መቻል ”አመራሮች አቅጣጫ እስከሚያስተላልፉልን እና ውሳኔ እስከምናገኝ ድረስ በፍፃሜው ጨዋታ አንሳተፍም” ሲል ቅሬታውን ገለፀ

በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ውድድር ለፍፃሜ የደረሰው መቻል ቅሬታውን ለሶከር ኢትዮጵያ ልኳል።

በመዲናችን አዲስ አበባ በደማቅ ሁኔታ እየተከናወነ የሚገኘው 16ኛው የከተማው ዋንጫ ውድድር በዛሬው ዕለት የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎችን ያከናወነ ሲሆን መቻል እና ቅዱስ ጊዮርጊስም ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈው ለፍፃሜ ማለፋቸው ተረጋግጧል። ሞቅ ባለ የደጋፊዎች ድባብ ታጅቦ የተደረገው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አበቤ ለሁለቱ ክለቦች ለእያንዳንዳቸው የ10 ሚሊዮን ብር ስጦታ ማበርከታቸው ይታወቃል። ይህ ስጦታ እና እውቅና ለሁለቱ የመዲናይቱ ክለቦች ብቻ መሰጠቱን ተከትሎ አንደኛው የከተማው ክለብ የሆነው እና የፍፃሜ ተፋላሚ የሆነው መቻል ቅር መሰኘቱን ለዝግጅት ክፍላችን ገልጿል።

የመቻል ክለብ ፕሬዝዳንት የሆኑት ኮሎኔል ደረጄ መንግስቱ “መቻል የአዲስ አበባ ክለብ ነው። ከሌሎች ቦታዎች የቀረቡልንን የተሳተፉ ጥያቄ ትተን የመዲናውን ጥያቄ አክብረን እየተሳተፍን የምንገኘው የከተማው ክለብ ስለሆንን ነው። ይህ ሆኖ ሳለ ከተማ መስተዳደሩ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ብቻ ሽልማት እና እውቅና መስጠቱን አልተቀበልነውም ፤ ከፍ ያለ ቅሬታም ፈጥሮብናል።” ካሉን በኋላ ይህንን ቅሬታ ለአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንዳቀረቡም አስረድተውናል።

ኮሎኔሉ ጨምረው “ቅሬታችንን ለፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አሳውቀናል። እነርሱም ጥያቄያቸውን ለሚመለከተው አካል አቅርበው እስከ ነገ 6 ሰዓት እንደሚመልሱልን ነግረውናል። እኛም ለመከላከያ የበላይ አመራሮቻችን ጉዳዩን ነገ ጠዋት እናሳውቃለን። የመከላከያ አመራሮች አቅጣጫ እስከሚያስተላልፉልን እና ውሳኔ እስከምናገኝ ድረስ በፍፃሜው ጨዋታ አንሳተፍም።” የሚል ጠንከር ያለ ንግግራቸውን አጋርተውናል።