የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮ ኤሌክትሪክ

የሁለት ጊዜ ቻምፒዮኑ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ቀደመ ደረጃው ለመመለስ የፕሪምየር ሊግ ጉዞውን ይጀምራል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ታሪክ ትልቅ ስም ካላቸው ክለቦች መካከል ከውድድሩ በአዲስ መልክ መጀመር አንስቶ ተሳታፊ የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በቀድሞው አጠራሩ መብራት ኃይል አንዱ ነው። በ1990ዎቹ ሁለት ጊዜ ዋንጫውን ከማንሳት ባለፈ በኢትዮጵያ እግርኳስ ከፍ ባለ ደረጃ ለመጫወት የበቁ አዳዲስ ፊቶችን በየዓመቱ በማስተዋወቅ ትልቅ ስምን አትርፏል። ሆኖም ሚሌንየሙ ከገባ ወዲህ ይህ ታሪክ እየከዳው ሄዶ ለ21ኛ ተከታታይ የውድድር ዓመት ተሳትፎው ከጫፍ እየደረሰ ይመለስበት የነበረው የመውረድ ስጋት 2010 ላይ ይዞት ወደ ከፍተኛ ሊግ ወርዷል። ሄድ መለስ ይል በነበረው የከፍተኛ ሊግ ቆይታው ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚመልሰውን ውጤት ለማስመዝገብ አራት ዓመታትን ቢያስጠብቀውም የኋላ ኋላ ዓምና ተሳክቶለት አንድ ጨዋታ እየቀረው የተደለደለበትን ‘ምድብ ሀ’ በ 39 ነጥቦች ከተከታዩ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአራት ነጥቦች በመራቅ አሸንፎ ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን መቀላቀል ችሏል።

በኢትዮ ኤሌክትሪክ የሊግ ምልሰት የመጀመሪያው ተጠባቂ ውሳኔ ‘የአሰልጣኝነት መንበሩን ለማን ይሰጣል ?’ የሚለው ነበር። በሁለተኛ ዓመታቸው ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊግ የመለሰሱት አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና በወቅቱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለመቀጠላቸው እርግጠኛ እንደሆኑ ቢናገሩም ከከፍተኛ ሊጉ ማብቃት በኋላ እስከ ቅድመ ውድድር ዝግጅት ጊዜ የነበረው ሰፊ ክፍተት ‘ቦታው ለማን ይሰጣል ?’ የሚለው ጉዳይ ላይ በርካታ መላ ምቶች እንዲስተናግዱ በር ከፍቶ ነበር። አሰልጣኝ ክፍሌ ከዚህ ቀደም ሦስት ክለቦችን ለሊጉ አብቅተው አብረው አለመቀጠላቸው ደግሞ ለጭምጭምታዎች በር ከፋች ነበር። ሆኖም ክለቡ በአሰልጣኙ ላይ ያለውን ዕምነት በማስቀጠል ሐምሌ 08 ከአሰልጣኙ ጋር ለቀጣይ አንድ ዓመት የሚያቆየውን ውል ፈፅሟል። በመቀጠል ክለቡ በኢትዮጵያ ቡና የሚታወቁት አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማን ምክትልነት አሰልጣኝ ሲያደርግ አሰልጣኝ መሐመድ አህመድን ደግሞ የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ሆኖ ቀጥሏል። ከዚህ በተጨማሪም የቀድሞው ተጫዋቹ አሰልጣኝ ስምኦን አባይን በፐርፎርማንስ አናሊስትነት ቀጥሯል።

የዝውውር ገበያው ለኢትዮ ኤሌክትሪክ ቀላል አልነበረም። 2010 ላይ ትቶት የሄደው የሊጉ የዝውውር ሂሳብ ንረት ክለቡ በመጀመሪ እና በሁለተኛ ዕቅድ ያሰባቸውን ተጫዋቾች ለማግኘት የሚፈቅድ አልሆነም። አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ይህንን ሁኔታ ሲያስረዱ “ፕሪምየር ሊግ ላይ ፐርፎርም ያደረጉ ተጫዋቾችን ለመያዝ የገንዘብ አቅም ፈትኖናል፡፡ ባህር ዳር ሄጄ አንድ አራት አምስት ጨዋታ አይቼ ነበር። ከዛ ያመጣዋቸው ልጆች ወደ 21 ልጆች የጠየቁት ገንዘብ እና የክለቡ የፋይናንስ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ከዛ ውስጥ ለመያዝ አልቻልኩም። ሀገሪቷ ላይ በጣም ፐርፎርም ያደረጉ በ2014 በፕሪምየር ሊጉ ላይም ከእነኚህ ውስጥ አንድ አስር ልጆች ስምንት ልጆች ለመያዝ ፈልጌ ነበር አልተቻለም።” ይላሉ።

ምንም እንኳን ከከፍተኛ ሊጉ ዘንድሮ ቢያድግም በቶሎ ወደ ተፎካካሪነት የመምጣት ኃሳብ ያለው ክለቡ ኪሱን ከግምት በማስገባት ይሆኑኛል ያላቸውን ተጫዋቾች መሰብሰቡ ግን አልቀረም። በዚህም ፍቅሩ ውዴሳ እና ሰለሞን ደምሴን በግብ ጠባቂ ቦታ ላይ ሲያስፈርም ተከላካዮቹ ታፈሰ ሰርካ ፣ ኃይሌ ገብረትንሳይ ፣ ተስፋዬ በቀለ ፣ ጌቱ ኃይለማሪያም ፣ ወንድምአገኝ ማዕረግ እና ዮሐንስ ሱጌቦንም በቡድኑ አካቷል። አማካይ ክፍል ላይ ሙሴ ካበላ እና ሄኖክ አንጃ በመስመር ሚኪያስ መኮንን ፣ አላዛር ሽመልስ እና ናትናኤል ሰለሞን እንዲሁም በፊት አጥቂነት ሄኖክ አየለ እና ልደቱ ለማ በ2015 የቀዮቹ ስብስብ ውስጥ ተካተዋል። ይህም የክለቡን አዲስ ፈራሚዎች ቁጥር 15 አድርሶታል።

ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በከፍተኛ ሊጉ ምድቡን በበላይነት እንዲጨርስ ካደረጉት ተጫዋቾች መካከል በ2013ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፏቸው የማይዘነጉት ባለብዙ ልምዶቹ ምንያህል ተሾመ እና ዘሪሁን ታደለን ጨምሮ አብነት ደምሴ ፣ ኢብራሂም ከድር ፣ ስንታየሁ ዋለጬ ፣ ያሬድ የማነህ ፣ አንዳርጋቸው ይልሀቅ ፣ አቤል ሀብታሙ ፣ ማታይ ሉል እና ከፍተኛ ተሳፋ የተጣለበት ፀጋ ደርቤን ኮንትራት አራዝሟል።

ክለቡ ከዚህ ቀደም በሚታወቅበት ባህሉ ዘንድሮም ስድስት ወጣት ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን ማሳደግ ችሏል። አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ወጣቶቹ ዕድል ስለሚያገኙበት አግባብ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ቡድናቸው ከቡና ጋር ያሳየውን አቋም በማስታወስ ሀሳባቸውን ሲሰነዝሩ “እዚህ ጋር መጥቶ ፐርፎርም ካደረገ ጥሩ ከሆነ ማሰለፍ ነው። ማንም ከእናቱ ሆድ የወጣ የለም ዕድል ሲያገኝ ነው ጥሩ የሚሆነው ስለዚህ እነርሱ ላይም ትኩረት እናደርጋለን፡፡ ግን የግድ የጊዜ ጉዳይ ነው እነኚህ ተላምደው ፣ ውድድሩን ለምደው ፣ በአዕምሮ ዳብረው እስኪቀርቡ። ኮንፊደንስ ነው ፤ ፕሪምየር ሊግ ማለት በራስ መተማመን ነው ሌላ ነገር የለም። የአዕምሮ ጨዋታ ነው። ከፍተኛ ሊግ ላይ ፊትነስ ነው በብዛት። ሜዳውም ሁሉም ጭንቅንቅ ያለ ነው። ለአንደኛ ነው የምትጫወተው ከፍተኛ ሊግ ላይ እዚህ ላይ ግን አዕምሮ ነው” ይላሉ።

የኢትዮ ኤሌክትሪክ የዘንድሮ ቡድን አወቃቀር 50% በአዲስ ተጫዋቾች ላይ የተመሰረተ ሆኗል። ተጫዋቾቹ በአንድ ዓመት ኮንትራት ክለቡን መቀላቀላቸው ሲታይ ደግሞ ክለቡ አሁንም የአጭር ጊዜ ዕቅድን ይዞ እንደመጣ ያሳየናል። ከሁሉም በላይ አዲስ ቡድንን አዋቅሮ 30 ሳምንታት በሚዘልቀው ውድድር ላይ የማድረስ ከባዱ ፈተና እንደአብዛኞቹ የሊጉ አሰልጣኞች ሁሉ ለአሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተናም የመቅረቡ ጉዳይ አሰልጣኙንም ያሳሰባቸው ይመስላል። ይህንን አስመልክተን ላቀረብንላቸው ጥያቄም እንዲህ ሲሉ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተውናል።

“ለአሰልጣኝ ነው ችግር ፤ እዚህ ሀገር ውጤት ተኮር መሆን ነው፡፡ ጊዜ ካለኝ ይሄ ቡድን ጥሩ ይሆናል ፤ ደስተኛ ነኝ በቡድኑ። ግን ሥራዎች እንደምፈልገው ረክቼ አላሰራሁም ፤ ጊዜ አጠረኝ። እነኚህ ልጆች አላቀናጀውም፡፡ ማለት ጊዜው አጠረኝ ልጆች እየተንጠባጠቡ ስለፈረሙ ምን ላይ መስራት አለብኝ የሚለው ፈታኝ ነው፡፡ የእኛም ኮንትራት አንድ ዓመት ነው። እንግዲህ ዘጠኝ ወር ነው አሁን የቀረን ቡድኑ አንድ ወር ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ዓለም ላይ ተጨንቆ የሚሰራ አሰልጣኝ ካለ እኛ ብቸኛዎቹ ነን። የትኛውን ከየትኛው አሰርተህ ነው በጣም ከባድ የቤት ስራ ከባድ ጫና ነው፡፡ ጊዜ ካገኘ ጥሩ ቡድን ነው የሚሆነው። ያው እነዚህ ስራዎች ላይ ነው ያተኮርነው በጣም ጫና ፈጥሮብኛል፡፡ አምስት ስድስት ተጫዋቾች ቢያንስ በክፍያው ተስማምተው ቢመጡ እነዛን በቦታቸው ፊትነሳቸውን ማስተካከል እና የቡድን ሥራ ውስጥ ማስገባት ነው፡፡ ብዙ ሥራ የለብህም የምትፈልጋቸውን ስታመጣ ለአጨዋወትህም ፣ ለቡድንህም ኳሊቲ ናቸው። አምስት ከእነርሱ ውስጥ ቢያዝ እነዚህ ወጣቶች ላይ ተቀላቅሎ የተሻለ ስራ ትሰራለህ። ያም ቢሆን ግን ምንም ችግር የለውም ይሄኛው ቡድን ግን ትንሽ ጊዜ ይጠይቃል፡፡”

ኢትዮ ኤሌክትሪክ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ከነሐሴ መጀመሪያ አንስቶ አዳማ ላይ ሲያደርግ ቆይቷል። በአዳማው አበበ ቢቂላ ስታዲየም ልምምድኑን ሲከውን የቆየው ቡድኑ በአካል ብቃት ላይ ትኩረቱን በማድረግ በመቀጠል ወደ ቡድን ሥራዎች አምርቷል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ከሱዳኑ ኤልሜሪክ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ካደረገ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ በመሳተፍ ሁለት ጨዋታዎችን ከውኗል። አጠቃላይ የዝግጅት ጊዜው በቂ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች አድርጓል ለማለት ባያስደፍርም ከዚያም በላይ ግን የቡድን ውህደቱ ላይ ፈተና የሚሆንበት ጉዳይ አሁንም የአዲስ ፈራሚዎቹ ቁጥር መበራከት ነው። ከቁጥራቸው ባለፈ ተጫዋቾቹ ቡድኑ ዝግጅት ከጀመረበት ጊዜ አንቶ አዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ እስኪሳተፍ ድረስ በተለያዩ ጊዜያት መፈረማቸው የዝግጅት ጊዜውን በወጥነት ቡድኑን በመገንባት ሂደት ውስጥ ሆኖ እንዳያሳልፈው ዕክል የሆነበት ይመስላል። ከዚህ አንፃር ስንመለከተው በመጪው የውድድር ዓመት ክለቡ የሚወከልበት ሙሉ ቡድን አብሮ የቆየባቸው ጊዜያት በቂ ናቸው ለማለት አያስደፍርም። በሊጉ በብቁ ሁኔታ የሚፎካከር ቡድን ሆኖ ለመቀጠል በውድድሩ የመጀመሪያ ሳምንታትም ትክክለኛውን ቅርፅ ለማግኘት በሂደት ላይ ያለ ቡድን ሆኖ ልንመለከተው የምንችልበት ዕድል ሰፊ ነው። አሰልጣኙም ይህንን ሀሳብ ይጋራሉ ” ዓመታዊ ዕቅድ አቅርቤያለሁ። በራሴ መሰረት ሄጃለሁ ማለት አልችልም እና ከዕቅዱ ውጪ ቡድኑን ለማቀናጀት ጊዜ ይጠይቃል። በብዛት አዳዲሶች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡”

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ሊጉ ውድድር ሲመለስ እንደ ክለብ ያለው ደረጃ ከሁለት አቅጣጫ የሚታይ ነው። አንድም በዕድሜ አንጋፋ እና በውድድሩ የቻምፒዮንነት ታሪክ ያለው መሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ ከከፍተኛ ሊጉ ያደገ እና ከዛም ቀደም ብሎ ላለመውረድ ሲጫወት የቆየ መሆኑ የተለያየ መልክ ይሰጠዋል። እነዚህ እውነታዎች ወደ ክለቡ የሚመጡ አዳዲስ ተጫዋቾች የቡድኑን መለያ ለብሰው ለግጥሚያ ሲቀርቡ የሚኖራቸውም የሥነልቦና ደረጃ የመወሰን አቅማቸው በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። አሰልጣኝ ክፍሌ ግን ተጫዋቾቻቸው የሚኖራቸው የአዕምሯዊ አቀራረብ ከክለቡ የቅርብ ጊዜ ውጤት ይልቅ በታሪክ ላለው ስም የሚያደላ እንደሆነ ዕምነታቸውን ይገልፃሉ። “እነኚህ እንደውም ያንን ታሪክ አንዳንዶቹ አያውቁትም፡፡ ምንድነው የሚያውቁት ትልቅ ታሪክ ያለው እና ሁለቴ የኢትዮጵያ ሻምፒዮና እንደሆነ ነው። በርካታ ተጫዋቾችን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አበርክቷል፡፡ ሰባ ዓመት ታሪክ አለው። ይሄንን ነው የሚያውቁት ተጫዋቾቹ የሚነገራቸውም ይሄ ነው። በርካታ ተጫዋቾችን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከታች ከ15 ዓመት ፣ ከ17 ዓመት ፣ ከ20 ዓመት በታች በርካታ ልጆች ያሳድጋል። ለሀገሪቱ የሚጠቅም ትልቅ ተቋም ነው እና ያንን ታሪክ ነው የሚያውቁት ሁለቴም ቻምፒዮን እንደሆነ ፣ የሰባ ዓመት ታሪክ እንዳለው ይሄን ያውቃሉ። ‘ብራንድ ቡድን ነው’ ነው የሚሉት እነርሱ። አንጋፋ ክለብ ስለሚባል ሁሉም ኃላፊነት ይዞ ነው የሚጫወተው። ጥሩ ነው በጎ አመለካከት አለ፡፡”

ዘንድሮ የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከዚህ ቀደም በጠንካራ ተፎካካሪነቱ የሚታወቀውን ክለብ ከመቀበሉ ባሻገር ወደዚህ መድረክ እየደረሱ ከሚመለሱት አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተናም ጋር ትውውቅ ያደርጋል። አየር ኃይል ፣ ጅማ ከተማ እና ሰበታ ከተማን ከከፍተኛ ሊጉ ማሳደግ ችለው አብረው ያልቀጠሉት አሰልጣኙ ዘንድሮ ግን ከቀዮቹ ጋር በቀዳሚው የሀገሪትቱ ሊግ ላይ ሲሰሩ የምንመለከታቸው ይሆናል። “እኔ ያው ከመጀመሪያ ጀምሮ ራሴን ማሳየት ስለምፈልግ ነው፡፡ ከፍተኛ ሊግ አሁን መብራት ኃይል ከሚከፍለኝ ዕጥፍ ደመወዝ አግኝቻለሁ። መውጣት የሚፈልግ ቡድን አለ ፤ አናግረውኛል። ‘እስቲ ራሴን ላሳይ ቻሌንጆች አሉ ተጫዋች እንደምፈልገው አላስፈረምኩም ፈተናዎችም አሉብኝ እስቲ ምን ይመስላል ፕሪምየር ሊጉ ?’ የሚለውን እንደገና ደግሞ ሰዎች መስራት አይፈልግም ይላሉ ልክ እንደኔ ሆነው የሚያወሩ አሉ፡፡ ያወጣ እና ሌላ ይይዛል ፕሪምየር ሊግ አይፈልግም አይሰራም የሚል ነገር አለ፡፡ ይኸው ብዙ ነገር ሳይመቻች ለመስራት ትልቅ ኃላፊነት ይዤ እየጣርኩ ነው” የሚሉት አሰልጣኙ ዘንድሮ ራሳቸውን የማሳየት ዕድል ይዞላቸው የመጣ ሲሆን በዛው ልክ በአዲስ ስብስብ ወደ ሉጉ የመቀላቀላቸው ነገር ሲታይ ደግሞ ራሳቸውንም ሆነ ስብስቡን ከውድድሩ ጋር የማላመድ ፈተናም እንደሚጠብቃቸው መገንዘብ ይቻላል።

ለወጣቶች ዕድል በመስጠት እና ጥሩ እግርኳስን በመጫወት የብዙዎች ‘ሁለተኛ ቡድን’ የነበረው የቀድሞው መብራት ኃይል ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲመለስ የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን ያማከለ አቀራረብ እንደሚኖረው ይጠበቃል። በአመዛኙ ቀጥተኝነት በሚንፀባረቅበት ከፍተኛ ሊጉም ተመሳሳይ መልክ የነበረው ኤሌክትሪክ በፕሪምየር ሊጉ ከሜዳ እና ከስብስብ ጥራት አንፃር ይህን አስተሳሰብ በሚፈልገው የውጤታማነት ደረጃ ለመተግበር የተሻለ ዕድል ቢኖረውም ፈተናዎቹም መዘንጋት የለባቸውም። በተለይም አጨዋወቱ የሚፈልገውን የተግባቦት ደረጃ ለማምጣት የሚረዳ አዲሱን ስብስብ በሚገባ በሚያስተሳስር የዝግጅት ጊዜ አለማለፉ ዋነኛው ፈተናው ይሆናል። በአጨዋወት ሂደቱ ውስጥ የማጥቃት እና የመከላከል ሚዛኑን አስተማማኝ ለማድረግ ከጊዜ ጋር ካለበት ትግል ባለፈ በዝውውር መስኮቱ በሊጉ በዓመት ከአስር ግብ በላይ ሊያስቆጥርለት የሚችል ሁነኛ አጥቂ ያለመያዙ ጉዳይም ግቦችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች እንዲጠብቅ የሚያደርገው በመሆኑ የስብስቡ የውህደት ደረጃ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ከታየውም በላይ እጅግ መሻሻል ይጠበቅበታል። ይህንን ለማድረግም በየዲፓርትመንቱ ላይ አንጋፋ የሚባሉ ተጫዋቾችንም መያዙ ሊረዳው እንደሚችል ይገመታል።

ከላይ የተነሱት ነጥቦች እንዳሉ ሆነው አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና ቡድናቸው በዘንድሮው ውድድር ላይ ስለሚያልመው ውጤት ሲናገሩ ተከታዩን ሀሳብ ሰንዝረዋል። “በዚህ ዓመት ደረጃ ውስጥ ገብተን ጥሩ ተፎካካሪ ሆነን ባለበት ማቆየት ነው ፤ ግልፅ እኮ ነው፡፡ ቡድን የሚሰራው በዘጠኝ ወር በስምንት ወር ብቻ አይደለም። እነኚህም አንድ አንድ ዓመት ነው የፈረሙት። በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዋንጫ በላለው ፣ እንዲህ አደርጋለሁ ፣ ሦስተኛ ሁለተኛ ወጣለሁ ማለት ይከብዳል። በእርግጥ ጫና የለብንም ፤ ልጆቹም ጫና የለባቸውም። ካለው ነገር በእጅም የሚሰጥ ነገር የለም። እዚህ ደመወዛቸው ሦስት ልጅ ነው ሁለት ልጅ 120 ሺህ ሌሎች 70 ፣ 80 ፣ 90 እንደዚህ የሚከፈላቸው እና ጫና የለም። እንደሌሎች ክለቦች አሁን ሦስት መቶ ሺህ ፈረመ እከሌ ለዋንጫ ነው ይሄንን ሁሉ ብር አወጥቷል የሚል ጫና የለብንም ነፃ ሆነን እንጫወታለን፡፡ እግር ኳስ ነው የሚመጣውን አናውቅም እኛ ብቻ መዘጋጀት ነው ያለብን፡፡”

በዘንድሮው የቀይ ለባሾቹ ስብስብ ውስጥ በቀጣይ ዓመታት ራሳቸውን በኮከብነት ደረጃ ላይ የማድረስ ዕድሉ ያላቸው ተጫዋቾች ተካተዋል። አማካይ ክፍል ላይ አምና በቡና እና በጅማ ጥሩ የተንቁሳቀሱት አብነት ደምሴ እና ሙሴ ካበላ ይበልጥ ተሻሽለው እንደሚቀርቡ ሲጠበቅ ወጣቱ አጥቂ ፀጋ ደርቤ እና ኢብራሂም ከድር በከፍተኛ ሊጉ የጎል ምንጭ የነበሩበትን ሂዱት የማስቀጠል ኃላፊነት ይጠብቃቸዋል። በሌላ ጎን ከመስመር የሚነሳው ሚኪያስ መኮንን ይጣልበት ከነበረው ተስፋ አንፃር ዝግ ያለ ዕድገት ያሳየባቸውን ያለፉትን ዓመታት የሚያካክስ አዲስ የእግርኳስ ህይወት ለመጀመር ሌላ ዕድል ያገኛል።

ኢትዮ ኤሌክትሪከረ የ2015 የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ጨዋታውን በመጪው አርብ ከባህር ዳር ከተማ ጋር በማድረግ ይጀምራል።

የ2015 የኢትዮ ኤሌክትሪክ ሙሉ ቡድን


ግብ ጠባቂዎች

44 ፍቅሩ ወዴሳ
13 ዘሪሁን ታደለ
30 ሰለሞን ደምሴ
31 ኪሩቤል ኃይሌ

ተከላካዮች

4 ተስፋዬ በቀለ
5 ጌቱ ኃይለማሪያም
25 አንዳርጋቸው ይልሀቅ
16 ወንድምአገኝ ማዕረግ
19 ዮሐንስ ሱጌቦ
18 ኃይሌ ገብረትንሳይ
26 ታፈሰ ሰርካ
29 ማታይ ሉል
21 ያሬድ የማነህ
12 ሄኖክ አንጃው
42 ናትናኤል ዱባለ

አማካዮች

2 አብነት ደምሴ
17 ሙሴ ካበላ
8 ስንታየሁ ዋለጬ
14 ምንያህል ተሾመ
10 በረከት ብርሀኑ
50 ሄኖክ ገብረህይወት
6 ሙክረም ረሺድ

አጥቂዎች

11 ሄኖክ አየለ
7 ፀጋ ደርቤ
9 ኢብራሂም ከድር
39 ልደቱ ለማ
28 ሚኪያስ መኮንን
20 አላዛር ሽመለስ
27 ኤቤል ሐብታሙ
24 ናትናኤል ሰለሞን

የአሰልጣኝ ቡድን አባላት

ዋና አሰልጣኝ – ክፍሌ ቦልተና
ረዳት አሰልጣኝ – ገዛኸኝ ከተማ
ፐርፎርማንስ አናሊስት – ስምዖን አባይ
የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ – መሐመድ አህመድ
የቡድን መሪ – በድሉ ገብረሚካኤል
ወጌሻ – ዱናሞ ካበቶ

ያጋሩ