የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | ኢትዮጵያ መድን

በ1980ዎቹ አጋማሽ ከሀገር አልፎ በአህጉራዊ ውድድሮች የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ የነበረው ቡድን ከ1990ዎቹ መጨረሻ አንስቶ የነበረው ገናናነት ታሪክ ሆኖ አሁን ላይ ሊጉን ከስምንት ዓመታት ጥበቃ በኋላ ዳግም ተቀላቅሏል ፤ እኛም በዚህኛው ፅሁፋችን መድን ራሱን ለፕሪሚየር ሊግ ህይወት እያዘጋጀበት ስላለው መንገድ ተከታዩን ዳሰሳ አሰናድተናል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ በቀደመው ዘመን በገናናነታቸው ከሚጠቀሱ ክለቦች አንዱ የነበረው ኢትዮጵያ መድን አሁን ላይ በብዙዎች አዕምሮ ውስጥ ትዝታ ሆኖ የቀረውን ተፎካካሪነቱን ስለመመለስ ያልማል። ከ2007 በኋላ ዳግም ወደ ተናፈቁበት የሀገሪቱ ከፍተኛ እርከን ለመመለስ በተለያዩ አጋጣሚዎች ተቃርቦ የነበረ ሲሆን ይህ ጥረታቸው በስተመጨረሻም በ2014 የውድድር ዘመን ፍሬ አፍርቷል።በከፍተኛ ሊግ “ምድብ ሐ”ተደልድሎ የነበረው ቡድን እስከ መጨረሻው በከፍተኛ ፉክክር በዘለቀው ውድድር በ40 ነጥቦች ነቀምት ከተማን አስከትለው ወደ ሊጉ መመለሳቸው ይታወሳል።

በ2011 እና በ2013 የውድድር ዘመን ቡድኑን የመሩት ወጣቱ አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድም በ2011 በአንድ ነጥብ ተበልጠው ያጡትን ዕድል በ2013 ዳግም ወደ ኢትዮጵያ መድን ተመልሰው ቡድኑን ወደ ሊጉ በማብቃት ታሪክ መፃፍ ችለዋል ፤ ነገርግን የቡድኑ አመራሮች “ክለቡን በሊጉ የተደላደለ ቡድን ለማድረግ በማለም” በእሳቸው ምትክ በሊጉ ከተለያዩ ክለቦች ጋር የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ባለታሪክ የሆኑትን አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን ወደ መንበሩ አምጥተዋል። የክለቡ ሹም ሽር በዚህ ያላበቃ ሲሆን ባለፉት ዓመታት ክለቡን በፕሬዚዳንትነት የመሩት አቶ ተምትም ቶላንም እንዲሁ በቀድሞ ፕሬዚዳንታቸው በአቶ ካሳሁን ፀጋዬ ቀይረዋል።

ከክለቡ የአሰልጣኝ ሹም ሽር ጋር ተያይዞ በክረምቱ ብዙ ሀሳቦች ሲዘዋወሩ ቆይተዋል ከዚህ ጋር በተያያዘም የክለቡ አዲሱ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ “አሰልጣኝ የመምጣት የመሄድ ጉዳይ የነበረ እና የሚኖር ነው ፤ ምንም አዲስ ነገር የለውም የትኛውም አሰልጣኝ አዲስ ክለብ ሲቀጠር አሰልጣኝ ተሰናበቶ ነው እኔም ስሰናበት ሌላ ይተካል ይህ ያለም የሚኖርም ነው።ግን ይሄ ለምን ተጋኖ እንደተወራ አልገባኝም።”ይላሉ። ከአሰልጣኝ ገብረመድህን በተጨማሪ በሲዳማ ቡና አብረዋቸው የሰሩት ምክትላቸው ዶ/ር ለይኩን ታደሰ ወደ ኢትዮጵያ መድን አምርተው በስራ ላይ ቢገኙም ቅጥራቸው ግን በሂደት ላይ መሆኑን ለማወቅ ችለናል። በተጨማሪነትም በቀድሞው አሰልጣኝ ስር በምክትል አሰልጣኝነት እና በግብ ጠባቂ አሰልጣኝነት ሲሰሩ የነበሩት ሀሰን በሽር እና አንተነህ ላቀው ለተጨማሪ ዓመት ከቡድኑ ጋር የሚቀጥሉ ይሆናል።

አሰልጣኙ ከዚህ ቀደም በአብዛኛው በሰንጠረዡ አናት ተፎካካሪ የሆኑ ቡድኖችን በማሰልጠን ይታወቁ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ግን ከታች የመጣውን ኢትዮጵያ መድንን ለመያዝ ስለመወሰናቸው ሲያብራሩም ትልቅ ፈተና መኖሩን ተረድተው ለመጋፈጥ ስለመምጣታቸው እና በንፅፅር በስብስባቸው አምና የነበሩትን 17 ተጫዋቾች የማስቀጠሉ ነገር በእሳቸው አገላለጽ “አደገኛ ቢመስልም” ቡድናቸው ግን ዘንድሮ በሊጉ እንደ ቡድን ተንቀሳቅሶ በሊጉ ቆይታውን እንዲያረጋግጥ እንደሚሰሩ የገለፁ ሲሆን በቀጣይ ዓመት ግን አሰራሩን ሆነ ሌሎች ጉዳዮች ላይ እርምት በማድረግ የክለቡን የቀደመ ክብር እና ዝናው ላይ ለመመለስ መወጠናቸውን ይገልፃሉ።

አያይዘውም በክለቡ በሚኖራቸው ቆይታ ከዚህ ቀደም ከተጫዋችነት ዘመናቸው አንስቶ በሚያውቁት እና ከዚህ ቀደምም በአንድ አጋጣሚ ማሰልጠን የቻሉትን ኢትዮጵያ መድን በአደረጃጀቱም ሆነ በሌሎች እግርኳሳዊ ጉዳዮች ለሌሎች ክለቦች አርዓያ የነበረ ክለብ እንደመሆኑ ቡድኑን ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት እንደሚያደርጉም ይናገራሉ።

ለአዲሱ የውድድር ዘመን ራሱን በዝውውር ለማጠናከር ጥረት ያደረገው ቡድኑ የተወሰኑ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን ለመጨመር ሙከራ አድርጓል። ነገር ግን ክለቡ ከታችኛው ሊግ መምጣቱ እና የክለቡ የቀደመ የዝውውር ባህል ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው አሰልጣኝ ገብረመድህን ይናገራሉ ፤ ” ከታች ከፍተኛ ሊግ የነበረው የደመወዝ መጠን እና ፕሪሚየር ሊጉ ላይ ያለው በጣም የተለያዩ ናቸው። እኛ ልናስፈርም ያሰብናቸውን በሙሉ ከገንዘብ ጋር ተያያዘ እኛ ልናገኛቸው አልቻልንም። ከፍተኛ ብር ነው የጠየቁት ብዙዎቹ ወደ ፋሲል፣ ባህር ዳር ፣ መቻል ወደ ተለያዩ ክለቦች ሲዳማን ጨምሮ ጥለውን ሄደዋል።” የሚል ሀሳብን ያነሳሉ።

በዚህም ቡድኑ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ምርጫዎቹን ለማስፈረም እንደተገደደ እና በዚህም አሁን ላይ በእጃቸው ያሉትን ተጫዋቾች የሚጉድላቸውን በመሙላት ለውድድሩ እየተዘጋጁ እንደሆነም ገልፀዋል። በተጨማሪም እንደ አሰልጣኙ ገለፃ ከሆነ ሦስት የውጪ ተጫዋቾች (በተከላካይ ፣ በተከላካይ አማካይ እና አጥቂ ስፍራ) የማምጣት ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም ለሙከራ ባመጧቸው ተጫዋቾች እምብዛም አመርቂ ነገር ለማየት መቸገራቸው እና እስካሁን አንድ የውጪ ዜግነት ያለው የመሀል ተከላካይ ብቻ ወደ ስብስባቸው ስለመቀላቀላቸው ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ መድኖች በዝውውር መስኮቱ በግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ቡድን አባሉ አቡበከር ኑራን ሲያስፈርሙ ተከላካይ መስመር ላይ ደግሞ ስድስት ተጫዋቾችን መቀላቀል ችለዋል። በዚህም ፀጋሰው ድማሙ ፣ ቴዎድሮስ በቀለ ፣ አብዱልከሪም መሀመድ ፣ ተካልኝ ደጀኔ ፣ ሳሙኤል ዮሐንስን አገልግሎት የሚያገኙ ሲሆን አስጨናቂ ፀጋዬ ፣ ሀብታሙ ሸዋለም እና ዮናስ ገረመው ደግሞ የቡድኑን የመሀል ክፍል ለማጠናከር ስብስቡን የተቀላቀሉት ናቸው ተስፈኞቹ ሀቢብ ከማል እና ብሩክ ሙሉጌታም እንዲሁ ለማጥቃቱ ተጨማሪ አቅም ለመጨመር ነጭ እና ውሀ ሰማያዊዎቹን ተቀላቅለዋል።

ከዚህ ባለፈ ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ካስቻለው ስብስብ በአሰልጣኙ እምነት ከተጣለባቸው ተጫዋቾች መካከል ሰባቱ ውላቸውን አራዝመዋል። ከእነዚህም መካከል ከዚህ ቀደም በሊጉ በወልቂጤ መለያ የምናውቀው ወጣቱ ግብ ጠባቂ ጆርጅ ደስታን ጨምሮ ተከላካዮቹ ቻላቸው መንበሩ እና ፀጋ አለማየሁ ፣ ተስፈኛው አማካይ ቢኒያም ካሳሁን እንዲሁም አጥቂዎቹ ኪቲካ ጅማ ፣ እዮብ ወልደማርያም እና ያሬድ ደርዛ በቀጣይ ዓመታት በክለቡ ለመቆየት ተስማምተዋል።

ቡድኑ ምንም እንኳን በዝውውር መስኮቱ በአሰልጣኙ የሚፈለጉ ተጫዋቾችን ለማግኘት ቢቸገረም ስምንት ያህል ተጫዋቾችን ከዕድሜ እርከን ቡድኖች በማሳደግ ስብስቡን ለማሟላት ጥረት አድርጓል።

ቡድኑ መቀመጫውን በአዳማ በማድረግ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ከነሀሴ 15 ጀምሮ የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅቱን እያደረገ የከረመ ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች ባልተሟሏ ስብስብ ዝግጅታቸውን ከማድረጋቸው ውጭ ጥሩ የዝግጅት ጊዜ ስለማሳለፋቸው አሰልጣኙ ይገልፃሉ። የቡድኑ የቅድመ ውድድር ዘመን ዝግጅት በተለያዩ ምዕራፉች የተከፈለ የነበረ ሲሆን በቅድሚያ በአካል ብቃት እንዲሁም በቀጣይ በነበሩ ምዕራፎች ደግሞ በቴክኒክ እና ታክቲካዊ ጉዳዮች ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል።

አሰልጣኙም በዝግጅት ወቅት በተጫዋቾቻቸው ላይ በመሰረታዊነት በኳስ የማቀበል ሂደት ላይ ያስተዋሉትን ውስንነት ለመቅረፍ በከፍተኛ ትኩረት እየሰሩ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ከኳስ ጋር በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲሁ ጠንካራ ስራዎችን ለመስራት እየሞከሩ መሆኑን እና የቡድን ስራዎች ላይ ያተኮሩ ስራዎችን ለመስራት ግን የተጫዋቾች ጉዳት ችግር እንደሆነባቸው ጠቁመዋል።

በተለይ የቡድኑ የተከላካይ መስመር ክፉኛ በጉዳት የታመሰ ነው። ቡድኑ ይህን ፅሁፍ ስናዘጋጅ በስብስቡ ውስጥ ከተመስገን ተስፋዬ በስተቀር የተቀሩት የተከላካይ ተሰላፊ ተጫዋቾቹ በሙሉ ጉዳት ላይ ይገኛሉ።

አሰልጣኙ የጉዳቱን መጠኑን እና የፈጠረባቸውን ተፅዕኖ ሲያስረዱም “በተለይ የመሐል ተከላካይ ላይ ቴዎድሮስ በቀለ፣ ፀጋሰው ድማሙ፣ ፀጋ አለማየሁ እና ከወጣት ቡድኑ ያደጉ ተጎድተውብናል። ከተከላካይ ቦታ ከምንያዛቸው አምስት ተጫዋቾች አንድ ተመስገን ብቻ ነው የቀረው። አገገሙ ተሻላቸው ስንል ተመልሶ ችግር አጋጥሟቸዋል። እንደነዚህ ያሉ ችግሮች ስለነበሩ ወደ ወዳጅነት ጨዋታ ገብተን ራሳችን አይተን የምናስተካክልበት መንገድ መፍጠር አልቻልንም። ነገር ግን ተጨናንቀንም ቢሆን ማድረግ አለብን በሚል ከ23 ዓመት ቡድን ጋር ለመጫወት ችለናል።” ይላሉ።

ከወዳጅነት ጨዋታዎች ጋር በተያያዘም ቡድኑ ስብስቡ በጉዳት መሳሳቱን ተከትሎ በመዲናዋ ከሚደረገው የከተማ ዋንጫም እንዲሁ ራሱን ለማግለል ወስኖ የነበረ ቢሆንም ውድድሩን ላለማበላሸት በሚል ባልተሟላ ስብስብ ስለመግባት መወሰኑ የተነገረ ሲሆን ከአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫውም በፊት ከኢትዮጵያ 23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጋር ካደረገው ጨዋታ ውጭ ምንም ዓይነት ጨዋታ ሳያደርግ ቀርቷል። ከዚህ አንፃር በከተማዋ ውድድር ላይ ያደረገው ቡድኑ ወደ በስብስቡ የሚገኙ ወጣት ተጫዋቾቹን ለመገምገም በቂ እድል ያገኘ ይመስላል።

ከከፍተኛ ሊግ ወደ ሊጉ እንደተመለሰ ቡድኑ በአዲሱ የውድድር ዘመን ኢትዮጵያ መድን በሊጉ መቆየት ትልቁ ግባቸው መሆኑ አያጠያይቅም። ቡድኑ ወደ ሊጉ ሲያድግ ለኳስ ቁጥጥር አብዝቶ የሚጨነቅ ማራኪ እግርኳስን የሚጫወት ቡድን እንደነበር ይታወሳል። ታድያ የዚህ ስብስብ አካል የነበሩ በርካታ ተጫዋቾች ምንም እንኳን በአዲሱ የውድድር ዘመን በቋሚነት የመጀመራቸው ነገር አጠራጣሪ ቢመስልም በስብስቡ የመቀጠላቸው ነገር አሰልጣኝ ገብረመድህን ከሚመርጡት በቀጥተኛ ቅብብል እና በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የመጫወት እሳቤ አንፃር መድን ሁለቱን የጨዋታ መንገዶች ቀይጦ ሊጫወት ይችላል ተብሎ ይገመታል። ከዚህ ባለፈ ቡድኑ በሊጉ ለመቆየት በሚያደርገው ጥረት ጥሩ አጀማመር አለፍ ሲልም ጥሩ የመጀመሪያ ዙር ማሰለፍ የግድ ይለዋል። ይህ ካልሆነ ግን በሁለተኛው ዙር ሊጉ ከሚኖረው አስቸጋሪ ባህሪ አንፃር ሊቸገር ይችላል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የሊጉ ኮከብ ተጫዋች የነበረው አብዱልከሪም መሀመድ ያለፉት ጥቂት ዓመታት ለእሱ በመልካምነት የሚነሱ አልነበሩም። በመሆኑም የዘንድሮው የውድድር ዘመን የእግር ኳስ ህይወቱን ዳግም ወደ መስመር ለመመለስ እጅግ ወሳኝ ይመስላል። ከዚህ ባለፈም ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በከፍተኛ ሊጉ ከሦስት ተጫዋቾች ጋር በጣምራ ከፍተኛ አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀው ያሬድ ዳርዛ እንዲሁ በፕሪሚየር ሊጉ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴን ያሳዩት ሀቢብ ከማል እና አስጨናቂ ፀጋዬም ዘንድሮ በኢትዮጵያ መድን ቤት የሚጠበቁ ተጫዋቾች ናቸው።

ኢትዮጵያ መድን በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታውን ቅዳሜ መስከረም 21 የዓምና የሊጉን አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመግጠም ይጀምራል።

የኢትዮጵያ መድን የ2015 ቡድን ዝርዝር



ግብ ጠባቂዎች

1 አቡበከር ኑራ
30 ጆርጅ ደስታ

ተከላካዮች

13 ዳንኤል ይሳቅ
5 ቴዎድሮስ በቀለ
15 ፀጋሰው ዴማሙ
16 ተመስገን ተስፋዬ
19 ፀጋ አለማየሁ
2 አብዱልከሪም መሐመድ
14 ቻላቸው መንበሩ
12 ሣሙኤል ዮሐንስ
20 ተካልኝ ደጀኔ
3 ያሬድ ካሳዬ

አማካዮች

7 አሚር ሙደሲር
17 ሀብታሙ ሽዋዓለም
25 አስጨናቂ ፀጋዬ
22 ዮናስ ገረመው
10 ቢኒያም ካሣሁን
8 ብሩክ ሙሉጌታ
11 ሀቢብ ከማል

አጥቂዎች

21 ኪቲካ ጅማ
9 እዮብ ገ/ማርያም
23 ያሬድ ደርዛ

የቡድን አመራር አባላት

ገብረመድህን ኃይሌ – ዋና አሰልጣኝ
ሀሰን በሽር – ረዳት አሰልጣኝ
አንተነህ ላቀው – የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ
የቡድን መሪ – ካሳሁን አንበሴ
አዱኛ ተስፋዬ – ወጌሻ