የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና

በሊጉ ሰንጠረዥ ቀዳሚዎቹን ሁለት ስፍራዎች ይዘው ስለማጠናቀቅ የሚያልሙት ሲዳማ ቡናዎች በአሰልጣኙ እምነት ካለፉት ዓመታት የተሻለውን ስብስብ ይዘው አዲሱን የውድድር ዘመን የሚጀምሩ ይሆናል ፤ እኛም የክቡን የአዲሱ የውድድር ዘመን ዝግጅት በተከታዩ ፅሁፋችን ዳሰነዋል።

ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በሊጉ እጅግ ደካማ አጀማመርን አድርገው የነበሩት ሲዳማዎች ከውጤት ማጣት ባለፈ በቡድኑ አባላት እና በደጋፊዎቹ መካከል ተፈጥረው የነበሩ ውጥረቶች አጀማመራቸውን ፈታኝ አድርጎባቸዋል ፤ ነገርግን በሂደት ይህን አሉታዊ ከባቢ በማጥራት የተሻለ ግስጋሴን በማድረግ የውድድር ዘመኑን ምንም እንኳን በሁለተኝነት ካጠናቀቁት ፋሲሎች በ13 ነጥቦች ቢርቁም በ48 ነጥቦች ሊጉን በ3ኛ ደረጃ ማጠናቀቅ ችለዋል ይህን ተከትሎም በሲዳማ ቡና ቤት በአዲሱ የውድድር ዘመን ይህን ሂደት ስለማስቀጥል እና ይበልጥ ተፎካካሪ ስለመሆን ያልማሉ።

ሁለት አይነት መልክ የነበረውን የውድድር ዘመን ያሳለፉት ሲዳማዎች በውድድሩ ሂደት አሰልጣኝ ከቀየሩ ቡድኖች መካከል ተጠቃሽ ናቸው ፤ የውድድር ዘመኑን ከአሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ ጋር ቢጀምሩም በ23ኛ የጨዋታ ሳምንት በመከላከያ ያስተናገዱትን ሽንፈት ተከትሎ አሰልጣኙን በማሰናበት ቀሪውን የውድድር ዘመን በጊዜያዊነት የቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ በነበሩት የቀድሞ የቡድኑ ከ20 በታች ቡድን አሰልጣኝ ነበር የደመደሙት ፤ ወደ አዲሱ የውድድር ዘመን ሲመጡም አምና በጊዜያዊነት ተረክበው ሲያልጥኑ የቆዩትን አሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመን በቋሚነት ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ያስቀጠሉ ሲሆን ከእሳቸው በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በክለቡ በረዳት አሰልጣኝነት መስራት የቻለውን ቾንቤ ገብረህይወትንም በምክትል አሰልጣኝነት ወደ አሰልጣኝ ቡድኑ ቀላቅሏል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት በርከት ያሉ ባለ ልምድ ነባር ተጫዋቾችን ያጡት ሲዳማ ቡናዎች በተለይ ባለፉት ዓመታት በቡድኑ የማጥቃት ጨዋታ ላይ እድሎችን በመፍጠር ሆነ ግቦችን በማስቆጠር ወሳኝ የነበሩትን ዳዊት ተፈራ እና ሀብታሙ ገዛኸኝን ማጣታቸው በብዙሀኑ ዘንድ ስጋትን ያጫረ ቢመስልም የአሰልጣኙ እምነት ግን ከዚህ በተቃራኒ ነው።

ወደ ዝውውር መስኮቱ በፍጥነት ከገቡ ክለቦች መካከል አንዱ የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች በአሰልጣኙ እምነት በሁሉም የመጫወቻ ቦታዎች ቡድኑ የነበረበትን ክፍተት ለመድፈን እና የቡድኑን ቁመና ማስተካከል ያስችላሉ የተባሉ ተጫዋቾችን ገና በጊዜ ነበር ወደ ስብስባቸው መቀላቀል የቻሉት ከዚህም መነሻነት በአሰልጣኙ እምነት ቡድኑን በሊጉ ከአምናው የተሻለ ተፎካካሪ ማድረግ የሚችሉ በታክቲካል ዲሲፕሊን ሆነ በቴክኒክ ክህሎት የተሻሉ ተጫዋቾችን ስለማምጣታቸው ያምናሉ ይህም ከብዙሀኑ ስጋት በተቃራኒ ያለ ሀሳብ ነው።

እንደ አሰልጣኙ እምነት ከአምና አንስቶ በተለያዩ ሀላፊነቶችም ቢሆን ቆይታ ማድረጋቸው በቡድኑ ውስጥ የነበሩ ክፍተቶችን በመረዳት ለዘንድሮ የውድድር ዘመን ስብስባቸው አማራጮች እንዲኖሩት እና የተሻለ ቁመና እንዲኖረው በእሳቸው እምነት “እንደ ዘንድሮ ስራ ተሰርቶ አያውቅም” ሲሉ ቡድኑን ለማጠናከር በክለቡ አመራሮች ዘንድ የነበረውን ቁርጠኝነት አወድሰዋል።

ግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ ሲዳማ ቡናን ረዘም ላሉ ጊዜያት ያገለገለውን ፍቅሩ ወዴሳ ጨምሮ አምና ስብስቡን ተቀላቅሎ ከነበረው ተክለማርያም ሻንቆ ጋር የተለያዩ ሲሆን በምትካቸው በስብስቡ ከቀረው ባለልምዱ መክብብ ደገፉ ጋር እንዲፎካከር በመቐለ 70 እንደርታ የሊጉ ተፎካካሪነት በስተጀርባ ቁልፍ የነበረውን ኢኳቶሪያል ጊኒያዊውን ፊሊፕ አቮኖን የስብስባቸው አካል አድርገዋል ፤ ምንም እንኳን ግብ ጠባቂው ላለፉት ጥቂት ዓመታት ከአይናችን ቢርቅም ግብ ጠባቂው የቀደመ ብቃቱን በሲዳማ ቡና ማሳየት ከቻለ በቋሚዎቹ መካከል ሲዳማ ቡና እምነት የሚጣልበትን ዘብ ያገኙ ይመስላል።

ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ምንም እንኳን ባስቆጠራቸው ግቦች መጠን ቢሸፈንም የሲዳማ ቡና የመከላከል ሚዛን ጥያቄ የሚነሳበት ነበር በክረምቱም በዚህ ረገድ ይህን ሂደት ለመቀየር ግን እምብዛም ዝውውሮችን አልፈፀሙም ፤ ብቸኛው ዝውውርም ተከላካይ መስመር ላይ በፈጣን እድገት ላይ የሚገኘው ጊትጋት ጉትን እንዲያጣምር ባለልምዱን አንተነህ ተስፋዬ ወደ ቀድሞ ቤቱ የተመለሰበት ዝውውር ነው ፤ ይህም ዝውውር ለተከላካይ ክፍሉ ብስለትን እና መሪነትን ይጨምራል ተብሎ ሲጠበቅ ከዚህ ባለፈም የወጥነት ጥያቄ የሚነሳበት ነገርግን ጥሩ ቀን ሲያሳልፍ አስደናቂ የመከላከል አበርክቶ የነበረው ጋናዊው ያኩቡ መሀመድም በሲዳማ ቡና ለተጨማሪ ዓመት ለመቆየት ውሉን አድሷል።

አማካይ መስመር ላይም ብርሃኑ አሻሞን እና ዳዊት ተፈራን ያጡት ሲዳማ ቡናዎች በምትካቸው ሙሉቀን አዲሱ ፣ አበባየሁ ዮሀንስ እና አቤል እንዳለን አምጥተዋል ይህም ቡድኑ በተለይ በመሀል አማካይነት መጫወት የሚችሉ ተጫዋቾች አማራጩን ይበልጥ እንዲያሰፋ እድል የሚሰጡት ይሆናል ፤ ከዚህ ባለፈ ዓምና ቡድኑን የተቀላቀለው እና ብዙ ተስፋ ቢጣልበትም በቂ ነገር ማሳየት ያልቻለው ወጣቱ አማካይ ቴዎድሮስ ታፈሰም በአዲሱ የውድድር ዘመን ይበልጥ ራሱን አሻሽሎ በቡድኑ ውስጥ የተሻለ ሚና ይወጣል ተብሎ ይጠበቃል። በተመሳሳይም ከመሀል ተከላካዮች ፊት ባለው የመጫወቻ ስፍራም ከቡድኑ ደካማ የመከላከል ሚዛን በስተጀርባ ተወቃሽ የነበረው ሙሉዓለም መስፍን እና በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ቡድኑን ተቀላቅሎ ከነበረው ዩጋንዳዊው ክሪዚስቶም ንታምቢ ቡድኑ የተሻለ እንቅስቃሴን በአዲሱ የውድድር ዘመን ይጠዳሰነዋል።

ከዚህም ባለፈ ሮባ ዱካሞ እና ዮሃንስ ተሰማ የተባሉ ሁለት ወጣት የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች ቡድኑ በሰጣቸው የሙከራ ጊዜ አሰልጣኙን ማሳመናቸውን ተከትሎ ስብስቡን ተቀላቅለዋል።

ፊት መስመር ላይ ናይጄሪያ አጥቂ ጎዲዊን ኦባጅን የጨመሩት ሲዳማ ቡናዎች ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በ16 ግቦች የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ከነበረው ይገዙ ቦጋለ እና በሁለተኛው የውድድር አጋማሽ ወደ ስብስቡ ከተቀላቀለ ወዲህ 7 ግቦችን ማስቆጠር በቻለው ሳልሀዲን ሰዒድን የአጥቂ መስመራቸው በዋነኝነት የሚመራ ሲሆን ከዚህ ባለፈም በመስመሮች በኩል ያለውን ማጥቃት ይበልጥ ለማሻሻል ይረዳቸው ዘንድም ቡልቻ ሹራ ፣ እንዳለ ከበደ እና ፀጋዬ አበራም በቀጣዩ ዓመት በሲዳማ ቡና የአጥቂ ክፍል ላይ ተሳትፎ ሲያደርጉ የምንመለከታቸው ተጫዋቾች ናቸው።

ባሳለፍነው የውድድር ዘመን የሲዳማ ቡና የውድድር ዘመን ግስጋሴ ላይ በዋነኝነት ተግዳሮት ከፈጠሩ ጉዳዮች አንዱ ቡድኑ በሊጉ ያደረገው ደካማ አጀማመር ነበር ፤ አሰልጣኙም ይህን ስህተት ዘንድሮ አንደግመውም ይላሉ “አምና አጀማመር ላይ ጥሩ አልነበርንም፡፡ አጀማመር ላይ ጥሩ ብንሆን ኖሮ ሻምፒዮን ወይም በአፍሪካ ውድድሮች የመጫወት ዕድላችን ሰፊ ይሆን ነበር ስለዚህ ዘንድሮ ከመጀመሪያ ጨዋታ ጀምሮ ትኩረት አድርገን እያንዳንዱ ጨዋታዎች ለእኛ ዋጋ እንዳላቸው ከግንዛቤ አስገብተን ጠንካራ ስነ ልቦና በመገንባት ለጨዋታዎች ራሳችንን እንዲያዘጋጀን ለመቅረብ ከአሁኑ ትልቅ ስራ እየሰራን እንገኛለን ስለሆነም ከመጀመሪያው ጨዋታ ጀምሮ ጥሩ ተፎካካሪ ለመሆን እንሰራለን።” ይላሉ።

ከነሀሴ 2 አንስቶ በሀዋሳ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሲከውኑ የሰነበቱት ሲዳማዎች በወዳጅነት ጨዋታዎች ራሳቸውን ከሌሎች በሊጉ ተካፋይ ከሆኑ ክለቦች ጋር ለመፈተሽ ያደረጓቸው ጥረቶችን ባለመሳካታቸው በከፍተኛ ሊግ ተካፋይ ከሆነው ሻሸመኔ ከተማ ጋር ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ አድርገው ወደ ሊጉ የሚቀርቡ ይሆናል ይህም ምናልባት ቡድኑ ላይ በሊጉ ጅማሮ ወቅት ተፅዕኖ እንዳይፈጥርበት ስጋት የሚያጭር ነው።

ከዚህ ቀደም በቡድኑ በተጫዋችነት ሆነ በተለያዩ የአሰልጣኝነት ሀላፊነት የሰራው አሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመ በመጀመሪያ አመት የሊጉ የዋና አሰልጣኝነት ቆይታው ቡድኑን የሊጉ አሸናፊ ስለማድረግ ያልማል ፤ ” ቀን ከሌት በመስራት ከተጫዋቾቼ እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ጋር በጥሩ የቡድን መንፈስ ፣ በመከባከር እና በመፈቃቀር መስራት ከቻልን ዕቅዶቻችን የማይተገበሩበት ምንም ምክንያት የለም እና ስለዚህ ዋነኛ ዕቅዳችን የሊጉ አሸናፊ መሆን ነው ነገር ግን ይህ ካልተሳካ ደግሞ በሁለተኝነት በማጠናቀቅ ሲዳማ ቡናን የአፍሪካ ውድድር ተሳታፊ በማድረግ ቡድናችን ትልቅ ቡድን መሆኑን በማስመስከር ሲዳማ ቡና የሚለውን ስም ለዓለም ስለማስተዋወቅ እናስባለን።”

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ወጥ የሆነ እንቅስቃሴ ለማሳየት ተቸግሮ የነበረው ሲዳማ ቡና በዘንድሮው የውድድር ዘመን በዋነኝነት ይህን ችግር ቀርፎ መቅረብ ይኖርበታል ፤ ከዚህም ፍፁም ያልተረጋጋ የነበረውን የቡድኑን የመከላከል መዋቅር ማስተካከል የአሰልጣኝ ወንድማገኝ ተቀዳሚ የቤት ስራ መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም በዚህም ቡድኑ በዝውውሩ ከአንተነህ ተስፋዬ ውጭ የመከላከል ባህሪ ያለው ተጫዋች አለማስፈረሙን ተከትሎ በነበሩት ተጫዋቾች ይህን ነገር እንዴት ይቀርፉታል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል። ከዚህ ባለፈ በአሁኑ የቡድኑ ስብስብ ውስጥ መሀል ለመሀል ሆነ በመስመሮች ለማጥቃት የተመቹ የተጫዋቾች አማራጮችን እንደመያዙ ከአምናው በተሻለ አሰልጣኙ በስብስባቸው ያሉትን ተጫዋቾች አቅም ይበልጥ ለማውጣት የሚያስችል እና ተለዋዋጭ የማጥቃት ሂደትን ይዘው መቅረብ ከቻሉ ቡድኑ ከአምናው የተሻለ የማጥቃት አቅምን ጨምረው መምጣት ከቻሉ ከአምናው የተሻለ የውድድር ዘመን ከማሳለፈ የሚያግዳቸው አይኖርም።

ይገዙ ቦጋለ ዘንድሮም በሲዳማ ቡና ስብስብ የሚጠበቀው ተጫዋች ነው ፤ ከአማራጭነት ወደ ተዓማኒ የግብ አስቆጣሪነት የተለወጠው አጥቂው ከአስደናቂው የውድድር ዘመን ማግስት ዘንድሮም ሲዳማ ቡናዎች ብዙ ይጠብቁበታል ከዚህ ባለፈም አንጋፋው ሳልሀዲን ሰዒድም ልምዱን እና ያለው ግሩም አጨራረስ ሲዳማን ይበልጥ ያረዳል ተብሎ ሲጠበቅ በመከላከሉ ረገድ ደግሞ አዲሱ ፈራሚ ግብ ጠባቂ ፊሊፕ ኦቮኖ ኳሶችን በማዳን ሆነ ለተከላካዮች የራስ መተማመን በመጨመር ረገድ ተዓማኒ የሆነ ግብ ጠባቂ አጥብቆ ይፈልግ ለነበረው ስብስብ ምላሽ ይሰጣል በሚል የሚጠበቅ ሲሆን ወደ ቀድሞ ቤቱ የተመለሰውም አንተነህ ተስፋዬ ለተከላካይ መስመሩ መረጋጋትን እንዲሁ ያላብሳል ተብሎ ይጠበቃል።

በተጨማሪም ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ቡድኑ በተለያዩ ምክንያቶች የገጠመውን የቀኝ መስመር ተከላካይ ተሰላፊ ተጫዋች ችግር ለመቅረፍ ከታኛው ቡድን የመጣው ደግፌ ዓለሙ የተወጣው ሚና በትልቁ የሚነሳ ነበር ታድያ ዘንድሮም ሲዳማ ቡናዎች እንደ ደግፌ ዓለሙ ዓይነት ከእድሜ እርከን ቡድኖች የተገኙ ተስፈኛ ተጫዋቾችን በቂ የመጫወቻ ደቂቃ በመስጠት በማስተዋወቅ ረገድ ይበልጥ መስራት ይኖርባቸዋል።

የአሰልጣኝ ወንድማገኝ ተሾመው ስብስብ በመጪው ቅዳሜ መስከረም 21 ድሬዳዋ ከተማን በመግጠም የ30ሳምንት መርሃግብሩን ይጀምራል።

የሲዳማ ቡና የ2015 ስብስብ ዝርዝር

ግብ ጠባቂዎች

1 ፊሊፕ ኦቮኖ
30 አዱኛ ፀጋዬ
99 መክብብ ደገፉ

ተከላካዮች

42 ይስሀቅ ካኖ
5 ያኩቡ መሀመድ
6 መሀሪ መና
12 ግሩም አሰፋ
4 አንተነህ ተስፋዬ
24 ጊትጋት ኩት
16 ሰለሞን ሀብቴ
22 ምንተስኖት ከበደ

አማካዮች

28 ሮባ ዱካሞ
22 ዮሃንስ ተሰማ
29 በፍቅር ግዛቸው
23 በላይ ባልጉዳ
9 እንዳለ ከበደ
8 አቤል እንዳለ
17 ቡልቻ ሹራ
18 ሙሉቀን አዲሱ
21 አበባየው ዮሃንስ
20 ሙሉአለም መስፍን
15 ቴዎድሮስ ታፈሰ
10 ፍሬው ሰለሞን
ዘሪሁን በላይ
ሚካኤል ሀሲሳ

አጥቂዎች

7 ሰልሀዲን ሰይድ
14 ፀጋዬ አበራ
25 ጉድዊን ኦባጃ
11 ይገዙ ቦጋለ

አሰልጣኞች

ዋና አሰልጣኝ – ወንድማገኝ ተሾመ
ምክትል አሰልጣኝ – ቾንቤ ገብረህይወት
የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ – ስንታየው ግድየለው
ፊዚዮቴራፒ – ብሩክ ደበበ
ወጌሻ – ዮሴፍ ዮሃንስ
ቡድን መሪ – አሸብር ታመነ
ትጥቅ ያዥ – አስራት ቶማስ