በስድስት ክለቦች መካከል ለሰባት ቀናት በባሕር ዳር ከተማ ሲደረግ የነበረው የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ፍጻሜውን አግኝቷል።
09፡00 ላይ በቡል ኤፍ ሲ እና በወልቂጤ መካከል በተደረገው የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ በኩል መጠነኛ ፉክክር የታየበት ሲሆን የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ግን ቡሎች የተሻሉ ነበሩ። በቡሎች በኩል አራት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ሲደረጉ በወልቂጤ በኩል ሁለት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ተደርገዋል። የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉት ቡሎች ሲሆኑ 11ኛው ደቂቃ ላይ ካዚንዱላ ኢብራ ከቀኝ መስመር ወደግብ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው በቀላሉ ይዞታል። በሁለት ደቂቃዎችም ልዩነት ካሪም ንዱግዋ በቀኝ መስመር በጥሩ ሁኔታ ገፍቶ የወሰደውን ኳስ ወደግብ ቢሞክርም የግራውን ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል።
ወደ ኋላ ተመልሰው በመጫወት በሚያገኙት ኳስ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ሲከተሉ የነበሩት ክትፎዎቹ የመጀመሪያ ሙከራቸውን 17ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ አንዋር ዱላ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው የኋላሸት ሰለሞን ኃይል ባልነበረው ሙከራ የግብ ማስቆጠር አጋጣሚውን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ቡሎች ከራሳቸው የሜዳ ክልል የቅጣት ምት ሲያገኙ ኦቾላ ዋልተር ከረጅም ርቀት ያሻማውን ኳስ ካሪም ንዱግዋ በግንባሩ ገጭቶ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የላዩን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶበታል። በተደጋጋሚ ከተጋጣሚ የሜዳ ክልል መድረስ የቻሉት ቡሎች በ ካዚንዱላ ኢብራ እና በ ካሪም ንዱግዋ የግብ ሙከራዎችን ቢያደርጉም ግብ ጠባቂው በቀላሉ መያዝ ችሏል።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጭማሪ ደቂቃዎች ሲቀሩ ወልቂጤ ከተማዎች ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝተው የነበረ ሲሆን በቀኝ መስመር ሳሙኤል አስፈሪ ያሻገረውን ኳስ ተመስገን በጅሮንድ በግንባሩ ቢገጭም ግብ ጠባቂው ይዞታል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት በመልሶ ማጥቃት የሄደውና ኦኔክ ሂላሪ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው የቡሉ ካሪም ንዱግዋ በቀላሉ አስቆጥሮ ቡድኑ 1-0 በሆነ ውጤት እየመራ ወደ ዕረፍት እንዲያመራ አስችሏል።
ከዕረፍት መልስ እጅግ ተሻሽለው የቀረቡት ክትፎዎቹ በኳስ ቁጥጥሩም የግብ ዕድል በመፍጠሩም በኩል የበላይነቱን መውሰድ ችለዋል። 52ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል አስፈሪ ከቀኝ መስመር ለተመስገን በጅሮንድ ያሻማው ኳስ መረቡ ላይ አርፏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ይበልጥ የጨዋታ መንፈሳቸው የተነቃቃው ክትፎዎቹ 57ኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን ችለዋል። ጌታነህ ከበደ በግራ መስመር ከተሰጠ የቅጣት ምት ድንቅ ግብ ሲያስቆጥር አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራም ከዕረፍት መልስ ያደረጉት ቅያሪ እጅግ ውጤታማ ሆኖላቸዋል።
በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት አቤል ነጋሽ ከቀኝ መስመር ከሳጥኑ አጠገብ ለጌታነህ ከበደ አመቻችቶ ሲያቀብል ጌታነህ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ወደ ማዕዘን ሊያስወጣው ችሏል። ክትፎዎቹ መሪ መሆን ከቻሉ በኋላ ወደኋላ አፈግፍገው ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ጨዋታውን ሲያረጋጉ ታይቷል። ከዕረፍት መልስ ተቀዛቅዘው የቀረቡት ቡሎች የተሻለውን ሙከራ ያደረጉት 81ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ካላንዳ ፍራንክ ሳጥን ውስጥ የግብ ማግባት አጋጣሚ ቢያገኝም ኃይል ባልነበረው ሙከራ ቡድኑ አቻ ማድረግ የሚችል ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል። ጨዋታውም በወልቂጤ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ወልቂጤ ከተማ የመጀመሪያውን የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ማንሳት ችሏል።
በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው የወልቂጤ ከተማው ተከላካይ ዋሃብ አዳምስ የጨዋታው ኮከብ ተመርጧል።
ከጨዋታው በኋላም ለውድድሩ መሳካት ተሳትፎ ላደረጉ አካላት እና ለውድድሩ ኮከቦች የሽልማት ሥነስርዓት ተከናውኗል። የውድድሩ ተሻልሚዎች የሚከተሉት ሆነዋል።
የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ሳሙኤል አስፈሪ -> ከወልቂጤ ከተማ
የውድድሩ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ኦኬች ሳይመን -> ከቡል ኤፍ ሲ
የውድድሩ ኮከብ ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው -> ከወልቂጤ ከተማ
የውድድሩ ኮከብ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ -> ከወልቂጤ ከተማ
የውድድሩ የጸባይ ዋንጫ ተሸላሚ -> ባሕር ዳር ከተማ
ከዚህ ጨዋታ ቀደም ብሎ ረፋድ 4፡00 ላይ የሦስተኛነት ደረጃ ለማግኘት በሞደርን ጋዳፊ እና በድሬዳዋ ከተማ መካከል የተደረገው ጨዋታ በሞደርን ጋዳፊ አሸናፊነት ተጠናቋል።
ድንቅ አጨራረስ በታየባቸው ግቦች የታገዘው ጨዋታ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት እና በሁለቱም በኩል ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት የተመለከትንበት ነበር። የጨዋታው የመጀመሪያ ግብ 12ኛው ደቂቃ ላይ በሞደርኖች ሲቆጠር ሲሞን ሴሩንኩማ ከቀኝ መስመር ያሻገረትን ኳስ ለድሬዳዋ ከተማ ለመፈረም ከጫፍ የደረሰው ሙሲጌ ቻርልስ በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል።
የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ሁለቱም ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ መድረስ እና የግብ ዕድል መፍጠር ሲችሉ 42ኛው ደቂቃ ላይ የሞደርኑ ሲቢራ ዮነስ በግራ መስመር ከሳጥኑ አጠገብ ያገኘውን ኳስ አክርሮ በመምታት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ የክለቡን መሪነት ማሳደግ ችሏል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ሔኖክ ሀሰን ከቀኝ መስመር በተሻገረለትን ኳስ በአንድ ንክኪ ግሩም ግብ አስቆጥሮ የመጀመሪያው አጋማሽ 2-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።
ሁለተኛው አጋማሽ የተቀዛቀዘ እና ብዙ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር። የተሻለው ሙከራ የተደረገውም 56ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን በቀኝ መስመር የሞደርኑ ካኮሞ አሚሩ ሙኸዲን ሙሳ ላይ በሠራው ጠፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ጋዲሳ መብራቴ ወደ ግብ ቢሞክርም ግብጠባቂው በግሩም ብቃት ወደ ማዕዘን ሊያስወጣው ችሏል። ከዚህ ሙከራ በኋላ በሁለቱም በኩል ደካማ እንቅስቃሴ ያስመለከተን ሲሆን ጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ሲሞን ሴሩንኩማ ከቅጣት ምት ድንቅ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በሞደርን ጋዳፊ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የነበረው ሲሞን ሴሩንኩማ የጨዋታው ኮከብ በመባል ተመርጧል።
ውጤቱን ተከትሎም ሞደርን ጋዳፊ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ የሦስተኛነት ደረጃ በማግኘት የነሐስ ተሸላሚ ሆኗል።