የክለቦች የውድድር ዘመን ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ

ከአሠልጣኝ ጀምሮ ስብስባቸውን በአዲስ መልክ ያዋቀሩት ሠራተኞቹ በዘንድሮ ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንደ ቅፅል ስማቸው በርትተው ጠንካራ ፉክክር ለማድረግ ተዘጋጅተዋል።

2012 ላይ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ከፍተኛ የሊግ እርከንን የተቀላቀለው ወልቂጤ ከተማ የመጀመሪያ የሊጉ ተሳትፎ በኮቪድ-19 ምክንያት እንዲሰረዝ ከተደረገ በኋላ 2013 ላይ ወደ መጣበት ከፍተኛ ሊግ የመውረድ እጣ ፈንታ አጋጥሞት ነበር። ነገርግን የትግራይ ክልል ክለቦችን ለመተካት ሀዋሳ ላይ በተደረገ የማሟያ ውድድር ዳግም በሊጉ መክረሙን አረጋግጦ የ2014 የውድድር ዓመትን በአሠልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው እየተመራ ቀርቧል። ክለቡን በሊጉ ያከረሙት አሠልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው ግን በድሬዳዋ ስታዲየም በ12ኛ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ ከደረሰባቸው የ4ለ0 ሽንፈት በኋላ መቀጠል አልቻሉም ነበር። በምትካቸው የመጡት አሠልጣኝ ተመስገን ዳና ደግሞ የመጀመሪያ ጨዋታዎቹን ያለ ረዳት ከዛም ከቆይታ በኋላ ከረዳታቸው ነፃነት ክብሬ ጋር በመሆን ቀሪዎቹን የሊግ መርሐ-ግብሮች ቡድኑን ይዘው ቀጥለዋል።

በወጥነት ወጥ ብቃት እና ውጤት ማሳየት ተስኖት የ2014 የውድድር ዓመትን የፈፀመው ወልቂጤ ከተማ እስከ መጨረሻዎቹ የሊጉ ጨዋታዎች ድረስ የመውረድ ስጋት ነበረበት። በውድድር ዓመቱም አንድም ጊዜ ተከታታይ ሦስት ጨዋታዎችን ማሸነፍ ሳይችል በአጠቃላይ በ30 ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 90 ነጥቦች ዘጠኙን በማሸነፍ በአስራ አንዱ አቻ በመውጣት ቀሪዎቹን አስር ፍልሚያዎች ተረቶ 38 ነጥቦችን በመያዝ የሊጉን ደረጃ ሰንጠረዥ አካፋይ ቦታ በመያዝ ውድድሩን አገባዷል።

ወልቂጤ ገና ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሦስተኛ ዋና አሠልጣኙን ከሳምንታት በፊት ሾሟል። በሊጉ እንዲተርፍ ያደረጉትን አሠልጣኝ ተመስገን ዳና በኢትዮጵያ ቡና የተነጠቀው ክለቡም ከሌሎቹ ክለቦች ዘግየት ብሎ በመንበሩ አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን ቀጥሯል። አሠልጣኙ ሹመቱን ካገኙ በኋላ ዘነበ ፍሰሀን በረዳትነት ሳዳት ጀማልን ደግሞ በግብ ጠባቂ አሠልጣኝነት ወደ ስብስቡ አምጥተው የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ቢጀምሩም አሠልጣኝ ዘነበ ከጥቅማ ጥቅም ጋር በተያያዘ ሳይስማሙ ውስን ልምምዶች ላይ ካሰሩ በኋላ ከክለቡ ጋር ተለያይተዋል። ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስም አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ያለ ረዳት ከግብ ዘቦቹ አሠልጣኝ ሳዳት ጋር ብቻ በመሆን ቡድኑን እየመሩ ይገኛሉ።

በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ዘግየት ብሎ ወደ ዝውውር ገበያው ጎራ ያለው ክለቡ በአጠቃላይ 17 ተጫዋቾችን አስፈርሟል። አብዛኞቹ ተጫዋቾች ግን በአሠልጣኙ ምርጫ የፈረሙ አለመሆኑ ልብ ይሏል። የሚሾመው አሠልጣኝ የአጨዋወት ባህሪ እና የሚፈልጋቸው ተጫዋቾች አይነት ሳይታወቅ በዝውውር ላይ መሳተፉ ነገርየውን ‘ከፈረሱ ጋሪው ቀደመ’ ቢያስብለውም አሠልጣኙ ይህንን በተመለከተ “ክለቡ አስቀድሞ አሠልጣኝ ባይኖርም ተጫዋቾቹን ይዟል ፤ እነዛን ተጫዋቾች ደግሞ እኔ አይቼ ማረጋገጥ ነበረብኝና በአብዛኛው እንደዛ ነው የሠራነው።” ሲሉ ይደመጣሉ።

ከበጀት ጋር በተያያዘም ችግሮች እንዳሉበት የሚሰማው ክለቡ በኪሱ ልክ አስቤዛ ለማድረግ ጥሯል። እንደ አብዛኞቹ ክለቦች ውድ ውድ የሚባሉ ተጫዋቾችን ለመሻማት ባይሞክርም አሠልጣኙ “እኛ ጋር ውስን በጀት ነው ያለው ፤ ተጫዋቾች በአሁን ሰዓት የሚጠይቁህን ገንዘብ ለማሟላት ከባድ ነው። ውስን በጀት ስላለው ክለቡ የሚይዛቸው ተጫዋቾች በዛን ያህል ውስን የሆኑትን ነው። ካለህ በጀት አኳያ ነው ቡድን የምትመሠርተው።” እንዳሉት በተመጠነ በጀት ስብስቡን ለማዋቀር ጥሯል።

በ2014 የመጀመሪያው የውድድር ዓመይ አይቮሪያዊውን የግብ ዘብ ሲልቪያን ግቦሆ በእግድ ምክንያት ያጣው ክለቡ ዓመቱን ሲዒድ ሀብታሙ እና ሮበርት ኦዶንካራን እያፈራረቀ የተጠቀመ ሲሆን በክረምቱ ግን ከአዳማ ከተማ ጋር ሰዒድን በጀማል ጣሰው ተለዋውጧል። ወደ ቀድሞ ክለቡ የተመለሰው ጀማልም አሠልጣኙ ለሚከተሉት የኳስ ቁጥጥር ትልቅ መነሻ የሚሆን ሲሆን ከሮበርት ጋርም የሚያደርገው ፉክክር የሚጠበቅ ይሆናል። በኢትዮጵያ እግርኳስ ከታዩ ድንቅ ግብ ጠባቂዎች መካከል አንዱ የነበሩት ሳዳት ጀማል ደግሞ የእነርሱ አሠልጣኝ መሆናቸው በቦታው ጥንካሬ እንዲኖር ያደርጋል ተብሎ ይታሰባል።

በተከላካይ እና አማካይ ቦታ ላይ ግን ከአምናው ስብስብ በርከት ያሉ ተጫዋቾች ተለውጠዋል። ዓምና በተከላካይ ክፍሉ በቋሚነት ከሚያገለግሉት ተጫዋቾች መካከል ረመዳን የሱፍ፣ ዳግም ንጉሴ እና ተስፋዬ ነጋሽን ያጣ ሲሆን በምትካቸው ቴዎድሮስ ሀሙ፣ ብርሃኑ ቦጋለ፣ ሳሙኤል አስፈሪ፣ ተስፋዬ መላኩ እና አዲስዓለም ተስፋዬን አምጥቷል። የእነዚህ ተጫዋቾች ጥራት በወጡት ልክ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ክርክር እንዳለ ሆኖ በአንድ የዝውውር መስኮት የቡድኑን መሰረቶች ማጣት የሚያመጣው መናጋት ግን አስጊ ነው። በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ውድድር ላይ ግን የታየው የተከላካይ መስመር በጥሩ ቅኝት እየተገነባ ይመስላል። በሜዳው የመሐል ክፍል ላይም ዋነኞቹን ሀብታሙ ሸዋለም፣ አብዱልከሪም ወርቁ፣ በኃይሉ ተሻገር እና ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስን ቢያጣም ከአንጋፋው አስራት መገርሳ እስከ ወጣቶቹ አፈወርቅ ኃይሉ፣ ብዙዓየሁ ሰይፉ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ እና ማቲያስ ወልደአረጋይ ድረስ በስብስቡ ይዟል። ይህ የአማካይ ክፍልም ጨዋታን በመቆጣጠር የሚታማ ባይሆኑም በቅርብ ጊዜ በሊጉ ከሳምንት ሳምንት ያልተመለከትናቸው በመሆኑ መጠነኛ ፈተና ሊሆን እንደሚችል ሊገመት ይችላል።

ፊት መስመር ላይ ግን የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ማገር በሆነው ጌታነህ ከበደ ላይ የተገነባ በመሆኑ ስብስቡን የለቀቁት እነ ጫላ ተሺታ ያን ያህል ማጣት ያስከስታሉ ተብሎ አይጠበቅም። በእነርሱ ምትክም እነ ተመስገን በጅሮንድ እና የኋላሸት ሰለሞን አማራጭ እንደሚሆኑም ይገመታል።

ከአምናው ስብስብ ስድስት ተጫዋቾችን ብቻ በስብስቡ አስቀርቶ ወደ አዲስ የቡድን ግንባታ ያመራው ወልቂጤ ዘግይቶ ወደ አሠልጣኝ ቅጥር እና ዝውውር መግባቱ መጠነኛ ችግር እንዳይፈጠርበት ያሰጋል። በተጨማሪም ያገኟቸው ተጫዋቾች ጥራት ነገርየው በጥርጣሬ እንዲታይ ያደርገዋል። አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ግን “ችግሩን እኛ እንቀርፋለን ብለን የምናስበው በተጫዋቾች የመጫወት ፍላጎት ነው። ዋናው እግርኳስ ውስጥ የሚፈለገው ብዙ ስም ስላላቸው ስለሌላቸው አይደለም ፤ የመጫወት ፍላጎታቸው ከፍ ያሉ ተጫዋቾች ናቸው እኛ ቡድን ውስጥ ያሉት። ያ ነው በጣና ካፕ ውድድሩ ላይም የታየውና በዛ እናካክሰዋለን ብዬ አስባለሁ። እንጂ በርካታ ችግሮች ነበሩበት። አሰልጣኝ ዘግይተው ነው የቀጠሩት ስለዚህ እነዚህ ችግሮች አሉ ግን ችግሮቹን ለማቅለል ነው የምንሠራው።” የሚል ሀሳብ አላቸው።

ሀሳባዊው አሠልጣኝ ከቡድን ውህደት ጋር በተያያዘ ግን የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን የሰሩበት ጊዜ በቂ እንዳልነበር በማንሳት ውድድር ላይ ቢሆንም ቡድኑን እየገነቡ እንደሚሄዱ ያወሳሉ። “ከባድ ነው። እኛ የሠራነው አሁን አንድ ወራችን ነው። በዓል የሄዱበትን ጊዜ ስናስበው አንድ ወርም አይሞላውም በጥቅሉ። የዝግጅት ወቅታችን ለማከናወን ወደ አዳማ ስናቀናም አካባቢው ዝናባማ ነበርና የጠዋት እና የከሰዓት ፕሮግራምም ሙሉ መሥራት አልቻልንም። እነዚህ ተደማምረው ቡድናችን በአንድ ጊዜ ይዋሃዳል ብለን አናስብም ግን በጨዋታው ሂደት ይሻሻላል። ለዚህም ነው የጣና ዋንጫን የፈለግነው። ወደዚህም ስንመጣ ባህር ዳር ላይ አራት ጨዋታ ለመጫወት ነው ፤ እዛም እንድ ሦስት ጨዋታዎች አድርገን ነበርና እነዚህ ጨዋታዎች ቢያንስ ተጫዋቾች የሚጫወቱበት ቦታና አብረው ከሚጫወቱት ተጫዋቾች ጋር ምን ያህል ውህደት አላቸው ለማለት ያስችለናል። አሁን እንደጀመርንም ጥሩ ነገር ላይመጣ ይችላል። እንደፈለግነው ላይሆን ይችላል ፤ ነገር ግን ሁልጊዜ ቡድን በየቀኑ በሂደት ነው እየተገነባ የሚሄደው። ከስምንት ወይ ከዘጠኝ ጨዋታ በኋላ የቡድንህን ቅርጽ የምታየውና ያን እንጠብቃለን።”

ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በተዘጋጀው የአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ ላይ ተሳትፎ ታሪካዊውን ዋንጫ የግሉ ያደረገው ቡድኑ ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ክለቦች ጋር ተፋልሞ በጨዋታ ሁለት ሁለት ጎሎችን በአራቱ ጨዋታዎች በአማካይ አስቆጥሮ በተቃራኒው ሁለት ጊዜ ብቻ ግቡን አስደፍሯል። በጨዋታዎቹም የተለያዩ ተጫዋቾችን በመጠቀም አሠልጣኙ ከላይ ያሉትን የቡድን ውህደት እና የተጫዋቾች ሚና ለማየት ተሞክሯል። ይህንን ውድድር እንደ መስታወት እንደሚጠቀሙበት የሚናገሩት አሠልጣኙ ዋንጫ ከማምጣታቸው ባለፈ ብዙ ስህተቶችን ቡድናቸው ላይ እንዳዩ ይመሰክራሉ። “ለእኛ ይህ ውድድር ማያ ነው። እንደውም ብዙ ስህተቶችን አይተናል ፤ መጫወታችን ይሄንን ነው የጠቀመን። አሁን ለቀጣይ ጨዋታ እነዛን ስህተቶች የምናርምበት እንጂ ያን ዋንጫ አገኘን አላገኘን ለእኛ የሚያመጣልን ምንም ነገር የለም። በተጫዋቾቼም ላይ የብቃት ለውጥ አያመጣም። ተጫዋቾቼም ደግሞ በሚገባ ያ ዋንጫ እዛው ጋር መቅረቱን ይረዳሉ ብዬ አስባለሁ። ለቀጣይ ጨዋታ አዲስ አስተሳሰብ ይዘን ነው የምንቀርበው።”

ሠራተኞቹ ነሐሴ 13 ተሰባስበው ወደ አዳማ ከተማ በማምራት የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ጀምረዋል። እርግጥ በ13 ወደ ስፍራው ቢያቀኑም የመጀመሪያዎቹን ሦስት ቀናት ክለቡ የያዛቸው ተጫዋቾችን አሠልጣኝ እንዲያዩ ተደርጎ የሚፈለጉት እና የማይፈለጉት ከተለዩ በኋላ ነው መደበኛው የቅድመ ውድድር ዝግጅት ነሐሴ 16 የተጀመረው። አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራም በቅድመ ውድድር ጊዜያቸው ትኩረት ሰጥተው የሰሩበትን መንገድ እንደዚህ ይገልፁታል። “ሁሉም ክፍል ላይ ዝግጅት አድርገናል። ምክንያቱም ይሄ አዲስ ቡድን ነው። ተጫዋቾች አዲስ ስለሆኑ ባላቸው ነገር ላይ ለመጨመር መጀመሪያ የአካል ብቃታቸው መስተካከል አለበት። ይሄም የአካል ብቃትም ከቴክኒክ ጋር አብሮ ነው ፤ እኔ ጋር ሁሉም የአካል ብቃት ልምምዶች በኳስ ናቸው። እናም የአካል ብቃቱን ከቴክኒክ ጋር አብረው እንዲያዳብሩት ነው ያደረግነው።”

ከዚህ የመጀመሪያ ትኩረታቸው በመቀጠል ደግሞ በዚህ ዓመት የቡድኑ የአጨዋወት ዘይቤ ምን መምሰል አለበት የሚለውን መለየት ላይ እንደተጠመዱ ይናገራሉ። የቡድኑን እና የተጫዋቾችን የአጨዋወት መንገድ ከራሳቸው ዘይቤ ጋር በማድረግ ቡድኑን ተፎካካሪ ለማድረግ ከተከላካይ እስከ አጥቂ ክፍሉ ከጨዋታ መንገድ ጋር ተያይዞ ሥራዎችን እንደሰሩ ያመላክታሉ። ይህ ቢሆንም ግን የቡድኑ አጨዋወት የሚመሠረተው በተጫዋቾች እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተው ይናገራሉ። “የቡድን አጨዋወት የሚመሠረተው በተጫዋቾች ጥገኝነት ላይ ነው። አሰልጣኝ የራሱ ሀሳብ ስላለው ብቻ አይደለም ፤ አሰልጣኝ የራሱን ሀሳብ ይዞ ወደ ተጫዋቾች ለመምጣት እና ወደዛ ለማውረድ የተጫዋቾች የመቀበል ብቃት ይጠይቃል። ስለዚህ እኔ እነሱ ባላቸው ነገር ነው ቡድኑን የመሠረትኩት ፤ እንጂ የእኔን አስተሳሰብ እነሱ ላይ ሁሉንም አልጭንባቸውም። የተሻለ ጨዋታ ይታያል ፤ የራሱ አጨዋወት ያለው ቡድን ግን ልታዩ ትችላላችሁ ብዬ አስባለሁ።”

ወልቂጤ ከተማ ዓምና የማጥቃት አጨዋወቱ እጅግ አንድ ተጫዋች ላይ ጥገኛ ነበር። ጌታነህ ከበደ! ጎል አነፍናፊው አጥቂ በ2014 የውድድር ዓመት ለክለቡ 14 ግቦችን ማስቆጠሩ ጥሩ ሆኖ ሳለ እርሱ በሌለባቸው ጨዋታዎች ግን ቡድኑ ግብ ለማግኘት ሲቸገር አስተውለናል። እርግጥ ጫለ ተሺታ 8 ግቦችን ቢያስቆጥርም ሌላ ጫናውን የሚጋራ የግብ ምንጭ ግን ቡድኑ አልነበረውም። በአጨዋወት ረገድ ራሱ የቡድኑ ማጥቃት መዓከል ያደረገው ጌታነህ ከበደን ስለነበር ተጋጣሚዎች የማጥቃት ጥቃቶችን ገምተው ለመከላለል አይቸገሩም ነበር። ምናልባት በአማራ ባንክ ጣና ዋንጫ እንደታየው ከሆነ ግን ቡድኑ ያለ ጌታነህም ግብ ማስቆጠር እየቻለ ነው። ይህ ተጠናክሮ የሚመጣ ከሆነ የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት እንዳይገመትም ሆነ ተጫዋቹ ላይ ጫና እንዳይፈጠር ትልቅ ጥቅም አለው።

ባለፉት ሁለት ዓመታት የወልቂጤ ዋነኛ ጠንካራ ጎኖች የመስመር ተከላካዮቹ ረመዳን የሱፍ እና ተስፋዬ ነጋሽ ነበሩ። የማጥቃት ፍላጎት እና ብርታት ያላቸው ፈጣኖቹ የመስመር ተከላካዮች በበርካታ ጨዋታዎች የተጋጣሚ የራስ ምታት ሲሆኑ ያስተዋልን ሲሆን በዘንድሮ የውድድር ዘመን ግን በቅደም ተከተል ሊጉን አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው ባጠናቀቁት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ፋሲል ከነማ መለያ ነው የምንመለከታቸው። ቡድኑ እነርሱን ለመተካት ያደረገው ጥረት እምብዛም አጥጋቢ ባይሆንም በቀኝ መስመር ላይ የፈረመው ሳሙኤል አስፈሪ ግን ምናልባት ቦታውን በሚገባ ሊያበረታ እንደሚችል ይታሰባል። በአዲስ አበባ ከተማ ያሳለፈውን የውድድር ዓመት የተጫወተው ጉልበታሙ የመሐል እንዲሁም የመስመር ተከላካይ በጣና ዋንጫ ላይ ሁሉንም ጨዋታዎች ተጫውቶ ያሳየው ብቃት ድንቅ ነበር። ባሳየው ብቃትም የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ክብርን አግኝቷል። በተቃራኒ መስመር ግን በሊጉ ከተጫወተ ትንሽ ቆየት ያለው ብርሃኑ ቦጋለ መጥቷል። ተጫዋቹ ከሊጉ ከመራቁ፣ ከእድሜ፣ ከጉዳት እና ከጨዋታ ፊትነስ ጋር ያሉ ጥያቄዎችን እንዴት ይመልሳል የሚለው ጉዳይ ደግሞ የሚጠበቅ ይሆናል።

ከምንም በላይ ግን መነሳት ያለበት ጉዳይ ቡድኑ ወደ ሊጉ ከመጣ በኋላ ላለመውረድ መፍጨርጨርን ከአንድም ሁለቴ መተግበሩ ነው። ካለው አዲስ የቡድን ግንባታ አንፃር ምናልባት ቡድኑ ዘንድሮም ሊቸገር ይችላል የሚሉ ሀሳቦች በብዙሃኑ ዘንድ ቢኖርም አሠልጣኙ ግን ዘንድሮ ይሄ ስጋት አይሆንብንም ሲሉ ይደመጣሉ። “እንደሱ ዓይነት ስጋት ይገባናል ብለን አናስብም። ምክንያቱም መጀመሪያ ነው መዘጋጀት ያለብን። ስለዚህ ከመጀመሪያው ጨዋታ ጀምረን ተዘጋጅተን የተሻለ ነጥብ እንይዛለን ብዬ አምናለሁ። ይሄንን ደግሞ ተጫዋቾቼ ያደርጉታል የሚል እምነት አለኝ።”

ከነባሮቹም ሆነ ከአዳዲስ ተጫዋቾቹ ከነገ በስትያ በሚጀመረው የ2015 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በቡድኑ ውስጥ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ተብሎ የሚጠበቁ ተጫዋቾች አሉ። ከነባሮቹ ያለ ጥርጥር አምበሉ ጌታነህ ከበደ በላይኛው የፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ተፅዕኖ ፈጣሪነቱ እንደሚቀጥል እሙን ነው። በራስ ሳጥን ደግሞ ውሳኔ ለመወሰን ጊዜ የማያጠፋው ውሃብ አዳምስ ከአዲስ ፈራሚው ቴዎድሮስ ሀሙ ጋር የሚያደርጉት ጥምረት ለቡድኑ ትልቅ ግድግዳ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል። ከላይ እንደገለፅነውም ሳሙኤል አስፈሪ በመስመር እንዲሁም በመሐል ተከላካይ አማራጭ ለቡድኑ ጥሩ ግብዓት እንደሚሰጥ ይታመናል።

ወልቂጤ ከተማ የ2015 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታውን በመክፈቻው ቀን ከአርባምንጭ ከተማ ጋር የሚያደርግ ይሆናል።

የ2015 የወልቂጤ ከተማ ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

1 ጀማል ጣሰው
44 ሮበርት ኦዶንካራ
22 ፋሪስ አለዊ

ተከላካዮች

24 ውሃብ አዳምስ
66 ሳሙኤል አስፈሪ
10 ብርሃኑ ቦጋለ
6 አዲስዓለም ተስፋዬ
4 ቴዎድሮስ ሀሙ
15 ተስፋዬ መላኩ
17 ፍፁም ግርማ

አማካዮች

27 አፈወርቅ ኃይሉ
18 ፋሲል አበባየሁ
5 ማቲያስ ወልደአረጋይ
8 አሥራት መገርሣ
14 ብዙዓየሁ ሰይፉ
3 ኤፍሬም ዘካርያስ
አጥቂዎች

19 የኋላሸት ሰለሞን
9 ጌታነህ ከበደ
16 ተመስገን በጅሮንድ
21 አቤል ነጋሽ
7 አንዋር ዱላ
11 አቡበከር ሳኒ

የአሠልጣኝ ቡድን አባላት

ዋና አሠልጣኝ – ገብረክርስቶስ ቢራራ
ምክትል አሠልጣኝ – ዳዊት ሀብታሙ
የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ – ሳዳት ጀማል
የህክምና ባለሙያ – ታምሩ ናሳ
የቡድን መሪ – ጌታቸው ታደመ