በአፍሪካ ከ20 አመት በታች ዋንጫ ማጣርያ 1ኛ ዙር ሶማልያን በሜዳው አስተናግዶ 2-1 የረታው የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን ከ2 ሳምንት በኋላ እስከሚያደርገው የመልስ ጨዋታ ድረስ ተጫዋቾቹን ወደ ክለቦች ሳይልክ ዝግጅ ማድረጉን እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ ከእሁዱ ጨዋታ በኋላ ትላንት ለተጫዋቾቹ እረፍት የሰጠ ሲሆን በዛሬው እለት በአዲስ አበባ ስታድየም ዝግጅቱን ጀምሯል፡፡ በአዲ አበባ ስታድየም የሚከናወነው ልምምድ ለቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ከቀጠለ በኋላ የዝግጅት ቦታቸውን ወደ ድሬዳዋ እንደሚያዞሩ ታውቋል፡፡
አሰልጣኝ ግርማ ሀብተዮሃንስ እና ረዳቶቻቸው ከ15 ቀን በኋላ በጅቡቲ ሊካሄደው የመልስ ጨዋታ ተጨማሪ ተጫዋቾችን ለማካተት ሀሳብ ያላቸው ሲሆን በዞህ ሳምንትም ተጨማሪ ተጫዋቾችን ያካትታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ብሄራዊ ቡድን በአመዛኙ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ክለቦች የተዋቀረ በመሆኑ ከሁለት በላይ ተጫዋች ያስመረጡት ጅማ አባ ቡና ፣ ሙገር ሲሚንቶ እና አዲስ አበባ ከተማ የቀጣይ ሳምንታት ጨዋታቸውን አያደርጉም ተብሏል፡፡ ሶስቱ ክለቦች የዚህ ሳምንት ጨዋታዎቻቸውን አለማድረጋቸው ይታወሳል፡፡