ባህርዳር ከተማ ተከላካይ አስፈርሟል

ወደ ወልቂጤ ከተማ ለማምራት ከዚህ ቀደም ስምምነት ፈፅሞ የነበረው ተከላካዩ ዳዊት ወርቁ የትውልድ ከተማውን ክለብ ተቀላቅሏል፡፡

ለ2015 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን በክረምቱ በማስፈረም ወደ ዝግጅት የገቡት ባህርዳር ከተማዎች የዝግጅት ምዕራፋቸውን በአሰልጣኝ አብረሃም መብራቱ ጀምረው የነበረ ቢሆንም አሰልጣኙ ወደ ፊፋ በማምራታቸው በምትኩ ደግአረገ ይግዛው በቦታው መተካታቸው ይታወቃል፡፡ አሰልጣኙም ክለቡን ከተረከቡ በኋላ የመጀመሪያ ተጫዋቻቸውን ማስፈረማቸው ይፋ ሆኗል።

የቀድሞው የደደቢት፣ ወልዋሎ እና ወልድያ ተጫዋች የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን ደግሞ በመከላከያ ያሳለፈ ሲሆን ከአንድ ወራት በፊት ወደ ወልቂጤ ከተማ ለማምራት ስምምነት ፈፅሞ የነበረ ቢሆንም የተጫዋቹ ፊርማ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን መፅደቅ አለመቻሉን ተከትሎ በይፋ ለትውልድ ከተማው ክለብ ባህርዳር ለመጫወት የሁለት ዓመት ውል በዛሬው ዕለት ፈፅሟል።

ያጋሩ