”አመራሮች አቅጣጫ እስከሚያስተላልፉልን እና ውሳኔ እስከምናገኝ ድረስ በፍፃሜው ጨዋታ አንሳተፍም” ሲል ቅሬታውን በትናንትናው ዕለት የገለፀው መቻል ከአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጋር ባደረገው ንግግር በፍፃሜው ጨዋታ እንዲሳተፍ መስማማት ላይ ተደርሷል።
በትናንትናው ዕለት የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አበቤ ለሁለቱ ክለቦች ለእያንዳንዳቸው የ10 ሚሊዮን ብር ስጦታ ካበረከቱ በኋላ ይህ ስጦታ እና እውቅና ለሁለቱ የመዲናይቱ ክለቦች ብቻ መሰጠቱን በመጥቀስ መቻል ቅር መሰኘቱን ለዝግጅት ክፍላችን በክለቡ ፕሬዝዳንት በኩል የላከውን ሀሳብ አቅርበን ነበር።
የክለቡ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ደረጄ መንግስቱ “የመከላከያ አመራሮች አቅጣጫ እስከሚያስተላልፉልን እና ውሳኔ እስከምናገኝ ድረስ በፍፃሜው ጨዋታ አንሳተፍም።” የሚል ሀሳባቸውን ከሰጡን በኋላ ዛሬ ረፋፍ ከአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ደረጄ ጋር ካደረጉት ውይይት በኋላ መግባባቶች ላይ እንደተደረሰ ሁለቱ አካላት ነገረውናል። በዋናነት ክለቡ በነገው የፍፃሜ ጨዋታ እንዲሳተፍ ስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን ዝርዝር ጉዳዮች ግን በቀጣይ በሚኖር ውይይት እንደሚነሱ ተጠቁሟል።
መቻል እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ነገ 10 ሰዓት 16ኛውን የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ለማግኘት ለፍፄሜ የሚፋለሙ ይሆናል።