የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | መቻል

መቻል የቀድሞው መጠሪያውን በመመለስ እና ‘አዲስ ቡድን’ በመገንባት በብርቱ ለመፎካከር ተዘጋጅቷል።

ከሁለት ዓመታት የከፍተኛ ሊግ ቆይታ በኋላ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው የአምናው መከላከያ በሊጉ የሚያከርመውን ውጤት አስመዝግቦ ለዘንድሮ ውድድር በታሪካዊ ስያሜው ‘መቻል’ ተሰኝቶ መጥቷል። ዓምና ሊጉን በሁለት ተከታታይ ድሎች ጀምሮ ኮስታራ ተፎካካሪ ይመስል የነበረው መቻል በሂደት ወደ ሰንጠረዡ የታችኛው ክፍል ለመንሸራተት ተገዷል። ያም ቢሆን የከፋ የወራጅነት ስጋት ውስጥ ባይቆይም እንደአጀማመሩ ያላማረ ፣ ከታች እንደመምጣቱ ደግሞ የማያስከፋ ውጤትን አስመዝግቦ በሊጉ ሰንጠረዥ አጋማሽ ላይ አጠናቋል። 25 ግቦች ብቻ የተቆጠረበት መቻል በተመሳሳይ 25 ግቦችን አስቆጥሮ በ37 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ነበር የ2014 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የጨረሰው።

ይህ ውጤት ያላረካው ክለቡ ለከርሞው ስር ነቀል ለውጥ ማድረግ የጀመረው በጊዜ ነበር። በዚህም ከአዳማ ከተማ ጋር ተለያይተው የነበሩት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን በክረምቱ መግቢያ በዮሐንስ ሳህሌ ቦታ የተካበት ውሳኔ ቀዳሚው እርምጃ ሆኗል። በተጨማሪ ከግብ ጠባቂ አሰልጣኙ በለጠ ወዳጆ ጋር አብሮ ሲቀጥል አሰልጣኝ ታደሰ ጥላሁን እና አሰልጣኝ ሰለሞን ታደሰ ደግሞ በምክትልነት የመቻልን የአሰልጣኞች ቡድን ተቀላቅለዋል።

ከአሰልጣኞች ለውጥ በተጨማሪ መቻል ከአምና ወደ ዘንድሮ ይዞ የቀጠላቸው ተጫዋቾች 20% የሚሆኑትን ብቻ ነው። በመሆኑም በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ካስፈረሙ ክለቦች ተርታ የሚያስቀምጠውን የ16 ተጫዋቾች ቅጥር ፈፅሟል። አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ “ጥሩ ነው። ቡድኑ ውስጥ ከነበሩት ካለፈው ዓመት ተጫዋቾች ስድስት (6) ነበሩ። ሦስት ውላቸውን ያደሱ ፣ ሦስት ደግሞ ውል የነበራቸው አጠቃላይ ካለፈው ቡድን ላይ እነሱ ነበሩ። አንደ ስብስብ የጨዋታ ቁጥር ለማሟላት ከዝውውር ገበያው ላይ በደንብ ተሳትፈናል። በእርግጥ እኛ የምንፈልጋቸውን አንዳንድ ዝውውሮች ፈልገናቸው ያልተሳኩ አሉ። በዛው ልክ ደግሞ ፈልገናቸው ያገኘናቸው ነበሩ እና ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው።” ሲሉ በገለፁት የክለቡ የዝውውር ተሳትፎ ግብ ጠባቂዎቹ ተክለማሪያም ሻንቆ ፣ ዳግም ተፈራ እና ውብሸት ጭላሎ ተከላካዮቹ አህመድ ረሺድ ፣ ቶማስ ስምረቱ ፣ ደሳለኝ ከተማ እና የአብስራ ሙሉጌታ አማካዮቹ በኃይሉ ግርማ ፣ ተስፋዬ አለባቸው ፣ ከነዓን ማርክነህ ፣ በኃይሉ ኃይለማሪያም ፣ ፍፁም ዓለሙ ከመስመር የሚነሱት በረከት ደስታ ፣ ሳሙኤል ሳሊሶ ፣ ግርማ ዲሳሳ እንዲሁም አጥቂው ምንይሉ ወንድሙ ዘንድሮ ክለቡን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ሆነዋል።

መቻል ከአጠቃላይ ስብስቡ አንፃር ዘንድሮ የፈፀማቸው ዝውውሮች ከአምናው የተሻለ የተጫዋቾች ጥራት እንዲኖረው ያስቻለ ነው ማለት ይቻላል። በተለይም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ብቸኛ አማራጭ ይመስል የነበረው ቢኒያም በላይን ሚና ለመተካት ከነዓን ማርክነህ ፣ ፍፁም ዓለሙ ፣ በረከት ደስታ እና ሳሙኤል ሳሊሶ ወደ መቻል ቤት መድረሳቸው ትልቅ ልዩነት እንደሚፈጥር ይጠበቃል። ተጫዋቾቹ ዕድሎችን ከመፍጠር ባለፈ የግብ አስቆጣሪነት ባህሪ ያላቸው መሆኑም በ30 ጨዋታዎች 25 ግቦች ብቻ አስቆጥሮ ለነበረው ቡድን ትልቅ እርምጃ ነው። በኋላ መስመሩ ላይም 2014 ላይ በትልቅ ደረጃ የተጫወቱት ዳግም ተፈራ እና ተክለማሪያምን ሻንቆ በግቡ ብረቶች መካከል ማግኘቱ ከእነርሱ ፊት ባለልምዶቹ አህመድ ረሺድ እና ቶማስ ስምረቱ ትልቅ አቅም ካለው የአብስራ መሉጌታ ጋር የመጡበት ሂደት በበጎው የሚነሳ ነው። የተስፋዬ አለባቸውን የሀዲያ ሆሳዕና ብቃት ላስተዋለ ደግሞ መቻል አማካይ ክፍሉ የተሟላ በሚባል ደረጃ እንደተዋቀረ መረዳት ይቻላል።

የዘንድሮው ቡድን ከዓምናው ጋር ሲነፃፀር ብቻ ሳይሆን አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ረጅም ዓመታትን በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ካሳለፉ በኋላ በዋና አሰልጣኝነት በቆዩባቸው ባህር ዳር ከተማ እና አዳማ ከተማ ከያዟቸው ቡድኖች ጋር ሲነፃፀር የተሻለ የሚባል ነው። አሰልጣኙ ይህንን ሀሳብ በቀደሙት ክለቦቻቸው ቡድን ለማደራጀት ከነበራቸው ጊዜ ጋር አስተሳስረረው ሲገልፁት “ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። በእርግጥ ለምሳሌ የመጀመሪያው ዓመት ላይ በባህር ዳር ሁለት ዓመት ነው የቆየሁት እና በሁለት ዓመት ጊዜ የተሻለ ቡድን እንዲኖረን የተረጋጋ ጊዜ ነበረኝ። በአዳማ የሩጫ ሩጫ ነው። አዳማም መጥፎ ቡድን አልነበረኝም። ይሄኛው በሊጉ የተሻሉ የሚባሉትን ተጫዋቾች ለማግኘት ሞክረናል እንዳልኩህ በደንብ የፈለግናቸው ነው ያገኘናቸው። ያላገኘናቸው አሉ በርግጥ አንዳንድ ቦታ ላይ ያለመመጣጠን ችግር ይታይበታል። ከሞላ ጎደል ግን ጥሩ ቡድን አለን ብዬ አስባለሁ።” ይላሉ።

በሌላ በኩል የዝውውር ሂደቱን ስንመለከተው የአማካይ ክፍል አማራጮቹ ፊት መስመር ላይ ካሉት አማራጮቹ ጋር የሚመጣጠን አይመስልም። በእርግጥ ከስብስቡ አንፃር ቡድኑ አንድ ንፁህ ዘጠኝ ቁጥር የመጠቀም አዝማሚያ ያለው ይመስላል። ሆኖም ካለፈው ዓመት አፈፃፀማቸው አንፃር በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ደረጃ የሚፎካከር አጥቂን ይዟል ለማለት አያስደፍርም። በመሆኑም ወደ ቀድሞው ቤቱ የተመለሰው ምንይሉ ወንድሙ እና እስራኤል እሸቱን ብቃት ማሻሻል ጥሩ ተስፋ ያሳየው ተሾመ በላቸውን ወደ ከፍታው መግፋት ከአሰልጣኝ ቡድን አባላቱ ከሚጠበቁ የቤት ሥራዎች ውስጥ ይካተታል። መቻል ከእነዚህ ፈራሚዎቹ በተጨማሪ ከወጣት እና ከወታደር ቡድኖቹ ውስጥም በቡድኑ ውስጥ ያካተታቸው ተጫዋቾች ሊኖሩበት የሚችሉትን ክፍተቶች ከመሙላት አንፃር ዕድል እንደሚያገኙ ይጠበቃል።

መቻል ወደ አረንጓዴ እና ቀዩ መለያ ያመጣቸው ተጫዋቾች ጥራት የራሱን ፈተናዎች ይዞ መምጣቱም አይቀርም። የመጀመሪያው የጊዜ ጉዳይ ነው። ከግማሽ በላይ የሚሆን አዲስ ስብስብን ይዞ ውድድር መጀመር ለሀገራችን አዲስ ነገር ባይሆንም የሁኔታውን ከባድነት የሚያስረሳ ግን አይደለም። ተፈላጊ የውህደት ደረጃ ላይ የደረሰ እና በሊጉ ለወጥነት የሚፎካከር ቡድን ከመገንባት አንፃር ብቻም ሳይሆን ተጫዋቾቹ በነበሩባቸው ቡድኖች ውስጥ በአመዛኙ ቁልፍ ሚና የነበራቸው ከመሆኑ አንፃርም የመልበሻ ክፍልን ተግባቦት በመጠበቅ የቡድን መንፈሱን ጤናማ አድርጎ መቀጠል በራሱ በቀላሉ የሚታይ ነጥብ አይደለም። አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ይህንን የአብዛኞቹ አሰልጣኞች ፈተና ከሆነውን ጉዳይ ጋር በተያያዘ ይህንን አስተያየት ሰጥተውናል። “አዲስ ቡድን ስትገነባ አዳዲስ ተጫዋቾች ስታመጣ የውህደት ጊዜው አስቸጋሪ ነው።  አንዳንድ ጊዜ እንደ ዕድል ሆኖ ቶሎ ይሰርጻል አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጊዜ ያስፈልጋል። ዞሮ ዞሮ የሀገራችን እግርኳስ ባህሪ ሆኗል ፤ ብዙ ተጫዋቾችን መልቀቅ ብዙ ተጫዋቾችን ማስፈረም። ባለፈውም ዓመት አዳማ የነበረኝ ችግር ይሄ ነው። ቡድኑ እየተገነባ ባለ ሰዓት ሳትረጋጋ ነው ነገሮቹ የሚያልቁት እና አንዳንድ ጊዜ ቡድንህን የልፋትህን ፍሬ ሳታይ ለምን አዲስ ቡድን ስትገነባ ጊዜ ስለሚያስፈልገው በመጀመሪያው ዓመት ላይ መንገጫገጭ ተፈጥሮአዊ ነው። በተቻለ መጠን ከውጤት ጋር የተያያዙ መንገጫገጮች እንዳይኖሩን እና ሂደቱ ጊዜውን ጠብቆ እንዲሄድ ለማድረግ የምንችለውን እናደርጋለን።”

ሁለተኛው ፈተና ደግሞ ተጠባቂነት ነው። መቻል ከፍተኛ የደጋፊ ግፊት ይኖርበታል ተብሎ ባይጠበቅም በዝውውሩ ካፈሰሰው መዋለ ንዋይ አንፃር ግን እንደ ክለብ ውጤት በተለይም ከአምናው የተሻለ ውጤት መጠበቁ አይቀርም። ክለቦች ቡድን ለመገንባት ጊዜ አስፈላጊ መሆኑ ባይጠፋቸውም የተሻለ ጥራት ያለው ዝውውር ከመፈፀማቸው አንፃር በቶሎ ለውጦችን አይጠብቁም ብሎ ለመናገር ይከብዳል። “ቡድኑ ካመጣቸው ተጫዋቾች አንጻር ተጠባቂነቱ ከፍ ይላል። ተጋጣሚዎቻችንም ተጠባቂነቱን አስበው ይመጣሉ። ውጤት ለማምጣት ከእንደገና ውህደቱን አጠንክረህ ለመሥራት በዚህ መሃል ያለውን ነገር ማስታረቅ ከባድ ነው። በመጀመሪያ ዓመት የሥልጠና ጊዜ ሁል ጊዜ አስቸጋሪ ነው። አንዳንዴ እግርኳስ በምትፈልገው መልኩ ከተለያዩ ቦታ የተሰበሰቡ ተጫዋቾች አንድ ላይ አቆራኝተህ ቡድኑን ማቅረብ ነው። በተጨማሪ ደግሞ ውጤት ይጠበቅብሃል። ስለዚህ እነዚህን ሁለቱን ማስታረቁ ነው ከባድ። ግን ያው በመልፋት ፣ በመሥራት ተጫዋቾች ቶሎ ተረድተው እኔ በምፈልገው መንገድ እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ ለማድረግ ከዝግጅት ጀምሮ እየሠራን ነው።” የሚል ሀሳባቸውን የሰነዘሩት አሰልጣኝ ፋሲልም የተጠባቂነት ፈተናው የሚቀር አለመሆኑን የተረዱ ይመስላል።

ይህን መሳይ የቡድን ግንባታ ላይ የከረመው መቻል ከነሐሴ 9 ጀምሮ በቢሾፍቱ ማረፊያውን በማድረግ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ቅጥር ግቢ ሜዳ ላይ ዝግጅቱን ሲያደርግ ሰንብቷል። እንደ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ማብራሪያ ቡድኑ ዝግጅቱን በሦስት ክፍሎ ሲሰራ ቆይቷል። በዚህም የመጀመሪያው ክፍል ላይ በአካል ብቃት ላይ ያተኮሩ ስራዎች ፣ በሁለተኛው ክፍል ከታክቲክ ጋር የተያያዙ ሥራዎች በመጨረሻው ከወዳጅነት ጨዋታ እና ውህደት ጋር የተያያዙ ዝግጅቶችን አድርጓል። የመጨረሻው ክፍል አካል በሆኑ ጨዋታዎች መቻል ከወልቂጤ ከተማ እና ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጋር የተጫወተ ሲሆን እስከፍፃሜ በተጓዘበት የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ደግሞ ተጨማሪ አራት ጨዋታዎችን ማድረግ ችሏል።

መቻል ከስያሜ እና ከስብስብ አንፃር ብቻ ሳይሆን በአጨዋወትም ተቀይሮ እንደሚመጣ ይጠበቃል። ያልለምንም የጎል ልዩነት በጨረሰው የዓምናው የውድድር ዓመት ቡድኑ ለጥንቃቄ በማድላቱ ይኮነን ነበር። የኳስ ቁጥጥር ፍላጎት ቢኖረውም በአመዛኙ በተገደበ የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት ተሳትፎ 4-4-2 አደራደርን ምርጫው የሚያደርግ እና ለአማካይ ስፍራ ተሰላፊዎቹ ከፍ ያለ የመከላከል ኃላፊነት ይሰጥ የነበረ በመሆኑ የፈጣራ ምንጩ ተቀዛቅዞ ይታይ ነበር። አሰልጣኝ ፋሲል ደግሞ የዘንድሮው መቻልን መልክ ጠይቀናቸው ይህንን ብለዋል። “በእግርኳስ ውድድር ለማሸነፍ ውጤት ለማምጣት ወይ ጥሩ ደረጃ ለመድረስ ጨዋታ ማሸነፍ እና በእያንዳንዱ ጨዋታ ላይ ውጤት ማግኘት የግድ ነው። ስለዚህ የራስህን ብቻ ሳይሆን ተጋጣሚን ሁሉ ታያለህ ማለት ነው። በተቻለን መጠን ግን እኔ የምፈልገው እንዴት እንደሚጫወት የሚያውቅ ፣ አጥቅቶ የሚጫወት ቡድን ሜዳ ላይ እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ። ያን ለማድረግ እየሠራን ነው።”

ከአጨዋወት ባለፈ ከውጤት አንፃር ደግሞ መቻል እስከምን ድረስ ሊጓዝ እንደሚችል አሰልጣኙ ሲያስረዱ “ካለፈው ዓመት የተሻለ ሊጉ ላይ ጠንካራ  ለዋንጫ የሚፎካከር ቡድን መገንባት ነው እና ለዋንጫ ተፎካካሪ ፣ ደረጃ ውስጥ ለመግባት የሚሠራ ቡድን ለመሥራት ጠንክረን እንሠራለን። ለዛም ራሳችንን እያዘጋጀን ነው። ተጫዋቾችንም በአካልም በሥነልቦናም እናዘጋጃለን። አዲስ ቡድን እንደመሆኑ ጊዜ ሊያስፈልግ ይችላል። ግን ያው ጥረታችን በዚህ ደረጃ ነው ብዬ አስባለሁ።” ይላሉ።

በ2015 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በመቻል መለያ ጎልተው ሊወጡ የሚችሉ በርካታ ተጫዋቾች አሉ። በተለይም አማካይ ክፍል ላይ የከነዓን ፣ ፍፁም እና በረከት በጊዮርጊስ ፣ ባህር ዳር እና ፋሲል የነበራቸውን ከፍታ ማስቀጠል ይበልጥ ትኩረትን ይስባል። ከዚህም በላይ ግን ከወታደር ቡድን የተገኘው እና አምና አምስት ግቦችን ያስቆጠረው ተሾመ በላቸው በእጅጉ ተጠባቂ ነው። ዕድገቱን ማስቀጠል እና የቀጣይ ዓመታት ኮከብ መሆኑን ለማሳየት ወጣቱ አጥቂ ከቀናት በኋላ በሚጀመረው ውድድር ላይ ከፍ ባለ አቋም እንደሚመጣ ይጠበቃል። አዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ አሁንም ከግብ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዳለው ካሳየው ተሾመ በተጨማሪ አምና በተለያዩ ቦታዎች ላይ ይሰለፍ የነበረው እና በታታሪነት የሚንቀሳቀሰው ግሩም ሀጎስም ተጠቃሽ ነው። በአሰልጣኝ ፋሲል ስር ተጫዋቹ የሚሰጠው ኃላፊነት ምን እንደሚሆን ሊጉ ሲጀመር የሚጠበቅ ቢሆንም በመስመር ተከላካይነትም ሆነ በአማካይነት ያሳየው ብቃት እና የቆመ ኳስ አጠቃቀሙ ዘንድሮ የተሻለ አበርክቶ ይኖረዋል ተብሎ እንዲጠበቅ ያደርገዋል። በጅማ አባ ጅፋር ዓመቱን ያሳለፈው ተከላካዩ ያብስራ ሙሉጌታም ያሳየው ብስለት ዘንድሮም ከቀጠለ ለመቻል ልዩነት ፈጣሪ መሆን እንደሚችል ይገመታል።

በ1990ዎቹ መገባደጃ ላይ በአምበልነት የመሩት የያኔው መከላከያ የአሁኑ መቻልን በዋና አሰልጣኝነት የተረከቡት ፋሲል ተካልኝ በመጨረሻ በሰጡን አስተያየት የመቻልን የዝግጅት ጊዜ የዳሰስንበትን ፅሁፍ እንቋጫለን።

“እግርኳስ ጊዜ ያስፈልገዋል። አንዳንድ ጊዜ ሳትረጋጋ ወይም ደግሞ የቡድንህን ፍሬ ሳታይ አንዳንድ ጊዜ ነገሮች ይበላሻሉ። ዞሮ ዞሮ ግን አሁን እንደሚወራው መቻል ከሌሎች በተለየ ሁኔታ ብዙ ትልልቅ ተጫዋቾች እንደተሰበሰበ አድርጎ መታየቱ ስህተት ነው ብዬ ነው የማስበው። እንደውም ሌሎቹ ከኛ በተለየ መልኩ ተረጋግተው በሚፈልጉበት ቦታ ወሳኝ ወሳኝ ተጫዋቾችን አዟዙረው የተሻለ ዕድል ይዘው በውድድሩ እንደሚመጡ እንረዳለን። ለዛ ግን ራሳችንን አዘጋጅተን ደጋፊዎቻችን የሚደሰቱበት ቡድን እንዲኖረን በመሥራት እና በመሥራት ብቻ እንገኛለን።”

መቻል የ2015 የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ጨዋታውን በመጪው ሰኞ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር በማድረግ ይጀምራል።

የመቻል የ2015 ሙሉ ቡድን



ግብ ጠባቂዎች

1 ተክለማሪያም ሻንቆ
31 ዳግም ተፈራ
22 ውብሸት ጭላሎ

ተከላካዮች

2 ኢብራሂም ሁሴን
11 ዳዊት ማሞ
6 አሚን ነስሩ
4 ቶማስ ስምረቱ
13 አሕመድ ረሺድ
15 ያብስራ ሙሉጌታ
25 ደሳለኝ ከተማ
12 ዮዳዬ ዳዊት

አማካዮች

21 ተስፋዬ አለባቸው
23 ምንተስኖት አዳነ
10 ፍፁም ዓለሙ
8 ከነዓን ማርክነህ
21 በኃይሉ ግርማ
5 ግሩም ሀጎስ
27 በኃይሉ ኃይለማሪያም
18 ዮሐንስ መንግሥቱ

አጥቂዎች

9 እስራኤል እሸቱ
17 ሳሙኤል ሳሊሶ
7 በረከት ደስታ
14 ምንይሉ ወንድሙ
19 ግርማ ዲሳሳ
16 ተሾመ በላቸው
24 እዮብ ደረሰ
45 ቹል ላም

አሰልጣኞች

ዋና አሰልጣኝ – ፋሲል ተካልኝ
ረዳት አሰልጣኝ – ታደሰ ጥላሁን
ረዳት አሰልጣኝ – ሻለቃ ሠለሞን ታደለ
የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ – በለጠ ወዳጆ
የህክምና ባለሙያ – ዶ/ር ጌትዬ ተመስገን
ወጌሻ – ሻለቃ ደጀኔ አበበ
የቡድን መሪ – ሻለቃ ዓለሙ ዘነበ