ወልቂጤ ከተማ የቅሬታ ደብዳቤ ለፌዴሬሽኑ አስገብቷል

ወልቂጤ ከተማዎች በክረምቱ እንዳስፈረሙት የገለፁት ተከላካይ ወደ ባህር ዳር ከተማ ማምራቱን ተከትሎ የቅሬታ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስገብተዋል።

በአሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚመሩት ሠራተኞቹ ዘግየት ብለውም ቢሆን በዝውውር ገበያው በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ማስፈረማቸው ይታወቃል። በምስል በተደገፈ መረጃ እንዳስፈረሟቸው ከገለጿቸው ተጫዋቾች መካከል ደግሞ የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ዳዊት ወርቁ ይገኝበታል። ምንም እንኳን ተጫዋቹ ለወልቂጤ ከተማ ለመጫወት ተስማምቶ ፊርማውን ቢያኖርም ከቀድሞ ክለቡ መከላከያ የተረከበውን መልቀቂያ ሳይሰጥ አዳማ ላይ ሲዘጋጅ ከቆየ በኋላ ሀሳብ በመቀየር መልቀቂያ እና አስፈላጊ ወረቀቶችን ለትውልድ ከተማው ክለብ ባህር ዳር ከተማ በመስጠት ለጣና ሞገዶቹ በይፋ ፊርማውን አኑሯል።

ይህ ጉዳይ ቅር ያሰኛቸው ወልቂጤዎችም ተጫዋቹን ለአንድ ዓመት በማስፈረም በደቡብ ክልል ማፀደቃቸውን በመግለፅ ተጫዋቹ ለ1 ወር ከቡድናቸው ጋር ሲዘጋጅ ቆይቶ ያለ ስምምነት ለባህር ዳር ከተማ በመፈረሙ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስተማሪ ውሳኔ እንዲያስተላልፍ በሚል ደብዳቤ ማስገባታቸውን ለዝግጅት ክፍላችን መረጃ ልከዋል።