የክለቦች የውድድር ዘመን ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ

የሊጉ ጅማሮ መቃረቢያ ላይ የአሠልጣኝ ለውጥ ያደረገው ባህር ዳር ከተማ በመቀመጫ ከተማው የሚጀምረውን የፕሪምየር ሊግ ጉዞ የተመለከተ ዳሰሳ እንደሚከተለው ተሰናድቷል።

የጣና ሞገዶቹ በሚል ቅፅል ስም የሚጠሩት ባህር ዳር ከተማዎች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በከፍተኛው የሀገሪቱ ሊግ 2011 ላይ መሳተፍ ከጀመሩ በኋላ እስካሁን የሊጉ ቤተሰብ ሆነዋል። ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በተመረጡ ከተሞች መደረግ ከጀመረ በኋላም እንደ ባህር ዳር ደጋፊ ሊጉን በድምቀት ያሳመረ ማግኘት የሚከብድ ይመስላል። ይህ ደጋፊ ግን በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ እና ውጤት የሚገባውን ከክለቡ ያገኘ አይመስልም። በሁለቱ ዓመታት የተመዘገበውን ግርድፍ ውጤት ብንመለከት እንኳን ቡድኑ በሊጉ አጠቃላይ ማግኘት ከሚገባው 162 ነጥቦች 68ቱን ብቻ ነው ያሳካው። ይህ አጠቃላይ ምስል ቢሆንም በእንቅስቃሴ ደረጃም ወጥ የሆነ ብቃት ሳያሳይ የሊግ ተሳትፎን ብቻ አረጋግጦ ሁለቱን ዓመታት ፈፅሟል።

የ2014 የሊጉ ውድድር ከመጀመሩ በፊት ግን በጥሩ ባለሙያዎች የተዋቀረ የሚመስለው የክለቡ ቦርድ አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱን በመንበሩ ሾሞ የአሠልጣኝ ቡድን አባላቱን እንደ አዲስ ካዋቀረ በኋላ በአንፃራዊነት የተሻሉ ተጫዋቾችን ወደ ገበያ በመውጣት በመሰብሰብ በመቀመጫ ከተማው ዝግጅቱን አከናውኖ በመዲናችን በተከናወነው 15ኛው የከተማው ዋንጫ ውድድር ላይ ተሳትፎ የዋንጫ አሸናፊ ከሆነ በኋላ ብዙዎች ለሊጉ የዋንጫ ፉክክር ሲያጩት ነበር። ቡድኑ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦችን አስቆጥሮ ድል አድርጎ አጀማመሩን ቢያሳምርም የኋላ ኋላ ግን ቀጣይ ጉዞ ከብዙዎች ግምት በተቃራኒ ነበር። በአጠቃላይ 30 ሳምንታትም ስምንት ጨዋታዎችን አሸንፎ እኩል አስራ አንድ አስራ አንድ ጨዋታዎችን ደግሞ አቻ እና ሽንፈት በማስመዝገብ በ35 ነጥቦች 12ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

ባህር ዳር ከተማ ወደ ሊጉ ካደገ በኋላ የተረጋጋ አሠልጣኝ ያገኘ አይመስልም። በኮቪድ-19 የተሰረዘውን የውድድር ዓመት ትተን ባሉት ሦስት ዓመታት ሦስት አሠልጣኞችን የተጠቀመ ሲሆን በአራተኛው ዓመትም በሌላ አሠልጣኝ ሊጉን ለመቅረብ ተዘጋጅቷል። እርግጥ ያሁኑ ሹም ሽር ካለመፈላለግ ጋር የተገናኘ ባይሆንም የቡድኑ አሠልጣኝ የነበሩት አብርሃም መብራቱ የፊፋ የቴክኒክ ኤክስፐርት ሆነው በመሾማቸው የባህር ዳርን ሥራ እንዳይበድሉ በሚል በጋራ ስምምነት መለያየቱ ግድ ብሏል። አሠልጣኙ በዝውውሮች ላይ ተሳትፈው የቅድመ ውድድር ዝግጅት አሰርተው ይህ ነገር ቢፈጠርም ከክለቡ ቦርድ ጋር ተነጋግረው ሦስት አሠልጣኞችን በእጩነት በመያዝ ማጣራት ከተደረገ በኋላ የቀድሞ የአውስኮድ፣ ኢኮስኮ፣ ወልቂጤ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሠልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ተሹመዋል። እርሳቸውም ሊጉ ሊጀምር እጅግ በተቃረበ ጊዜ ወደ ክለቡ ቢመጡም ከቀድሞ አሠልጣኙ አብርሃም ጋር በመተባበር ጊዜውን ለመጠቀም ጥረዋል። በ2014 የመጨረሻ የጨዋታ ሳምንታት ምክንያቱ በይፋ ባልተገለፀ መንገድ ከምክትል አሠልጣኙ አብርሃም መላኩ ጋር የተለያየው ክለቡም እስካሁን በምትኩ አሠልጣኝ ባያመጣም በምክትል አሠልጣኝነት ሚና ደረጄ መንግስቱን አስቀጥሎ የሊጉን ጅማሮ እየተጠባበቀ ይገኛል።

ባህር ዳር ከተማ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከሞላ ጎደል ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን ያገኘ ይመስላል። እርግጥ በዛው ልክ እንደ ፍፁም ዓለሙ፣ ግርማ ዲሳሳ፣ አህመድ ረሺድ፣ መናፍ ዐወል እና ሰለሞን ወዴሳ የመሳሰሉ በቋሚነት ከሚጫወቱ ተጫዋቾች ጋር ቢለያይም ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ ክፍሉ ድረስ ጥሩ ጭማሪ የሚያመጡ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል። በግብ ጠባቂ ቦታ ከአቡበከር ኑሪ ጋር በስምምነት የተለያየው ክለቡ በሀገሩ አይቮሪኮስት ትልቅ ተስፋ የተጣለበትን ኤሊዘር ቴፕ ሲያመጣ በተከላካይ መስመሩ ላይ ደግሞ የሰለሞን ወዴሳ እና መናፍ ዐወልን መውጣት በብሔራዊ ቡድኑ የኋላ ደጀን ያሬድ ባየ ተክቷል ፤ ለተከላካዮች ተገቢውን ሽፋን መስጠት ላይ እንዲሁም ኳሶችን ወደ ፊት ማሳደግ ላይ ክፍተት የነበረበትን የአማካይ ክፍል ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ጥሩ ዓመት ዓምና ያሳለፈውን ቻርለስ ሪባኑ ከወቅቱ የሊጉ ሻምፒዮን የአብስራ ተስፋዬ ጋር ለመሙላት ጥሯል። በተጨማሪም ጉልበት እና ፍጥነት እንዲሁም የአጨራረስ ችግር የነበረውን የአጥቂ መስመር ደግሞ በሀብታሙ ታደሰ፣ ዱሬሳ ሹቢሳ እና ፍፁም ጥላሁን ለማስተካከል ሞክሯል። እነዚህ በቋሚነት ቡድኑን ሊያገለግሉ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ተጫዋቾች ግን በወቅቱ የቡድኑ አሠልጣኝ ደግአረገ ምርጫ አለመምጣታቸው ምናልባት የምርጫ ጉዳይ ሊያስነሳ ቢችልም ሁለቱ አሠልጣኞች በአተገባበር የሚለያይ ግን ተመሳሳይ የጨዋታ መንገድ ስለሚከተሉ እምብዛም ማነቆ ላይሆን ይችላል። አሠልጣኝ ደግአረገም ይህንን በሚገባ ደግፈው አስተያየት ሰጥተውናል።

“በአብዛኛው ጥሩ ጥሩ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ለማምጣት የተሞከረበት ሂደት እንዳለ ተመልክቻለሁ ፤ አሁንም በቡድኑ ውስጥ ያሉ ተጫዋቾችን ስንመለከት ጥሩ ናቸው። ሆኖም ግን አብርሃም ኳስን ተቆጣጥሮ የሚጫወት ነው። የጨዋታ መንገዱ ከእኔ ጋር ተቀራራቢ ቢሆንም አተገባበሩ ላይ ልዩነቶች ሊኖሩ ይችላሉ። እነሱ የተወሰነ ጊዜ የሚፈልጉ ነገሮች ናቸው። በእርግጥ የተጫዋች ምርጫ 50 % ወደ ውጤት ይዞህ የሚሄድ ነውና ምናልባት ይህንን ዕድል ቀደም ብዬ አግኝቼ ቢሆን ኖሮ ወደ ቡድኔ ላካትታቸው የምችላቸው ተጫዋቾች ይኖሩ ነበር ብዬ አስባለሁ። ሆኖም ግን አሁን ያለው ቡድን መልካም የሚባል ስብስብ ነው ያለው። ይሄንን ስብስብ ወደ ቡድን ሥራ ቀይሮ ወደ ውጤት ማምጣት ደግሞ ከእኛ ይጠበቃል። በሂደት እየሠራን የተሻለ ነገር እናመጣለን ብዬ አስባለሁ። ተግዳሮቱ ግን እንዳለ ሆኖ ማለት ነው።” ብለውናል።

ከነሐሴ 7 ጀምሮ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በመቀመጫ ከተማው ባህር ዳር ከተማ መስራት የጀመረው ክለቡ በጉዳት እና በብሔራዊ ቡድን ግዳጅ ሁሉንም ስብስቡን ባያገኝም በአሠልጣኝ አብርሃም መሪነት እስከ አዲሱ ዓመት ሲዘጋጅ ቆይቶ በመጀመሪያው የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ላይ ተሳትፏል። እርግጥ በዚህ ውድድር ላይ በእንቅስቃሴም ሆነ በውጤት ረገድ በአብዛኛው አሉታዊ ነገሮች ተመዝግበው ገና በጊዜ ከምድብ ቢሰናበትም ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች የተከሰቱት ክፍተቶች ግን ሊጉ ሳይጀምር በግልፅ መታየታቸው ከጉዳታቸው ጥቅማቸው ያመዝናል። በተለይ ደግሞ ተጫዋቾቹ ላይ የታየው የፊትነስ፣የጨዋታ ዝግጁነት እና የአጨራረስ ክፍተት ባሉት ጥቂት ቀናትም ቢሆን ትኩረት እንዲሰጥባቸው የሚያደርጉ ይሆናል። የሆነው ሆኖ ግን የወቅቱ አሠልጣኝ የቅድመ ውድድር ዝግጅት አለማሰራታቸው በራሱ የሚፈጥረው ችግር በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ይህንንም በተመለከተ አሠልጣኝ ደግአረገ “ይሄ ተግዳሮቱ ከፍ ያለ ነው የሚሆነው። እውነታው ከመጀመሪያው ጀምሮ በቅድመ ውድድር ዝግጅት አለመኖሬ የራሱ የሆነ ክፍተት ይኖረዋል። ሆኖም ግን ከዋናው አሰልጣኙ ከአብርሃም ምን ላይ አተኩረው እንደሠሩ አስተያየትም ያገኘሁበት መንገድ አለ ፤ አሁን በውድድሩ (ጣና ዋንጫ) ላይ ካየናቸው እንቅስቃሴዎች በመነሳት ቢሟሉ የምንላቸውንና ክፍተቶችን ናቸው ባልናቸው ላይ ለመሥራት ጥረት እናደርጋለን። ተግዳሮቱ ግን እንዳለ ሆኖ ማለት ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ያለችው ጊዜ አጭር መሆኗ በራሱ ፈተና ነው። እግርኳስ ጫና ነው። በየትኛውም መንገድ ቢሆን ያን ጫና ተቋቁሞ ለመሥራት ነው ጥረት የምናደርገውና በተቻለን አቅም በሀሳብም፣ በሜዳ ላይ ሥራም፣ በአእምሮም እንዲሁም በአካል ብቃትም ዝግጁ ሆነው እንዲቀርቡ ለማድረግ ያለችውን ጊዜ እንጠቀማለን። አብዛኛው ግን የሚሆነው በውድድር ውስጥ ነው ቡድናችንን እየገነባን የምንሄደው እና ደጋፊውም ይህንን ግምት ውስጥ አስገብቶ በትዕግሥት እንዲጠብቀን ነው አደራ የምለው ፤ ነገርግን ደጋፊውን የሚያስደስት ቡድን እንገነባለን ብዬ አስባለሁ።” የሚል ሀሳብ አላቸው።

በውድድር ጅማሮ ዋዜማ የአሠልጣኝ መለዋወጥ መከሰቱ የሽግግር ጊዜው ላይ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ያሰጋል። ከላይ እንደገለፅነው ሁለቱ አሠልጣኞች የጋራ የሚያደርጓቸው ተመሳሳይ የአጨዋወት መንገድ መከተላቸው ግን ነገሮችን ሊያቀል ይችላል። ግን ደግሞ አሠልጣኙ በትክክል የቡድኑን የዓምና ክፍተት በራሳቸው አስተያይ አለመገንዘባቸው መዳኒቱን በግላቸው መንገድ እንዳይቀምሙ ያደርጋል። ይህ በእንዲህ አንዳለ ግን ጊዜው አጭር ቢሆንም አሠልጣኙ ሽግግሩ በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ እንደሚገኝና የቀድሞ አሠልጣኝ አሁንም እየረዷቸው እንደሆነ ይናገራሉ። “ሁሉን አቀፍ ዝግጅት ነው ያደረገው። ሰነድ ተቀብያለሁ ፤ እጅግ የሚያስደስት ነው። ይህ በሌሎች ክለቦችም ሊለመድ የሚገባው እንደዚህ አይነት ጤናማ ሽግግር ሲኖር ለስፖርታችን ዕድገትም ዕጅግ ጠቃሚ ነው። አብርሃም የሁላችንም የሙያ አባት ነው ፤ ግንባር ቀደም ሆኖ ደግሞ በዚህ ዓይነት መንገድ ሲሠሩበት የነበረውን ነገር እንደቡድን ባለፈው ዓመትም የነበረውን የቡድኑ ጠንካራ እና ደካማ ጎን ሊገልፅ በሚችል መልኩ በቂ የሆነ ሰነድ በርክክብ ወቅት ሰጥቶኛል። ሰነድ ብቻም አይደለም የነበረውን እንቅስቃሴ አጠቃላይ ሂደት ቁጭ ብለን በነበረ ውይይት ለመረዳት ችያለሁ። ቡድኑ ተገቢውን ዝግጅት ለማድረግ የሞከረበትን ሂደት ነው ያየሁት ፤ ሆኖም ግን ተጫዋቾች አምስት ስድስት ቀን ለበዓል ዕረፍት ሄደው ነበር። ያን ዕረፍት ግን ተጫዋቾቻችን በአግባቡ ተጠቅመውበታል ብዬ አላስብም። ምክንያቱም በጣና ዋንጫ ክፍተቶችን ለማስተዋል ችለናል። ምናልባት እኔ ከዛ የመነጨ ነው ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ በዚህች ባለችው አጭር ቀን አንድ ላይ አድርገን የጨዋታ ዝግጁነትም ሆነ የቅንጅት ሥራውን ነው ለመሥራት እንሞክራለን። በእርግጥ ቀኑ በጣም አጭር ነው ፤ ሆኖም ግን በሂደት በውድድሩ ውስጥም ሆነን ሥራዎችን እንሠራለን ብዬ አስባለሁ። በዚህ አጋጣሚ የጠንካራ ደጋፊ ባለቤት ነን ደጋፊ ለኛ ተጨማሪ ጉልበት ነው ፤ ሆኖም ግን ይህችን አጭር የሽግግር ጊዜ ግምት ውስጥ በማስገባት ደጋፊው ከጎናችን እንዲሆን በሂደት ግን ባህርዳር የራሱ የሆነ የጨዋታ መንገድ የሚኖረው የራሱ የሆነ መለያ ቀለም ያለው ጠንካራ ቡድን እንገነባለን ብዬ አስባለሁ ። በጣና ዋንጫውም ብዙ ተጫዋቾች በጉዳት ያልተሳተፉበት ነበር ፤ ተጫዋቾች ከጉዳት ሲመለሱ ለውድድር ብቁ ሆነው ይቀርባሉ ብዬ አስባለሁ። ከእንቅስቃሴው በመነጨ ይህችን አጭሯን ጊዜ ቅርጽ አስይዘን ለመሥራት የሞከርነው ወይም የጀመርነው ሥራ ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ነው። በተቻለን መጠን ለዋናው ውድድር አብርሃም የጀመረውን ሥራ በተሻለ መንገድ አስቀጥለን የተሻለ ቡድን ይዘን እንቀርባለን ብዬ አስባለሁ።”

ባህር ዳር ከተማ ዓምናም ጥሩ ስብስብ ቢኖረውም ኮስታራ የዋንጫ ተፎካካሪ የመሆን የሥነ-ልቦና ችግር ያለበት ይመስላል። በየቦታው የሚጫወቱ ተጫዋቾችም በግልም ሆነ በቡድናዊ መዋቅር የሚሰሯቸው ስህተቶች በተደጋጋሚ ቡድኑን ዋጋ ሲያስከፍሉ ታይቷል። ይህንን የተጫዋቾችን የግል ብቃት እና የራስ መተማመን ማሳደግ ብሎም በመዋቅራዊ ቅርፅ በማጥቃትም ሆነ በመከላከል ያለውን የህብረት ጨዋታ ማስተካከል ትልቁ የቤት ሥራ ነው። “ተጫዋቾች ያላቸውን አቅም አውጥተው እንዲጫወቱ ለማድረግ ሁለንተናዊ የሆነ ሥራ ይጠይቃል። ይህ ደግሞ ከማረፊያ ቦታቸው ይጀምራል። ከሆቴላቸው እንዲሁም ከልምምድ ቦታ እና ግላዊ ስብዕናንም ያካተተ ነው የሚሆነው እና ቡድኑ የተወሰኑ የማስተካከያ ሥራዎችን ሠርቶ ነው አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ የጋበዘው። ነባር ተጫዋቾች ደግሞ የነበረውን የክለቡ ባህል እና መንገድ ያውቃሉ እና ለአዳዲሶቹ ተጫዋቾች ያስተላልፋሉ ብለን እናስባለን። ሆኖም ግን እግርኳስ በጋራ የምትሠራው ሥራ ከመሆኑ አኳያ የተጫዋቾች እገዛም እዚህ ላይ ጠቃሚ እና አስፈላጊ ነው። ተጫዋቾቹ ከባለፈው ቁጭት በመነሳት ደጋፊውን የምንክስበት ዓመት ይሆናል ብዬ አስባለሁ ፤ ያን ደጋፊ እንክሳለን ስንል ግን በንግግር ብቻ ሊሆን አይገባም ፤ ሥራ ይጠይቃልና እኛ የቀን ዕጥረት ውጥረት ውስጥ ሆነን ነው እየሠራን ያለነውና ተጫዋቾችም ይህን እንዲረዱ ነው እየሞከርን ያለነው።” ያሉት አሠልጣኙ ተጫዋቾቹም በዕረፍት አወሳሰድ እና በአመጋገብ ተገቢውን ዕገዛ እንዲያደርጉልን እንጠይቃለን ሲሉ መልዕክታቸውን ለቡድኑ አባላት አስተላልፈዋል።

ውሀ ሰማያዊ መለያ ለባሾቹ እንደ አብዛኞቹ የሊጉ ክለቦች ከሜዳ ውጪ ያሉ አስተዳደራዊ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው እምብዛም ባይስተዋልም ሜዳ ላይ ግን የተረጋጋ እና ወጥ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ አይታይም። በዋናነት በየጨዋታው በቋሚነት ቡድኑን የሚያገለግሉ ተቀዳሚ ተጫዋቾችን ሳይመርጥ ሊጉን የፈፀመ የሚመስለው ቡድኑ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በስብስቡ ከያዛቸው 31 ተጫዋቾች አራተኛው የግብ ዘቡ ናትናኤል በልስቲ እና ታዳጊዎቹን ፍፁም ፍታለው እና ብሩክ ያለውን ብቻ ሜዳ አስገብቶ ሳይጠቀም ሌሎቹን ለመሞነር ሲጥር አስተውለናል። በየጨዋታው ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ መስመር የተጫዋቾች ለውጥ ብቻ ሳይሆን የአደራደር (Formation) እና የሚና ለውጦችም ሲከወኑ ታዝበናል። ይህ ደግሞ የቡድን ውህደት ላይ መጠነኛ ችግሮች እንደፈጠረ ይታሰባል። ከምንም በላይ ግን በቡድናዊ አጨዋወት ላይ በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጪ በተጫዋቾች መካከል እንደተፈጠሩ ሲሰማ የነበሩ ችግሮች የቡድን ህብረቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደፈጠሩ ይታመናል። ይህንን ችግር ክለቡ በተጫዋቾች የዝውውር ወቅት ለማረም የጣረ ቢመስልም ቡድኑ የገባበትን የውጤት ድባቴ ማስተካከል ግን የአሠልጣኝ ደግአረገ ተቀዳሚ ሥራ ነው። አሠልጣኙ “በአንድ ጀምበር የምትቀይረው ነገር አይኖርም። እግርኳስ ሂደት ነው። ብዙ ነገሮችን እያስተካከልን ተጫዋቾቹ የአሸናፊነት ስነ-ልቦናን እንዲላበሱልን የሚያደርግ ሥራ እንሠራለን ብዬ አስባለሁ። በዲሲፕሊንም ትልቅ ሥራ ይጠብቀናል። ከዚህ በፊት የነበሩ ክፍተቶችን አርመን ለመሄድ ነው እየሠራን ያለነው።” የሚል አስተያየታቸውን መስጠታቸው ችግሩን በሚገባ እንደተረዱ ያመላክታል።

ከዚህ ባለፈ በመከላከል እና ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚደረግ ሽግግር ቡድኑ ያለው መዋቅር መሻሻል እንደሚገባው ዓምና በበርካታ ጨዋታዎች ታዝበናል። ግለሰባዊ የአቋቋም፣ የኳስ ማቀበል እና የቦታ አያያዝ ስህተቶች እንዳሉ ሆነው ቡድኑ በአምስትም ሆነ በአራት ተከላካዮች ወደ ሜዳ በገባባቸው ጨዋታዎች ኳስ በሚያጣባቸው ጊዜያት ያለው የመከላከል አተገባበር ብዙ ክፍተቶች ያሉበት ነበር። ይህንን ለማስተካከል ግለሰቦችን መቀየር አንዱ አማራጭ ቢሆንም መዋቅሩን ማስተካከል ግን አዋጩ እና የረጅም ጊዜ መፍትሔው ነው። በዚህ ሂደት የያሬድ ባየ ቡድኑን መቀላቀል አሠልጣኙ የሚከተሉትን የኳስ ቁጥጥር ከኋላ ከማስጀመር ባለፈ በመከላከል ወቅት የሚሰጠው መረጋጋት ለቡድኑ እጅግ ከፍ ያለ ጭማሪ ነው። ከያሬድ ኋላ ያለውም ቁመታሙ የግብ ዘብ ኤሊዘር ቴፕ በሀገሩ ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት በመሆኑ ዓምና ፋሲል ገብረሚካኤል እና አቡበከር ኑሪ በጋራ ካስመዘገቡት ዘጠኝ ክሊን ሺት (በፎርፌ ከተመዘገበው አንድ ጨዋታ ውጪ) በላይ እንደሚያስመዘግብ ይገመታል። ይህ ደግሞ በራስ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ትልቅ መሻሻልን እንደሚያመጣ ይገመታል። ከዚህ በተጨማሪ ከኳስ ጋርም ከኳስ ውጪም ኃይል እና ጉልበት የሌለው የአማካይ መስመርም የጎል ምንጭ የሆነውን ፍፁም ዓለሙን ቢያጣም እንደ ቻርለስ ሪባኑ እና የአብስራ ተስፋዬን ማግኘቱ ማጣቱ ብዙ እንዳይወሳ የሚያደርገው ይመስላል። በአጥቂ መስመር ላይም እንደሚያገኙት የጨዋታ ደቂቃ ውጤታማ ያልሆኑትን እንደ ግርማ ዲሳሳ እና ዓሊ ሱሌይማን የመሳሰሉ ተጫዋቾች በሀብታሙ ታደሰ፣ ዱሬሳ ሹቢሳ፣ ፍፁም ጥላሁን መተካቱ ከፊት የጎል አማራጩን በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲያሰፋ ያደርገዋል።

“ጠንክረን ሠርተን የተሻለ ቡድን እንገነባለን ብዬ አስባለው” የሚሉት አሠልጣኝ ደግአረገ ከላይ እንደገለፅነው ሙሉ የቅድመ ውድድር ጊዜ ባለማሳለፋቸው ትልቅ ፈተና እንደሚጠብቃቸው ብንገምትም የዘንድሮውን የውድድር ዓመት ጨምሮ በሦስቱ ዓመታት ከቡድኑ ጋር ያላቸውን ዕቅድ እንደሚከተለው አስረድተውናል።

“እኔ ወደዚህ ቡድን ስመጣ ለራሴ ዕቅድ አድርጌ የመጣሁት በዚህ ሦስት ዓመት ውስጥ በአፍሪካ መድረክ ተፎካካሪ የሚሆን ጠንካራውን ባህር ዳር ከተማ የመገንባት እሳቤ በውስጤ ይዤ ነው። ያ በምን ያህል ርቀት ይሳካል የሚለውን በሂደት የምንመለከተው ነው የሚሆነው። ሆኖም ግን ባለፈው ዓመት ቡድኑ የማይገባውን ደረጃ ይዞ ወጥቷልና መጀመሪያ ይህንን ቡድን ወደማሸነፍ ስነልቦና መመለስ ነው ትልቁ የቤት ሥራ የሚሆነው። ይህ ደግሞ በሜዳ ላይ ሥራ ብቻ ሳይሆን በአእምሮም ደረጃ ተጫዋቾችን ማዘጋጀት ይጠይቃል። እኛ ጋር ካሉት ባለሙያዎች በተጨማሪ ተጋባዥ ባለሙያዎችንም በመጋበዝ በስነልቦናው ረገድ ተጫዋቾቹን ለማዘጋጀት በቀጣይ ሂደቶች ላይ ጥረት የምናደርግ ነው የሚሆነው። በዛ መልክም አዘጋጅተን ተጫዋቾቹን ለውድድር እናቀርባለን ብዬ አስባለሁ። ሆኖም ግን በዚህ ዓመት ባለፈው ከነበረበት የውጤት ድብርት አውጥተን ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ክለቡን በአስተማማኝ መሠረት ላይ ማስቀመጥ የእኔ የመጀመሪያ ዕቅዴ ነው። ይህ ደግሞ ተጫዋቾች ላይ ይህንን አስተሳሰብ በማስረጽ የማሸነፍ ስነልቦናቸውን ከፍ ለማድረግ ከልምምድ ሰዓት ጀምሮ ሥራዎችን የጀመርንበት ሁኔታ ነው ያለው። ልምምድ ላይ በፍላጎት እና በተነሳሽነት እየሠሩ ነው ያለው። ይህንን የበለጠ አጠናክረን የምንፈልገውን ነገር ለማሳካት እንሄዳለን። እንግዲህ እግርኳስ ሂደት ነው። የተሰጠኝ የሥራ ዕድል እጅግ አስደሳች ነው ፤ ብዙ ነገር እንድትሠራ ያደርግሃል። በእርግጥ ቡድኑ ተዋቅሮ ዘግይቼ ነው የገባሁትና በሂደት እየተስተካከሉ የሚሄዱ ሥራዎች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ። እኔ በዚህ ዓመት ትልቁን ነገር እንዲህ አደርጋለሁ ብል ከመጠን በላይ መጠበቅ ነው የሚሆነው ነገር ግን ይህ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም። እስከሠራን እስከጣርን ድረስ የማናሳካው ምንም ነገር አይኖርም ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ ትልቁን ነገር እያሰብን ዓመቱ መጨረሻ ላይ የሚመጣውን ውጤት የምንመለከት ይሆናል። ስለዚህ ትልቁን ስታስብ ቡድኑ አስተማማኝ ቦታ ላይ መቀመጡን እርግጠኛ መሆን ትችላለህና በዛ ልክ ጥረት እናደርጋለን ብዬ ነው የማስበው። በረጅሙ ሂደት ግን ይህንን ቡድን እየገነባን እና ክፍተቶቹን እየሞላን በመሄድ በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያን ውክሎ የሚወዳደር ጠንካራው ባህር ዳር ከተማን መፍጠር እንዲሁም የራሱ መለያ የሆነ የጨዋታ መንገድ ያለው የሚታወቅበት ተመልካችን የሚዝናናበት ቡድን እንገነባለን ብዬ አስባለሁ።” የሚል ሀሳባቸው ለዝግጅት ክፍላችን ሰጥተዋል።

ባህር ዳር ከተማ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ኤሊዘር ቴፕ፣ ያሬድ ባየ፣ ፋሲል አስማማው፣ ዳዊት ወርቁ፣ ፍራኦል መንግስቱ፣ የአብስራ ተስፋዬ፣ ቻርለስ ሪባኑ፣ ሀብታሙ ታደሠ፣ ዱሬሳ ሹቢሳ፣ ፍፁም ጥላሁን እና ተስፋዬ ታምራትን ያስፈረመ ሲሆን ከእነዚህ አስራ አንድ ተጫዋቾች መካከል ከላይ እንደገለፅነው ዓምና ቡድኑ ላይ ከነበረው ክፍተት መነሻነት በተከላካይ መስመሩ ላይ ያሬድ ፣ በግብ ጠባቂነት ኤሊዘር፣ በአማካይ ክፍል ቻርለስ እና የአብስራ እንዲሁም በአጥቂ መስመር ሀብታሙ እና ፍፁም ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋቾች እንደሚሆኑለት ይታሰባል።

ባህር ዳር ከተማ የ2015 የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ጨዋታውን ከነገ በስትያ ዓርብ 10 ሰዓት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር በደጋፊው ፊት የሚያደርግ ይሆናል።

የባህር ዳር ከተማ የ2015 ስብስብ


ግብ ጠባቂዎች

1 ኤሊዘር ቴፕ
44 ፋሲል ገብረሚካኤል
19 ይገርማል መኳንንት
40 ኑርሁሴን መሐመድ

ተከላካዮች

2 ፈንቱዲን ጀማል
27 መሳይ አገኘሁ
3 ሄኖክ ኢሳይያስ
16 ያሬድ ባየ
5 ጌታቸው አንሙት
28 ተስፋዬ ታምራት
6 ዳዊት ወርቁ
13 ፍራኦል መንግስቱ
18 ሳለአምላክ ተገኘ
31 አምሳሉ ሳሌ
15 ቴዎድሮስ መልኬ
30 ፍፁም ፍታለው

አማካዮች

23 አለልኝ አዘነ
10 ፉዐድ ፈረጃ
8 የአብስራ ተስፋዬ
21 ፍቅረሚካኤል ዓለሙ
20 ቻርልስ ሪባኑ
12 በረከት ጥጋቡ

አጥቂዎች

25 ሀብታሙ ታደሠ
24 አደም አባስ
29 ይበልጣል አየለ
7 ዱሬስ ሹቢሳ
11 ፍፁም ጥላሁን
9 ፋሲል አስማማው
17 ኦሴ ማውሊ
14 ይሄነው የማታው
32 ፈይሰል አህመድ

የአሠልጣኝ ቡድን አባላት

ዋና አሰልጣኝ – ደግአረገ ይግዛው
ምክትል አሠልጣኝ – ደረጀ መንግስቱ
የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ- አሻግሬ አድማሱ
ቡድን መሪ – ሄኖክ ሀብቴ
የህክምና ባለሙያ – ኢሳይያስ ማሞ
ቴክኒክ ዳይሬክተር – መብራቱ ሀብቱ
ሥነ-ምግብ ባለሙያ -ዶክተር ተስፋየ ብርሃኔ
ኮቪድ ኦፊሰር – ፍረወይኒ ሠመር

ያጋሩ