የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ

ያለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት ለአዳማ ከተማዎች እምብዛም ለማስታወስ የሚፈልጓቸው እንዳልነበሩ መናገር ይቻላል ፤ ዘንድሮ ይህን ሂደት ለመቀልበስ በቀድሞው ኮከባቸው እየተመሩ ውድድሩን በተስፋ ይጀምራሉ። እኛም ዝግጅታቸው ምን ይመስላል ስንል ተከታዩን ፅሁፍ አሰናድተናል።

በ2014 የውድድር ዘመን አዳማ ከተማዎች ከተወሰኑ ጨዋታዎች በስተቀር በአመዛኙ ጨዋታዎች ከተጋጣሚዎቻቸው በተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም ከጨዋታዎች ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው ለመውጣት መቸገራቸው ሳይጠበቁ ራሳቸውን ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ እንዲያገኙ ብሎም በሊጉ ቆይታቸውን ለማረጋገጥ እስከ 29ኛው ሳምንት ድረስ መጠበቅ ግድ እንዲላቸው አስገድዷል። በ35 ነጥቦች ከወራጅ ቀጠናው በሦስት ነጥቦች ከፍ ብሎ ሊጉን በ11ኛ ደረጃ የፈፀመው ቡድን ብዙ በተጠበቀበት የውድድር ዘመን በዚህ ደረጃ ዓመቱን መፈፀሙ ብዙዎችን ያስገረመ ነበር።

በሁለት አሰልጣኞች የውድድር ዘመኑን ያጠናቀቀው ቡድኑ በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ መሪነት እስከ 24ኛ ሳምንት እንዲሁም ቀሪዎቹን 6 የጨዋታ ሳምንታት ደግሞ በጊዜያዊት የቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ በነበረው ይታገሱ እንዳለ ነበር ዓመቱን የተቋጩት። በይታገሱ እንዳለ ስር ተስፋ ሰጪ ነገር የተመለከቱት የክለቡ አመራሮች አሰልጣኙን በቋሚነት በማስቀጠል ነበር ክረምቱን የጀመሩት።

የቀድሞው የአዳማ ከተማ አስደናቂ አማካይ ወደ ሥልጠናው ፊቱን ካዞረ ወዲህ በአዳማ ከተማ የዕድሜ እርከን ቡድኖች ሥልጠናን አሀዱ ብሎ የጀመረ ሲሆን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ደግሞ ራሱን ይበልጥ ለማጎልበት ከተለያዩ አሰልጣኞች ስር ሲማር የቆየ ቆይቷል። አሁን ላይ ደግሞ ራሱን በትልቁ በከፍተኛው የሊግ እርከን የሚያሳይበትን እድል ያገኘ ይመስላል። ባለፈው የውድድር ዘመን ቡድኑ ከነበረበት ሁኔታ እና ኃላፊነቱንም የተረከበበት ወቅት የራሱን ሀሳብ ሜዳ ላይ ለመመልከት እምብዛም የተመቸ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ግን በትልቁ ራሱን የሚያሳይበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በተጨማሪም ላለፉት ዓመታት በገላን ከተማ ሲሰራ የምናውቀው ወጣቱ አሰልጣኝ ተረፋ ሂርጳሳ ደግሞ የአሰልጣኝ ይታገሱ ረዳት በመሆን እንዲሁ የአሰልጣኝ ቡድኑን ተቀላቅለዋል።

በ2005 የውድድር ዘመን ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የተመለሱት አዳማ ከተማዎች በተለይ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ መሪነት ወጣቶችን ከአንጋፋዎች ባጣመረው የወቅቱ ስብስብ በሰንጠረዡ አናት ጥሩ ተፎካካሪ የነበሩ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ዓመታት ግን ነገሮች ጥሩ አልሆኑላቸውም ። በ2013 ከሊጉ ከተሰናበቱ በኋላ በተገኘ ዕድል በሊጉ ለከርሞ መካፈላቸውን ሲያረጋግጡ በ2014ም እንዲሁ አስጨናቂ ጊዜን ማሳለፋቸው ብዙሀኑን የክለቡን ደጋፊ ስጋት ውስጥ የከተተ ነበር። አሰልጣኝ ይታገሱ ግን ይህ ሂደት በአዲሱ ዓመት አይኖርም ይላሉ ፤ “በእርግጠኝነት ልናገር የምችለው ያለፈው ዓመት ፈተና አይገጥመንም። ያለፈው ዓመት የነበሩ ችግሮች አሉ ከእነሱ በመነሳት ነው የምትሰራው እና እነዛን ነገሮች አርመህ ነው የምትመጣው ከውድድሩ በፊት። ከዛ አንጻር የተሻለ ቡድን ይኖረናል ብዬ አስባለሁ።” ሲል ለክለቡ ደጋፊዎች ማረጋገጫውን ሰጥቷል።

ከሌሎች ክለቦች አንፃር እጅግ ዘግይተው ወደ ዝውውር ገበያው የገቡት አዳማ ከተማዎች በትልቅ ደረጃ የሚጠቀሱ ዝውውሮችን በስፋት ሲፈፅሙ አልተመለከትንም። አማካይ ስፍራ ላይ ለቡድኑ መሪነትን ሆነ እርጋታን እንደሚያላብስ የሚጠበቀው መስዑድ መሀመድን ከጅማ አባ ጅፋር ያስፈረሙ ሲሆን ተስፈኛው ዊልያም ሰለሞንም እንዲሁ አወዛጋቢ ከነበረ ሂደት በኋላ ወደ አዳማ ያደረገው ዝውውር ርዕሰ ዜና የሚፈጥሩት ዝውውሮች ናቸው ብለን ማንሳት እንችላለን።

“እንደ ቡድን ገና ነው ፤ ችግር ተፈጥሮብኛል የምትለው ጨዋታ ላይ ባለው ነገር ነው። ዝውውር ላይ ያመለጡን ተጫዋቾች አሉ ፤ አራት እና አምስት የሚሆኑ ልጆች አምልጠውናል። ይህም ቢሆን ግን ቡድኑ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራሉ ብዬ አላስብም። ቢመጡ እንጠቀምባቸው ነበር ፤ አሁን ያዘዋወርናቸው ልጆች በጣም ጥሩ ናቸው። የሚቀጥለው ዓመት የተሻለ ቡድን ይኖረናል።” አሰልጣኝ ይታገሱ ዘግይተው ወደ ዝውውር መግባታቸው ስለሚፈጥረው ተፅዕኖ የሰጡን ቃል ነበር።

ከዚህ ባለፈ በግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በወልቂጤ ከተማ ጥሩ ጊዜያትን ያሳለፈውን ሰዒድ ሀብታሙ እና ከጋና ያስመጡት ክዋሜ ባህ የሚፋለሙ ሲሆን ባለፈው ዓመት ከሊጉ በወረደው ጅማ አባ ጅፋር በተለይ በሁለተኛው ዙር ጥሩ ብቃታቸውን ያሳዩት አድናን ረሻድ እና ቦና ዓሊን ጨምሮ ጋናዊው አማካይ ፍሬድሪክ አንሳህ ሌሎች ተጠቃሽ ዝውውሮች ናቸው። ከዚህ ባለፈ ከአርሲ ነገሌ እና የኢትዮጵያ ቡና የዕድሜ እርከን ቡድን የተገኙትን ታዬ ጋሻው እና ኤልያስ ለገሰን ጨምሮ ቡድኑ አምስት ተጫዋቾች ከዕድሜ እርከን ቡድኑ አሳድጓል። በአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ይሁንታ አግኝተው ወደ ዋናው ቡድን ያደጉት በተከላካይ መስመር ላይ አብዲ ዋበላ እና ፉአድ ኢብራሂም እንዲሁም በአማካይ ስፍራ ደግሞ ጋዲሳ ዋዶ እና ሳዲቅ ዳሪ ሲሆኑ ፊት መስመር ላይ ደግሞ አብዱልፈታህ ሰፋህ ናቸው።

አሰልጣኙ ስለነዚህ አዳጊ ተጫዋቾች ሲናገሩም ፤ “አምስት ልጆች አሳድገናል። ባለፈው ዓመት ደግሞ ስድስት ልጆች ነበሩ። እነሱን በሂደት ነው ለመጠቀም ያሰብነው። ከዋናው ቡድን ጋር አብረው በመሥራታቸው ከቀን ወደ ቀን ለውጥ እየተመለከትንባቸው እንገኛለን እንደ ቡድን ታዳጊዎች ላይ ትኩረት አድርገን እንሠራለን ብለን እናስባለን።” ይላሉ።

አሰልጣኝ ይታገሱ ስለቡድኑ የዝውውር ዒላማዎች እና አጠቃላይ በገበያው ስለነበራቸው ቆይታ ሲያነሱ የገበያው ንረት ተግዳሮት እንደፈጠረባቸው አልሸሸጉም ፤ ” ዓምና የተቸገርንበት ቦታ የመሃል ክፍሉ ነበር። ለዚህም ይረዳን ዘንድ ይህን ክፍል ለማሻሻል ተጫዋቾችን ያስፈረምነው። መሃል ክፍሉ ላይ በትኩረት እየሠራን እንገኛለን። በዝውውር መስኮቱ ያመለጡን ልጆች አሉ። በዋነኝነት በገንዘብ ምክንያት ልጆች አጥተናል ፤ የጠሩት ብርና እኛ እንደ ቡድን ያስቀመጥነው ነገር የሚጣጣም አልነበረም ከሞላ ጎደል የምንፈልጋቸውን ተጫዋቾች በተለይ መሀል ሜዳ ላይ አምጥተናል ማለት ይቻላል።”

ወደ ዝውውር ገበያው ዘግይቶ ስለመግባቱ ያነሳነው አዳማ ከተማ በተመሳሳይ ወደ ባቱ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ለማድረግ ያመራውም ከሌሎች ክለቦች እጅግ ዘግይቶ ነበር። አብዛኞቹ ቡድኖች በነሀሴ የመጀመሪያዎቹ ቀናት ዝግጅታቸውን ቢጀምሩም አዳማ ከተማዎች በአንዳንድ ቅድመ ሁኔታዎች አለመሟላት በተደራጀ መልኩ ወደ እንቅስቃሴ የገቡት በነሀሴ 23 መሆኑ በአሰልጣኝ ይታገሱ ዕቅዶች ላይ የተወሰነ መፋለሶችን የፈጠረ ሆኗል። አሰልጣኙ ቡድናቸውን ለመፈተሽ በከተማ ዋንጫዎች ላይ የመሳተፍ ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም ወደ ዝግጅት ዘግይተው በመግባታቸው ያለ በቂ ጊዜ ወደ እነዚህ ውድድሮች መግባት ተሳተፍን ከማለት ውጭ ለቡድኑ የሚያስገው ጥቅም ሊኖረው እንደማይችል በማመን አለመሳተፍን ምርጫቸውን ማድረጋቸውን ሲገልፁ ከዚህ መነሻነት ግን ሌሎች አማራጮችን ስለመውሰዳቸው ያስረዱት አሰልጣኙ በራሳቸው መንገድ ከሊጉ ተሳታፊዎች ጋር ስድስት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ማድረግ የቻሉ ሲሆን በእነዚህ ጨዋታዎችም ቀሪ የቤት ሥራዎቻቸውን በሚገባ ተመልክተዋል ተብሎ ይገመታል።

በመጨረሻም በአዲሱ የውድድር ዘመን ቡድናቸው ሊከተለው ስላሰበው የጨዋታ መንገድ ሀሳባቸውን የሰጡት አሰልጣኙ ይህን ብለዋል ፤ “በአጨዋወት ረገድ ሁኔታዎች ሜዳ ላይ በሚፈጠሩ ነገሮች የሚወሰኑ ናቸው። ነገር ግን የእኔ ቡድን ኳስን አንሸራሽሮ በኳስ ቁጥጥር በልጦ የሚጫወት ቡድን ይኖረናል ብዬ አስባለሁ።” ይላሉ።

በ2014 የውድድር ዘመን ካደረጋቸው 30 ጨዋታዎች ውስጥ ከግማሽ የሚልቁትን ጨዋታዎች በአቻ ውጤት የፈፀመው ቡድኑ በአጠቃላይ ያስቆጠሩትም የግብ ብዛትም 24 ማለትም በጨዋታ በአማካይ ከአንድ ግብ በታች መሆኑ ስለ አዳማ ከተማ የአዲሱ የውድድር ዘመን ተቀዳሚ ዕቅዶች በሚገባ ይነግሩናል። በመሰረታዊነት ቡድኑ ኳስ የመያዝ ፍላጎት ያለው ቢመስልም የኳስ ቁጥጥሩን ወደ ግብ ዕድሎች በመቀየር ረገድ ሰፊ ውስንነት እንዳለበት ተመልክተናል። በመሆኑም መስዑድ መሀመድ እና ዊልያን ሰለሞንን የጨመረው ቡድኑ የኳስ ቁጥጥሩን ወደ በቂ የግብ ዕድሎች በመቀየር ረገድ የተሻሻለ የውድድር ዘመን ማሳለፍ የሚኖርበት ይሆናል። ከዚህ ባለፈም አምና በመሀል ሜዳ ተጫዋቾች ስም የተመዘገቡ ግቦች ቁጥር ብዛት 2 የመሆኑ ነገር አማካይ ክፍሉ በግቦች ላይ ያለው ተሳትፎም እንዲሁ ከፍ ማለት እንዳለበት ጠቋሚ ሲሆን አምና ለቡድኑ ብዙ ዕድሎችን የፈጠረው የመስመር ተከላካዩ ደስታ ዮሐንስ እንዲሁ ይጠበቃል።

ዕድሎች የሚፈጠሩ ከሆነ ደግሞ በዛው ልክ የመጨረስ አቅምም ወሳኝ ድርሻ አለው። በዚህኛው ዓመት የአዳማ የአጥቂ መስመር ይበልጥ ስል መሆን ሌላው የትኩረት አቅጣጫ ነው። ዕድሎችን መፍጠር ያለ እርጋታ የተላበሰ አጨራረስ ትርጉም አልባ እንደመሆኑ የአዳማ አጥቂዎች ከአምና በተሻለ ዕድሎችን ወደ ግብነት መቀየር ይጠበቅባቸዋል ። በአዲሱ የውድድር ዘመንም በዳዋ ሆቴሳ ከሚመራው የአጥቂ መስመር የአዳማ ደጋፊዎች ብዙ ይጠብቃሉ።

በመከላከሉ ረገድ በ2014 የውድድር ዘመን በሊጉ ከፋሲል ከነማ እኩል 23 ግቦችን ብቻ በማስተናገድ በጣምራ የሊጉ ሁለተኛ ጠንካራ የመከላከል መስመር ባለቤት የሆነው ቡድን ዘንድሮም ይህን ጥንካሬ ማስጠበቅ ይኖርበታል ። ከዚህ ጥንካሬ በስተጀርባም ፍፁም እምርታን እያሳየ የሚገኘው ሁለገቡ ተከላካይ ሚሊዮን ሰለሞን በአዲሱ የውድድር ዘመንም ይህን ብቃቱን ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በመጪው አርብ በሚጀምረው የ2015 የውድድር ዘመን የሊጉ ውድድር አዳማ ከተማ ሰኞ መስከረም 23 ላይ ፋሲል ከነማን በመግጠም ይጀምራሉ።

የአዳማ ከተማ የ2015 ቡድን አባላት



ግብ ጠባቂ

22 ሰይድ ሀብታሙ
1 ኩዋሜ ባህ
30 በቃሉ አዱኛ

ተከላካዮች

7 ደስታ ዮሀንስ
21 እዮብ ማቲዮስ
5 ጀሚል ያቆብ
19 አዲስ ተስፋዬ
4 ሚሊዮን ሰለሞን
25 አብዲ ዋበላ
6 ፉዐድ ኢብራሂም
15 ታዬ ጋሻው

አማካዮች

8 አማኑኤል ጎበና
3 መስዑድ መሐመድ
11 ዊሊያም ሰለሞን
29 አዲስ ግርማ
14 አድናን ረሻድ
17 ቦና ዓሊ
20 ፍሬድሪክ ሀንሰን
23 ኤልያስ ለገሰ
13 ጋዲሳ ዋዶ
41 ሳዲቅ ዳሪ
18 ነቢል ኑሪ
16 አቤኔዘር ሲሳይ

አጥቂዎች

12 ዳዋ ሆቴሳ
9 አሜ መሐመድ
10 አብዲሳ ጀማል
27 አቡበከር ወንድሙ
31 አብድልፈታ ሰፋ
28 ቢኒያም አይተን
44 ፍራኦል ጫላ
47 ዮሴፍ ታረቀኝ

የአሰልጣኝ ቡድን አባላት
ዋና አሰልጣኝ – ይታገሱ እንዳለ
ረዳት አሰልጣኝ – ተረፋ ሂርጳሳ
ቡድን መሪ – አብዲ ቡሊ
የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ – መስፍን ነጋሽ
የህክምና ባለሙያ – በዳዳ ቶሎሳ