የቀድሞ የፋሲል ከነማ ስድስት ተጫዋቾች ቅሬታቸውን አሰምተዋል

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ከፋሲል ከነማ ጋር ቆይታ ያደረጉ ስድስት ተጫዋቾች ያላቸውን ቅሬታ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል።

በ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀው ፋሲል ከነማ ለተጫዋቾቹ በጎንደር ከተማ ከፍተኛ አቀባበል በማድረግ ለቡድኑ አባላት የ10 ሚልየን ብር ሽልማት ለማበርከት ቃል መግባቱ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ በቅርቡ ለአብዛኛው የቡድኑ አባላት ቃል የተገባላቸው የገንዘብ ሽልማት ተበርክቷል። ሆኖም በያዝነው ዓመት ከክለቡ ጋር ለተለያዩ ስድስት ተጫዋቾች ይህ ሽልማት አለመፈፀሙ በተጫዋቾቹ ላይ ቅሬታ አስነስቷል።

ቅሬታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ የገለፁት ሙጂብ ቃሲም ፣ ያሬድ ባየህ ፣ በረከት ደስታ፣ ሰዒድ ሀሰን ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ እና ኦኪኪ አፎላቢ ናቸው። እንደ ተጫዋቾቹ ገለፃ ከሆነ “በ2014 ቡድኑ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ እንዲያጠናቅቅ የምንችለውን ሁሉ አድርገናል። በዚህም ክለቡ ሽልማት ለመስጠት ቃል በገባው መሠረት ለሌሎቹ የቡድኑ አባላት ሽልማቱን ሲሰጥ ለእኛ አለመሰጠቱ ቅር አሰኝቶናል” በማለት ተናግረዋል።

ይህን ቅሬታ ይዘን ለክለቡ ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አበበ ጋር ደውለን የገንዘብ ሽልማቱ የተሰጠው ከ2015 በጀት ለዚህ ዓመት ከቡድኑ ጋር አብረው ለሚገኙ ተጫዋቾች የማነቃቂያ ሽልማት መሆኑን በመግለፅ የስድስቱ ተጫዋቾች ቅሬታ እንደደረሳቸው ተናግረዋል። በዚህ ዙርያ የፊታችን ሐሙስ የክለቡ ቦርድ ተነጋግሮበት አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥም ነግረውናል።

ሶከር ኢትዮጵያ በዚህ ዙርያ የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎችን ተከታትላ የምታቀርብ መሆኑን እንገልፃለን።