አማኑኤል ገብረሚካኤል ውሉን አራዝሟል

በግብፅ ሊግ ያመራል ተብሎ በስፋት ይነገር የነበረው አማኑኤል ገብረሚካኤል በፈረሰኞቹ ቤት የሚያቆየውን ውል አራዝሟል።

ያለፉትን ሁለት ዓመታት ከፈረሰኞቹ ጋር መልካም ጊዜን በማሳለፍ የ2014 የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ማንሳት የቻለው አማኑኤል ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ለአንድ ዓመት ለመቆየት መስማማቱን ክለቡ ይፋ አድርጓል።

በዳሽን ቢራ ቢ ቡድን የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው አማኑኤል በመቐሌ 70 እንድርታ በማምራት የሊጉን ዋንጫ በማንሳት መልካም ጊዜ ካሳለፈ በኋላ ነበር ፈረሰኞቹን የተቀላቀለው። የሀገር ውስጥ ዝውውር መስኮት ከተከፈተበት ጊዜ አንስቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ ውሉን ያራዝማል ተብሎ ቢጠበቅም በግብፅ ሊግ ተፈላጊነትን ማግኘቱን ተከትሎ የዝውውር ሂደቱን ለመፈፀም ለወራት ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። ዛሬ አልያም ነገ ወደ ግብፅ ያቀናል ተብሎ ሲጠበቅ ድንገት ዝውውሩ በምን ምክንያት እንከን እንደገጠጠመው ሳይታወቅ በፈረሰኞቹ ቤት ለተጨማሪ ዓመት የመቆየቱ ነገር እርግጥ ሆኗል።

የፊት መስመሩ በጉዳት ምክንያት ሳስቶበት የነበረው የወቅቱ ሊጉ ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ የአማኑኤል መፈረም እንደ መልካም ዜና ሆኖለታል።

ያጋሩ