​የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | አርባምንጭ ከተማ

አርባምንጭ ከተማ ከአምናው የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ በነባር ስብስቡ ላይ መጠነኛ ለውጦችን አድርጎ መቅረብን መርጧል።

ከሰባት ዓመታት የፕሪምየር ሊግ ተሳትፎ በኋላ ወደ ሁለተኛው የሊግ ዕርከን የወረደው አርባምንጭ ከተማ ወደ ሊጉ ያደረገውን ምልሰት ዐምና በመልካም ውጤት አጅቦ ጨርሷል። በመጣበት ዓመት ከሊጉ ወገብ በአንድ ደረጃ ከፍ ብሎ ያገባደደው አርባምንጭ በተወሰኑ ሳምንታት ላለመውረድ ከሚጫወቱ ክለቦች ዝርዝር ውስጥ የተካተተባቸው አጋጣሚዎች ቢኖሩም በጥቅሉ ሲታይ ጥሩ አፈፃፀም በማሳየት 27 ግቦችን አስቆጥሮ እና 26 ግቦች አስተናግዶ 40 ነጥቦችን በመሰብሰብ ውድድሩን ጨርሷል። ይህም በዚያው ዓመት አብረውት ሊጉን ከተቀላቀሉት መከላከያ እና አዲስ አበባ ከተማም ሆነ በሊጉ ከሰነበቱ ክለቦች አንፃር ሲታይ አርባምንጭ በብዙ መመዘኛዎች ጥሩ የሚባል የውድድር ዓመት እንዳሳለፈ መናገር ይቻላል።

ይህ የ2014 ውድድር ዓመት የአርባምንጭ ከተማ ውጤት ክለቡ በአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ላይ ዕምነት እንዲጥል አድርጓል። በዚህም አዞዎቹን ከከፍተኛ ሊጉ ያሳደጉት እና በሊጉ ጥሩ ያፎካከሩት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ውል በአንድ ዓመት ተራዝሞላቸዋል። አርባምንጭ በአጠቀላይ የአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ላይም ለውጥ ያላደረገ ሲሆን ምክትሎቹ አሰልጣኝ አበው ታምሩ እና ማቲዮስ ለማ እንዲሁም የግብ ጠባቂ አሰልጣኙ ስለሺ ሽፈራው ከአዞዎቹ ጋር አብረው ዘልቀዋል።

አርባምንጭ ከተማ በዝውውር መስኮቱ ለሌሎች ክለቦች ምሳሌ የሚሆን ጊዜን አሳልፏል። አምና ጥሩ አፈፃፀም በነበረው ቡድን ላይ የጨመራቸው ተጫዋቾች በቁጥር ስድስት ብቻ ናቸው። በዚህም ግብ ጠባቂው አቤል ማሞ ፣ ተከላካዮቹ አዩብ በቀታ እና አካሉ አትሞ አማካዩ ኢማኑኤል ላሪያ እንዲሁም አጥቂዎቹ ተመስገን ደረሰ እና ወንድምአገኝ ኬራ አዲሶቹ የአርባምንጭ ከተማ ተጫዋቾች ሆነዋል። አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ይህን መሳዩን የክለባቸው የዝውውር ሂደት እንዲህ ገልፀውታል። “ስድስት አዳዲስ ተጫዋቾችን አምጥተናል፡፡ ሁለት አጥቂ አንድ አማካይ እና ሁለት ተከላካይ አንድ በረኛ አካተናል፡፡ ተጫዋቾችን ስናመጣ ባለፈው ዓመት የነበሩብን በማጥቃት እንዲሁም አማካይ ላይ በመከላከል ላይ በምድርም ሆነ በሰማይ የነበሩብንን የአካል ብቃትም የተለያዩ ነገሮችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ችግሮቻችንን ባየንበት መልኩ ፣ ሊጉን ባገናዘበ መልኩ የማጠናከር ሥራዎችን ሰርተናል። ጠንካራ ጠንካራ ተጫዋቾችን በተለያዩ ቦታዎች በገለፅኩት በአራቱም ዲፓርትመንት አምጥተናል፡፡”

በእርግጥም ከዓምናው ስብስብ የተለዩት ሳምሶን አሰፋ ፣ ማርቲን ኦቼና ፣ ተካልኝ ደጀኔ ፣ ፀጋዬ አበራ ፣ ፍቃዱ መኮንን እና ሀቢብ ከማልን በአግባቡ ለመተካት የተደረጉት የክለቡ ዝውውሮች በቁጥርም ሆነ በተጨዋቾች ደረጃ ተመጣጣኝነት ይታይባቸዋል። ይህ መሆኑ በሊጉ ጥቂት ግቦችን በማስተናገድ ስድስተኛ ደረጃን ይዘው ለጨረሱት አዞዎቹ ጠንካራ ጎን እንዲቀጥል መነሻ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። አምና ከአጠቃላይ የጨዋታ እሳቤም ሆነ ከተጨዋቾች ባህሪ አንፃር አርባምንጭ ከተማ ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት እንደነበረው ግልፅ ነው። በዚህ ጥንካሬ ውስጥ ከፍ ያለ ሚና የነበራቸው ተጫዋቾች ቢኖሩም እንደ ግሩፕ እና እንደ ቡድን አዞዎቹ የነበራቸው ህብረት ግን ዋነኛው የመከላከል ጥንካሪያቸው መሰረት ነበር። በላይኛው የሜዳ ክፍል ላይ ተጋጣሚ ኳስ መስርቶ እንዳይወጣ ለማድረግ በማፈን እንዲሁም አስፈላጊ ሲሆን በጥልቀት በመከላከል ቡድኑ ነጥብ ይዞ የወጣባቸው አጋጣሚዎች ላይ ከግለሰባዊ ጥንካሬ ይልቅ የቡድኑ ታክቲካዊ ትግበራ የነበረው ሚና የጎላ ነው። ዘንድሮ የተደረጉት የተመጠኑ ዝውውሮች ደግሞ ይህ ጥንካሬ ሳይሸረሸር ይበልጥ አጎልብቶ ለመምጣት ለአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ጥሩ መንገድ እንደሚሆንላቸው መናገር ይቻላል።

ከዚህ በተቃረነ ሁኔታ በማጥቃት ሂደቱ በተለይም ግብ በማስቆጠሩ ረገድ አዞዎቹ ከአምስት ክለቦች ብቻ የተሻለ ቁጥር ነበር ያስመዘገቡት። በቡድኑ ውስጥ ከነበሩት አጥቂዎች በተናጠል ያገኙት ከፍተኛው ግብ ኤሪክ ካፓይቶ ያስቆጠራቸው ሰባት ግቦች ነበሩ። ከነዚህ ውስጥ አራቱ በፍፁም ቅጣት ምት የተቆጠሩ መሆናቸው ሲታሰብ ደግሞ ቡድኑ ፊት ላይ ዘንድሮ ይበልጥ ተሻሽሎ መቅረብ እንደሚገባው ይጠቁማል። ከዚህ እውነታ አንፃር ክለቡ ፊት መስመር ላይ ያደረጋቸው ዝውውሮች በተናጠል ከአንድ አጥቂ ከአስር በላይ ግቦችን ለማግኘት ሙሉ እምነት የሚጣልባቸው ናቸው ለማለት አያስደፍሩም። በመሆኑም አዞዎቹ ያሏቸውን አጥቂዎች ግብ የማምረት አቅም መጨመር ፣ የግብ አጋጣሚዎች የሚፈጥሩባቸውን መንገዶች ማብዛት እንዲሁም ከአጥቂ መስመር ተሰላፊዎቻቸው ውጪ ካሉ ተጨዋቾች ግቦችን ለማግኘት መስራት ይጠበቅባቸዋል።

ከዝውውሮች ባለፈ ወጣት ተጫዋቾችን በማስደጉ ረገድ አርባምንጭ ከተማ ዘንድሮ የተለየ መንገድን መርጧል። በእግርኳሳችን በብዛት እንደሚታየው ክለቦች በየዓመቱ ወጣቶችን በስብስባቸው ከማካተት ባለፈ አንድ ለእናቱ በሆነው እና ውጤት በቶሎ በሚጠበቅበት የሊግ ውድድር ላይ ብቻ እንደመሳተፋቸው ለታዳጊዎች ዕድል ለመስጠት ሲቸገሩ ይታያሉ። በዚህም የቡድን ዝርዝር ውስጥ ከመካተት ባለፈ ወጣቶቹ እንደተጫዋች ሲያድጉ አንመለከትም። አዞዎቹ ይህንን አካሄድ ለመቀየር በማሰብ ይመስላል ዘንድሮ አዳዲስ ተጫዋቾችን ከማሳደግ ይልቅ አምና ዓመቱ ሲጀመር እና በመሀል ወደ ዋናው ቡድን ለቀላቀሏቸው ተጫዋቾች ዕድል መስጠትን መርጠዋል። አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ይህንን ነጥብ አስመልክተው ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተውናል።

“እግርኳስን በደንብ መረዳቱ ተገቢ ነው የሚሆነው። ባለፈው ዓመት በእኛ ደረጃ ብዙ ወጣቶችን ያሳተፈ የለም። አሁንም ምንአልባት ብሔራዊ ቡድን ከ23 ዓመት በታች አምስት ወጣት ልጆችን አስመርጠናል። እንደዚሁም ከ17 ዓመት በታችም ከተስፋ ቡድንም ባለፈው ዓመትም አሁንም ማሳደግ ላይ ነው ያለነው። ወደ አምስት የሚሆኑ ተጫዋቾችን በተለያየ ቦታ ልምድም ትምህርትም  እንዲያገኙ ያሳደግናቸው ልጆች አሉ፡፡ ምን አልባት ያው አሁን አውሮፓ እነ ሲቲ እነ ሊቨርፑልም እነ ማንችስተርም አርሰናልም ሰው አንዳንዴ በደንብ የእግር ኳሱን ባህሪ ማወቁ ተገቢ ነው ፤ በሦስት በአራት ዓመት አንድ ተጫዋች ካደገ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በየዓመቱ ብቁ እና ተስፋ ያላቸው ሊጉን ሊመጥኑ የሚችሉ ዕቅድም የሚያሳኩ ወጣቶችን እናሳድጋለን፡፡ ሰላሳውንም ሲኒየር አታደርግም ሰላሳ አምስቱም ወጣት አይሆንም። እነርሱን አንድ ላይ ወጣቱን ከነባሩ ጋር እያዋሀድክ መሄድን ይፈልጋል። እነዛ ሥራዎች ከሌሎች ክለቦች በተሻለ በስፋት የሚታየው እኛ ቡድን ላይ ነው፡፡ ወጣቶችን የማሳደግ ሥራ እኛ ቡድን ላይ በስፋት አለ። ”

አርባምንጭ ከተማ ከነሐሴ 15 ጀምሮ በመቀመጫ ከተማው የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሲከውን ቆይቷል። በአራቱም የእግርኳስ ስልጠና መሰረታዊ ክፍሎች እንዲሁም በዲስፕሊን ላይ ትኩረቱን አድርጎ ሲዘጋጅ የነበረው የአሰልጣኝ መሳይ ስብስብ በክረምት ውድድሮች ላይ አልተካፈለም። ጨዋታዎች የዝግጅት አንድ ክፍል ከመሆነቸው አንፃር በተለይም የውድድር መልክ ባላቸው ጨዋታዎች ውስጥ ማለፍ ድክመት እና ጥንካሬን ለመገንዘብ የሚሰጠውን ዕድል አርባምንጭ ባያገኝም ከጋሞ ጨንቻ ጋር ሁለት ጊዜ እንዲሁም ከወላይታ ድቻ ጋር አንድ ጊዜ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን አድርጓል።
በጥቅሉ በተረጋጋ የቡድን ግንባታ ውስጥ መቆየትን የመረጠው አርባምንጭ ከተማ የአምናው መልኩ አብሮት እንደሚዘልቅ ይጠበቃል። በቀላሉ ግብ ላለማስተናገድ የሚሰራ ፣ በጥሩ የአካል ብቃት ደረጃ ጨዋታዎችን የሚጨርስ በዚህም የተጋጣሚን የኳስ ፍሰት አቋርጦ በቶሎ ወደ ማጥቃት የሚሸጋገር ቡድን ከአዞዎቹ ይጠበቃል። ከውጤት አንፃርም አሰልጣኝ መሳይ ቡድናቸው ከአምናው በተሻለ ደረጃ ላይ ስለመጨረስ እንደሚያስቡ ይናገራሉ። “ከባለፈው ዓመት የተሻለ ዕቅድን አስበናል፡፡ አንድ ዓመትን ልምድ አድርገህ በመጣህ ቁጥር ብዙ ነገር ሊጉ ላይ እያወክ እየተሻሻልክ ትሄዳለህ፡፡ ይሄን ከማድረግ አንፃር ከባለፈው ዓመት ከፍ ያለ ነገርን አቅደናል፡፡ ከሰባት ከፍ ያለ ከአንደኛ እስከ ሰባተኛ ያለ ቦታን ከመያዝ አንፃር አንደኛንም ሆነ ሁለተኛን ታሳቢ ባደረገ ከሰባተኛ በወረደ ደረጃ ከአንድ እስከ ስድስት ለመጨረስ ነው በእኛ ደረጃ ያቀድነው። ይሄ ሲባል አንደኛ ለመውጣት አንሰራም ሁለተኛ ለመውጣት አንሰራም አይደለም፡፡ በአንድ ጀምበር የሚሆን ነገር የለም በከፍተኛ ሊግ ከሰላሳ ምናምን ቡድን ለዋንጫ ነው የተጫወትነው። ዋንጫ በልተን ነው የመጣነው። አሁን ደግሞ ትልልቅ ስኬቶችን ለማምጣት እየተጋን ነው፡፡ ሊጉን በአንደኛ ዓመታችን አይተናል በዚህ ሁለተኛ ዓመት ያው እነ ሊቨርፑልም እነ ክሎፕም ስናይ አብዛኛዎቹ ወደ አራት ዓመት ነው ሻምፒዮን ለመሆን ጊዜ የሚፈለገው። ስለዚህ በእዚህ አራት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ቻምፒዮን ለመሆን ነው የምናቅደው። ስለዚህ ከአንድ እስከ ስድስት ለመውጣት ዝግጅት አድርገናል፡፡ በእዚህ ውስጥ ራሳችንን አስገብተናል በዚህ መንገድም ለመጨረስ ነው ዕቅድ አድርገን የተዘጋጀነው እየሰራንም ያለነው፡፡”

ዓምና በወጥነት ካሳዩት ብቃት አንፃር በአዞዎቹ የ2015 የውድድር ዓመት ጎልተው የሚወጡ እና የተሻለ ኃላፊነት የሚጫንባቸው ተጫዋቾች እንደሚኖሩ ይጠበቃል። አማካዩ እንዳልካቸው መስፍን በዚህ ረገድ ዋነኛ ተጠቃሽ ሲሆን ከተከላካዮች ፊት ከነበረው ሚና ወደ ማጥቃት ዞን በመድረስ ግብ የሆኑ ኳሶችን በማመቻቸት ጭምር ያሳየውን ብቃት ዘድሮ ከኢማኑኤል ላሪያ ጋር ጥሩ ውህደት በመፍጠር ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል። የቡድኑ የኋላ መስመር ደጀን የሆነው አሸናፊ ፊዳም እንዲሁ በመሀል ተከላካይ ቦታ ላይ ጎልቶ የመውጣት ዕድል ያለው ሲሆን አደገኛ ተሻጋሪ ኳሶችን ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በማድረስ ትልቅ ሚና የነበረው ሙና በቀለም ለአዞዎቹ ዘንድሮም የግብ ምንጭ እንደሚሆን ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪ በአጥቂ ስፍራ ላይ ቡድኑ ከነበረበት ድክመት አኳያ የተመስገን ደረሰ በስብስቡ መካተት በቦታው ያለውን ፉክክር ከፍ የማድረግ እና የአዞዎቹን ፊት አውራሪዎች ከማሻሻል ባለፈ ተጫዋቹም ጥሩ አበርክቶ እንደሚኖረው ይገመታል።

በመጨረሻም ዘንድሮ ከአዞዎቹ ጋር አምስተኛ ዓመታቸውን የሚያሳልፉት አሰልጣኝ መሳይ ለደጋፊዎቻቸው ተከታዩን መልዕክት አስተላልፈዋል። “አንደኛ ደጋፊ የሚለው የሞራል ነው። ሁለተኛው የማቴሪያል እና ፋይናንሺያል ነገሮችን መደገፍ ነው። ሁሉም ባለቤት መሆን አለበት ፤ ስፖርቱ ከፍተኛ ወጪ የሚፈልግ ነው፡፡ ከፊት ለፊት መቅደምን እንፈልጋለን ይሄ ከሆነ ደግሞ ክለቡን በተለያየ መልኩ መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ በሞራል አሁን ቅድም በገለፅናቸው በማቴሪያሎች መደገፍ በጎ ካልሆነ እና የተጫዋቾችን ሞራል ከሚነካ አሰልጣኞችን ፣ አመራሮችን ከሚነካ እኛ ራሳችንን እየደገፍን ቅድሞ ያልኳቸው ዕቅዶች አሉ በዛ ዕቅድ መሠረት መጠየቅ ያለበት አካል በየደረጃው ይጠየቃል፡፡ ደጋፊው በጨዋነት እስከ መጨረሻው ክለቡን እየደገፈ በጥሩ ጊዜ ብቻ አይደለም ክለባችንን መደገፍ ያለብን በአስቸጋሪ ጊዜም ከክለቡ ጎን እየተሰለፍን ቢወርድም ተመልሰን ለሚቆም እየበረታም ቆሞ እንዲሄድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ክለባችንን እየደገፍን የምንደጋገፍበት ዓመት እንዲሆን ማሳሰብ እፈልጋለሁ፡፡”

አርባምንጭ ከተማ የ2015 የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ጨዋታውን በመጪው አርብ በውድድሩ የመክፈቻ ግጥሚያ ከወልቂጤ ከተማ ጋር በማድረግ ይጀምራል።

የ2015 የአርባምንጭ ከተማ ሙሉ ስብስብ


ግብ ጠባቂዎች
30 ይስሀቅ ተገኝ
99 አቤል ማሞ
31 መኮንን መርዶኪዮስ
1 ሠራዊት ሰዬ


ተከላካዮች
4 አሸናፊ ፊዳ
15 በርናርድ ኦቼንግ
14 ወርቅይታደስ አበበ
6 አዩብ በቀታ
12 ሙና በቀለ
3 መላኩ ኤልያስ
5 አንድነት አዳነ
2 አካሉ አትሞ
23 አስቻለው ስሜ
28 በረከት ሳሙኤል

 

አማካዮች

25 ኢማኑኤል ላሪዬ
24 መሪሁን መስቀሌ
20 እንዳልካቸው መስፍን
18 አቡበከር ሻሚል
21 አንዷለም አስናቀ
19 ቡተቃ ሻመና
27 ሱራፌል ወንድሙ
16 ፀጋዘአብ ማንያዘዋል
22 ሳሙኤል ተስፋዬ


አጥቂዎች
10 አህመድ ሁሴን
8 ተመስገን ደረሰ
11 ኤሪክ ካፖይቶ
26 ወንድማገኝ ኪራ
7 አሸናፊ ተገኝ
17 አሸናፊ ኤልያስ
9 በላይ ገዛኸኝ
29 አላዛር መምሩ

አሰልጣኞች

ዋና አሰልጣኝ – መሳይ ተፈሪ
ረዳት አሰልጣኝ –  አበው ታምሩ
ረዳት አሰልጣኝ – ማቲዮስ ለማ
የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ -ስለሺ ሽፈራው
ቡድን መሪ – መንግሥቱ ደምሴ
የህክምና  ባለሙያ – ዶ/ር ብሩክ አማሰ
ወጌሻ – ማቱሳላ ቶራቶ