የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የመካከለኛ-ሰሜን ዞን በ10ኛ ሳምንት ሊካሄዱ ፕሮግራም የተያዘላቸው ሁለት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው ደደቢት መሪነቱን ያጠናከረበትን ድል አስመዝግቧል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ነጥብ አስጥሏል፡፡
በ9፡00 መከላከያን የገጠመው ደደቢት 4-1 በሆነ ሰፊ ውጤት በማሸነፍ 100% የማሸነፍ ሪኮርዱን አስጠብቋል፡፡ ብርቱካን ገብረክርስቶስ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ በቮሊ በመምታት በግሩም ሁኔታ ከመረብ ባሳረፈችው ግብ ሰማያዊዎቹ ቀዳሚ ሲሆኑ ሎዛ አበራ ሁለተኛውን አክላ ደደቢት የመጀመርያው አጋማሽን በ2-0 መሪነት እንዲያጠናቅቅ ረድታለች፡፡
ከእረፍት መልስ ሙሉ የጨዋታ ብልጫ ያሳዩት ደደቢቶች ብርቱካን ገብረክርስቶስ ባስቆጠረችው ጎል 3-0 መምራት ችለዋል፡፡ ብርቱካን ያስቆጠረችው ግብ የተጫዋቿን የግል ክህሎት ያሳየች ነበረች፡፡
መከላከያዎች በምስር ኢብራሂም ግብ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረት ቢያደርጉም ሎዛ አበራ ከርቀት በግራ እግሯ አክርራ በመምታት ያስቆጠረችው ግሩም ግብ የደደቢትን ድል ያረጋገጠች ሆናለች፡፡
ደደቢት ድሉን ተከትሎ ከ9 ጨዋታ ሙሉ 27 ነጥብ እና 42 የግብ ልዩነት በመሰብሰብ በሊጉ አናት ተቀምጧል፡፡
በ11፡00 የተገናኙት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ከከፍተኛ የመሸናነፍ ፉክክር በኋላ ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል፡፡
በፈጣን እንቅስቃሴ ጨዋታውን የጀመሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቱቱ በላይ ግብ ቀዳሚ በመሆን አመዛኙን የመጀመርያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለጊዜ መመራት ሲችሉ በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ሽታዬ ሲሳይ ከእረፍት መልስ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች የቅዱስ ጊዮርጊስ ተከላካዮችን ትኩረት ማነስ ተጠቅማ ንግድ ባንክን አቻ አድርጋለች፡፡
ንግድ ባንክ ግብ ካስቆጠረ በኋላ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥሮ ሲንቀሳቀስ ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ ወደ ኋላ በማፈግፈግ ነጥብ ይዞ ለመውጣት ያደረገው ጥረት ሰምሮ ነጥብ ተጋርቶ ወጥቷል፡፡
በአጠቃላይ ዛሬ በተደረጉት ጨዋታዎች የታዩት እንቅስቃሴዎች ከሌላው ጊዜ በቁጥር ጨምሮ የመጣውን ተመልካች ያስደሰተ ሲሆን የፉክክር ደረጃው ፣ የግቦቹ ውበት እንዲሁም የተጫዋች የግል ክህሎት ድንቅ ነበር፡፡
ትላንት ጎንደር ላይ በተደረገ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ዳሽን ቢራ ቅድስት ማርያምን 3-1 አሸንፏል፡፡
የደረጃ ሰንጠረዥ
ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታዎች
አርብ መጋቢት 30 ቀን 2008
09፡00 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ልደታ (አአ)
11፡00 ኤሌክትሪክ ከ ደደቢት (አአ)