄ። “እባክህ ይህን ነገር ቀይር።” አለው። ሉቻኖ ፊት ለፊት ነው የሚናገረው። ደግሞ-ለኢትዮጵያ ስፖርት ያለው ፍቅር ይለያል።


በአብዮቱ ማግስት ከባድ ጊዜ አሳልፏል። በተለይ ሶስቱን ዓመታት (1968-1970)። በእርግጥ እነዚያ ዓመታት ለአብዛኞቻችሁ አስቸጋሪ ነበሩ። አንተም በብዙ ተፈትነሃል። ወደ መጨረሻ አካባቢ ትገናኙ ነበር? ሉቻኖስ በድብቅም ቢሆን የሚያራምደው የፖለቲካ አቋም ነበረው?

ሉቻኖ ከስፖርት ውጪ ምንም ውስጥ አልነበረም። ስለምንም የፖለቲካ ሁኔታ አይመለከተውም። ‘ጣልያናዊ ነኝ፤ ኤርትራዊ ነኝ፤…’ ብሎም አስቦም አያውቅም። ንጹህ ኢትዮጵያዊ ነበር። እንደማስታውሰው እናቱ ኢትዮጵያዊና ኤርትራዊ ናቸው። አባቱ ጣልያናዊ ነው። እናቱን በጣም ይወዳል። ጠይም ናቸው። ኢትዮጵያን ይወዳል። ከወደደህ – ወደደህ ነው። ከጠላህ ደግሞ – ጠላህ ነው። ኩርፊያ ሳይሆን ጭራሽ አያናግርህም። አንድም ሰው ሉቻኖን በክፉ ሲያነሳ ሰምቼም አይቼም አላውቅም። ሁሌም ቅድሚያ ለስፖርት ነው። ኮተን ጨዋታ ካቆመ በኋላ ከዚራ ውስጥ ጋራዥ ከፍቶ ነበር። ጎበዝ መካኒክ ነበር። በጣም ሃብታምም ነበር። የተለየ መካናም ነበረው። ባልሳሳት ከንጉሳውያን ቤተሰብ ልዑል ወሰንሰገድ ጓደኛው የነበር ይመስለኛል። ከእርሱ ጋር ነው የሚገናኘው ሁልጊዜ። ከማስታውሰው ልዑል በዕደማርያም የሲመንት፣ ልዑል ወሰንሰገድ ደግሞ የኮተን ደጋፊዎች ነበሩ። ወሰንሰገድ ጋር እንሄድ ነበር። የሐረርጌ ዱቅ ነው መሠለኝ የሚባል ነገር ነበር – የሱ ተወካይ ነበርና ወሰንሰገድ ጋር እንሄዳለን። ሉቻኖ ከንጉሳውያን ቤተሰቦች ጋር ብዙ ይቀራረብ ነበር። ሉቻኖ – ታችም-ታች ነው። ላይም-ላይ ነው። የትም ቦታ ታገኘዋለህ። እኔንጃ ! እኔ አሁን ቢራ ጠጥቻለሁ፤ ሉቻኖ ግን ቢራም ቀምሶ የሚያውቅ አይመስለኝም። ፍጹም! ጥሬ ሥጋም የሚያውቅ አይመስለኝም። ስለ ሉቻኖ እንዴት ላስረዳህ? ሰው እኮ ኖሮ ነው ማስረጃ የምታቀርብበት። እርሱ እኮ የለም። በዚያ ላይ በጣም ደግ ነው። ድሬዳዋ ውስጥ ማንኛውም የተቸገረ ሰው በእሱ ያልተረዳ ያለ አይመስለኝም። በሞራል፣ በገንዘብ፣ … በሌላም። ስፖርት ከጀመርክ ደግሞ አይለቅህም። በጣም ያበረታታሃል።


በዚያ ዘመን እንዲያው ደፈር ብለህ “የዚህ ፓርቲ አባል ሁን!” ብለህ ጠይቀኸው ታውቃለህ። አንተ የነበርክበትንም ሊሆን ይችላል።

በፍጹም! በፍጹም! እርሱ አይፈልግም።


እናንተንስ ” ከስፖርቱ ውጪ እንዴት እንደዚህ አይነቱ ጉዳይ ውስጥ ገባችሁ? ራሳችሁንስ ለምኝ ለአደጋ ታጋልጣላችሁ?” ብሏችሁ አያውቅም?

ሉቻኖ እንደዚህ አይነት ነገር ጨርሶ አይወድም። መሣሪያ ስትይዝ አይወድም። ሽጉጥ አይፈልግም። ሉቻኖ በቃ- ንጹህ የስፖርት ሰው ነው። ትርጉሙ ትንሽ ይከብዳል እንጂ ባላጋራ ሲባል-ጊዜያዊ ባላጋራ ወይም የስፖርት ተወዳዳሪ ነው። ባላጋራዎቹ እንኳን እኮ ያከብሩታል! በጣም! ጨዋታው እስኪያልቅ ይገላምጡታል፤ እርሱም እንደዚያው። ጨዋታው ካለቀ በኋላ ግን እንደዚያ ያለ ነገር አታይም።


ወጣት ተጫዋቾች በመመለመልም የተለየ አቅም እንደነበረው ይመሰከርለታል።

እንዴ ታዲያስ! ነፍሱን ይማርና ሱልጣን የሚባል ልጅ ነበር። ሎጋ ቁመና ነበረው። የአመጋገብ ሥርዓቱን አስተካክሎለት በአንዴ ሰውነቱ የስፖርተኛ ቅርጽ እንዲኖረው አደረገ። እንጀራ እንዳይበላ እንዲሁም ስፓጌቲ፣ …. ሌላም-ሌላም እንዲመገብ ብሎ የአመጋገብ ዕቅድ አወጣለት። ብዙም ሳይቆይ ተጫዋቹ ለብሔራዊ ቡድን ተመረጠ። ይህ ሁሉ የሆነው ሱልጣን ኮተን በገባ በአንድ ዓመቱ ነው እንግዲህ። የሚገርም ነበር። ታደለ የሚባል ግብ ጠባቂም ነበር። ዓባይነህ (የስምዖንና የዮርዳኖስ አባት) ሌት ተቀን እያሰራቸው አቋማቸውን ያስተካክልላቸዋል። እና ሉቻኖ ስፖርቱ ላይ የነበረው አስተዋጽዖ በጣም በጣም ትልቅ ነበር።


” ያኔ ድሬዳዋ ጠበብ ያለች ከተማ በመሆኗ ሉቻኖ ስለ ተጫዋቾች ውሎ።፣ አመሻሽና አዳር መረጃ አያመልጠውም።” ይባላል።

አያመልጠውም! አያመልጠውም! የሚከታተልህን ሰው ያስቀምጥብሃል። ያን ሰው አንተ አታውቀውም። እሱ ግን ይከታተልሃል። ከሉቻኖ ጋር “ተጣላሁ!” የሚል ሰው አላስታውስም። አንዴ ብቻ አስመራ ላይ በረከት ከሚባል ተጫዋች ጋር ተጣላ መሰለኝ እንጂ ከማንም ጋር ተጣልቶ አያውቅም። ይፈራል፤ ይከበራል፤ ገልበት አለው። እንደ ጉልበቱ ግን አልባሌ ቦታ መደባደብ የለም።


ከደርግ መንግስት መውረድ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ አግኝተኸው ነበር?

አዎ! አግኝቼዋለሁ። ስታዲየም ሜዳው ላይ እንግዳወርቅ ታራኩ (ሰበታ)፣ ገዛኸኝ ማንያዘዋል፣ እኔ እና ሉቻኖ ታቅፎኝ ፎቶ ተነስተናል። በሞቱ እጅግ በጣም ነው ያዘንኩት። ሞቱ ለእኔ በጣም ከባድ ነው። የተፈጥሮ ዕጣ ነው መቼስ ምን ይደረጋል። (ምስሉ ከላይ የሚታየው ነው)


ትልቅና ስመጥር ዳኛ ሆነህ ጠበቅኸው። ሲያገኝህ ምን አለህ?

ምን ብዬ ልንገርህ? ልታስታውሰው በማትችላቸው ቃላት አበረታታኝ። ሌላ ሰው ቢሆን ጠጅ፣ ጠላ፣ አረቄ፣ ሥጋ ይጋብዝሃል። እርሱ የስፖርት ትጥቅ ነው የሚሰጥህ። ባሬላ ፊሽካ ሸለመኝ። የዳኞች ቱታ፣ ካልሲ፣ መለያ፣ …. እነዚህን ሰጠኝ። በቅጽል ስሜ ነበር የሚጠራኝ። ” ጌታቸው ፖሊስ!” ይለኛል። የተለየ ፍቅር ነው የነበረኝ ለሉቻኖ። ሳይሄድ በፊት ሜክሲኮ ወረድ ብሎ ነበር የሚኖረው። በጣም ትሁት ሰው ነበር።


ከሉቻኖ ከአጠቃላዩ ስፖርታዊ ስብዕናው ለሙያህ ምን ወሰድክ?

እኔ ከሉቻኖ ትዕግስተኝነትንና ሰው መርዳትን ወስጃለሁ። ሉቻኖ ረድቶህ እንኳ ምስጋናህን አይፈልግም። የተለየ ሰው ነው ሉቻኖ። ሰሞኑን ሐዘን አልተቀመጥኩም እንጂ ቤተሰቤን እንዳጣሁ ነው የቆጠርኩት። (እንባቸውን መቆጣጠር ተሳናቸው።) መንገድ እየሄድኩ መሞቱን ሳስታውስ እምባ ይይዘኛል።


ከመንግስቱ ወርቁ ጋር የነበራቸው ወዳጅነት የተለየ ነበር።

ሁለቱ ብዙ ዓመታት የዘለቀ ወዳጅነት መስርተዋል። አንዳንድ ሰዎች መሃል ገብተው ሊያጣሏቸው ይፈልጋሉ። እነርሱ መሃል ግን ምንም አልገባም። ወሬ አይሰሙም። ሁለቱ በጣም ነበር የሚዋደዱት። ሶስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ የተመሠረተ ወዳጅነት ነው የነበራቸው።


ትልልቆቹ የእግርኳስ ሰዎቻችን እያለፉ ነው። ተገቢው እውቅና ሳይሰጣቸው እያመለጡን በመሆኑ ምን ይሰማሃል? ከዚህ በኋላስ ምን መደረግ አለበት?

ይስሟችሁም – አይስሟችሁም ትልቁ ሥራ ያለው ሚዲያው ጋ ነው። ሸክሙ ያለው ሚዲያው ጋ ነው። የአሁኑን ትውልድ መውቀስ ሳይሆን ማሳወቅ የምፈልገው ሽልማት ከሆነ በህይወት እያለ ነው መሸለም። ሉቻኖ ብዙ ሰርቷል። ለትውልዱ የሚተርፍ ታሪክ ጠይቃችሁ የሚቀበል ይቀበል፤ ትውልዱን ማሳወቅ አለባችሁ። የገንዘብ ሳይሆን የአገርና የስሜት፣ የፍላጎት መሆን አለበት። ለአገሬ ኢትዮጵያ ምን ሰራሁ? ጤናህን ጠብቀህ፣ አካባቢህን ጠብቀህ እኮ ከተጫወትክ አገርህን ብቻ ሳይሆን አንተንም ነው የምትጠቅመው። ቅድሚያ ተጠቃሚ የምትሆነው አንተ ነህ። እናንተ ቆፍራችሁም ፈልፍላችሁም ወጣቱ ይቀበላችሁም አይቀበላችሁም ወጣቱን አስተምሩ። ወጣቱ ታሪኩን እንዲያውቅ ማድረግ አለባችሁ። ታሪክን በመስራት መሻማት አለባችሁ። መምከሩ፣ ማሳወቁ ጥሩ ነው። በዳኝነት፣ አሰልጣኝነት፣ ተጫዋችነት ታሪክ የሰሩትን እዩዋቸው። እንዲታዩ ዘመን ያላገዛቸውን ሰዎች አሳዩ። ብዙዎች አልፈዋል። አሳውቁ። በአፍሪካ ዋንጫ ያልተጫወቱ ብዙ ተጫዋቾች አሉ። እነርሱንም ማንሳት ያስፈልጋል።