የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ ውድድር የሚጀምርበት ቀን ይፋ ሆነ

የ2015 የኢትዮጵያ ወንዶች ከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ የውድድር መጀመርያ ቀን እና የዕጣ ማውጣት መርሐ ግብር የሚከናወንበት ዕለት ይፋ ሆነ።

የ2015 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከፍተኛ እና አንደኛ ሊጎች የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከጳጉሜ 1 ጀምሮ ክፍት መደረጉ የሚታወስ ሲሆን ከተሳታፊዎች ብዛት አንፃር ውድድሮችን በጊዜ ለመጀመር በማሰብ የውድድር ዳይሬክቶሬት የውድድሮቹ መጀመርያ እና የዕጣ ማውጣት ቀንን ማሳወቁን የውድድሩ የበላይ አካል የሆነው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በድረ-ገፁ አስነብቧል።

በዚህም መሠረት የከፍተኛ ሊግ የዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ጥቅምት 28 የሚደረግ ሲሆን የአንደኛ ሊግ ደግሞ ጥቅምት 29 ይከናወናል። ህዳር 3 ደግሞ ሁለቱም ውድድሮች የሚጀመሩበት ቀን እንዲሆን መወሰኑ ተመላክቷል። በተጨማሪም እስከ ህዳር 15 የነበረው የሁለቱ ሊጎች የተጫዋቾች የዝውውር ጊዜ የቀን ሽግሽግ ተደርጎበት እስከ ጥቅምት 25 ብቻ እንደሚከናወን ተገልጿል።