የክለቦች የውድድር ዘመን ቅድመ ዳሰሳ | ወላይታ ድቻ

የጦና ንቦቹ በዘንድሮው ውድድር የዓምናው ቡድናቸው ላይ መጠነኛ ለውጦችን በማድረግ ቀርበዋል።

በየዓመቱ በሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆነው ከሚታዩ ቡድኖች መካከል የሆነው ወላይታ ድቻ ዘጠነኛ የውድድር ዓመቱን ለመጀመር በዝግጅት ላይ ይገኛል። ዓምና የነበረው የድቻ ጉዞ 5ኛ ደረጃን ይዞ በመጨረስ የተደመደመ ቢሆንም በሁለቱ ዙሮች ፍፁም የተለያየ መልክን አሳይቷል። በመጀመሪያው ዙር 9 ድሎችን በማስመዝገብ እና አንድ ጊዜ ነጥብ በመጋራት በ28 ነጥቦች 2ኛ ደረጃን ይዞ ጨርሷል። በሁለተኛው ዙር ግን በጀመረበት የዋንጫ ፉክክር መቀጠል ሳይችል ያገኛቸው ነጥቦች በግማሽ ቀንሰው ዓመቱን በ42 ነጥቦች ቋጭቷል። ደካማ በነበረበት ሁለተኛ ዙር ላይም ግን ስምንት ጨዋታዎችን ነጥብ በመጋራት መጨረሱ ቡድኑ ከሰንጠረዡ አጋማሽ ሳይወርድ የተረጋጋ ዓመት እንዲያሳልፍ ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው።

ቀደም ባለው የ2013 የውድድር ዓመት በመሀል የአሰልጣኝ ለውጥ በማድረግ እንዲሁም 2014 ላይም በአስተዳደር እና በዋና አሰልጣኝነት ቦታ ላይ ለውጦችን በማድረግ ጀምሮ የነበረው ድቻ ዘንድሮ የተረጋጋ ክረምትን አሳልፏል። አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም ከክለቡ ጋር አብረው የቀጠሉ ሲሆን ረዳታቸው አሰልጣኝ ጣሰው ታደሰ እና የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኙ ዘላለም ማቲዮስ አሁንም በጦና ንቦቹ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ናቸው።

ወትሮም ከአብዛኞቹ የሀገራችን ክለቦች በተለየ አቅሙን ያገናዘቡ የተመጠኑ ዝውውሮችን በማድረግ ከዕድሜ ዕርከን ቡድኖቹ በሚያሳድጋቸው ተጫዋቾች ላይ አመዝኖ ቡድኑን የሚሰራው ወላይታ ድቻ ዘንድሮም ይህንኑ ይበል የሚያሰኝ መንገድ ቀጥሎበታል። በዚህም ዘግየት ብሎ ወደ ገበያ በመውጣት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥሎ ጥቂት ዝውውሮችን የፈፀመ ክለብ ሆኗል። አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም የክለባቸው የዝውውር ሂደት ላይ ጠቅለል ያለ ሀሳባቸውን ሲሰጡ “የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዝውውር መስኮት በአብዛኛው ከሐምሌ 1 ጀምሮ እስከ ሀምሌ 8 ከፍተኛ ዝውውር የተደረገበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ በዛን ሰዓት የተለያዩ የሚፈለጉ ተጫዋቾች ወደ ተለያዩ ክለቦች አምርተዋል። እኛ አቅማችንን ታሳቢ አድርገን ነው ተጫዋቾች የምናስፈርመው እና አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ደግሞ ቡድኑ ላይ የነበሩ ናቸው።” ይላሉ።

ወላይታ ድቻ ዘንድሮ በፈፀማቸው ዝውውሮች በአርባምንጭ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ብዙ ደቂቃዎችን ያላገኙት የመስመር ተከላካዩ ሳሙኤል ተስፋዬ እና አጥቂው ፍቃዱ መኮንን እንዲሁም በወልቂጤ ከተማ አማካይ ክፍል ላይ ቁልፍ ሚና የነበረው በኃይሉ ተሻገር ወደ ወላይታ ድቻ መጥተዋል። ክለቡ ከአንድ ዓመት በኋላ ፊቱን ወደ ውጪ ተጫዋቾች በመመለስ ጋናዊው አጥቂ ሚኬል ሳርፖንግን ደግሞ አራተኛው ፈራሚው አድርጓል። ከሐምሌ መጨረሻ በኋላ ወደ ዝውውር ሂደቱ እና ወደ ዝግጅት መግባታቸውን ተከትሎ በቅድሚያ ያሰቧቸው ተጫዋቾች በተለየም ወደ መድን ፣ ቡና እና ሀዋሳ እንዳመሩ የሚገልፁት የቡድኑ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም አሁን ባመጧቸው ተጫዋቾች ላይም ዕምነት እንዳላቸው ይናገራሉ። “ከአራቱ ተጫዋቾች ሁለቱ ፍቃዱም ሆነ ሳሙኤል ብዙም በነበሩበት ክለብ የመሰለፍ ዕድል ያላቸው ልጆች አይደሉም፡፡ ያ ማለት ግን ችሎታ የላቸውም ማለት አይደለም። እኛ ጋር መጥተው የተሻለ ነገርን ሊያሳዩን ይችላሉ፡፡ በተረፈ ከቋሚ ተጫዋች አንድ በኃይሉን ነው ያመጣነው። የውጪ ተጫዋችም በማጥቃት ላይ እጥረት ስላጋጠመን ማጠናከር ስለነበረብን አንድ የውጪ ተጫዋች አምጥተናል፡፡”

አምና ጥቂት ግቦችን በማስተናገድ (24) በሊጉ አራተኛ ደረጃ ላይ ሆኖ የጨረሰው ወላይታ ድቻ ከዚህ በመነሳት ይመስላል ከወገብ በታች ያለው ስብስቡ ላይ ሳሙኤል ተስፋዬን ብቻ ነው የጨመረው። አንጋፋው ደጉ ደበበን ጨምሮ አንተነህ ጉግሳ ፣ በረከት ወልደዮሐንስ ፣ አናጋው ባደግ ፣ ያሬድ ዳዊት እና ጥሩ ዕድገት ያሳየው መልካሙ ቦጋለ አሁንም የጦና ንቦቹ የኋላ ደጀን ሆነው ይቀጥላሉ። አማካይ ክፍል ላይም የንጋቱ ገብረስላሴ እና ሀብታሙ ንጉሴ ጥምረት እንዳለ ሲሆን ከታታሪው አበባየሁ አጪሶ በተጨማሪ የቡድኑ የፈጠራ ምንጭ የነበረው እንድሪስ ሰዒድ ላይ በኃይሉ ተሻገር መጨመሩ ለአሰልጣኝ ፀጋዬ ጥሩ አማራጭ እንደሚፈጥርላቸው ይታሰባል። የወላይታ ድቻ ትልቁ ድክመት የነበረው ግብ የማስቆጠር ችግር በምንይሉ ወንድሙ መውጣት ምክንያት ከጉዳት ጋር እየታገለ ባሳለፈው ስንታየሁ መንግሥቱ እና ቃልኪዳን ዘላለም እንዲሁም አምና ከዕድገቱ ተቀዛቅዞ የታየው ቢኒያም ፍቅሬ ላይ ብቻ እንዳይመሰረት የፍቃዱ መኮንን እና ሚካኤል ሳርፖንግ መምጣት መልካም የሚባል ነው።

ወላይታ ድቻ እንደክለብ አምና የ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ሲሆን በ17 ዓመት በታች ደግሞ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል። ይህም ክለቡ አሁንም ከስር አስተማማኝ ምንጭ እንዳለው ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ባለፉት ሁለት የውድድር ዓመታት ከተስፈኝነት ተነስተው በርካታ ደቂቃዎችን ወደማግኘት የተሸጋገሩት መልካሙ ቦጋለ እና አበባየሁ አጪሶ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው። በመቀጠል የተሻለ የመታየት ዕድል የነበራቸው ቢኒያም ፍቅሬ እና መሳይ ኒኮልን ጨምሮ አምና ጥቂት ደቂቃዎችን ያገኙት ዮናታን ኤልያስ ፣ ዘላለም አባቴ ፣ ውብሸት ወልዴ ፣ ሳሙኤል አጂሶ እንዲሁም ወደ አሰላለፍ ያልመጣው አዛሪያስ አቤል ዘንድሮ የተሻለ ጎልብተው እንደሚመጡ ይጠበቃል። አሰልጣኝ ፀጋዬም በእነዚህ ወጣቶች ላይ ብርቱ ዕምነት እንዳላቸው አበክረው ይናገራሉ።

“ልጆቻችን አምና ትንሽ ወጣ ገባ እያሉ ሜዳውን እንዲለምዱ እያደረግን ነበር፡፡ በዝግጅት ወቅት ግን በጣም በብቃት ወደ ቋሚ ተሰላፊነት የሚገቡበት እና ቅድሚያ የምንለይበት ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ነው ያሉት ፤ በጣም ጥሩ ሆኗል። ከአንድ ዓመት በኋላ በሥልጠና ሁለተኛ ዓመታቸው የዝግጅት ወቅት ከእኛ ጋር ሲያሳልፉ የራሳቸውን አቅም መፍጠር የሚችሉበት ደረጃ ላይ ነው ያሉት። አሁንም ወጣት ተጫዋቾቻችን ተማምነን ነው ያለነው። ወላይታ ድቻ ደግሞ ልጆች የማሳደግ ችግር የለበትም። ትልቁ እንደውም ዕቅዳችን ወጣቶችን ማብቃት ነው። እነርሱ ስላሉን እንደውም እኛ አልተጨናነቅንም ማለት ይቻላል፡፡”

ወላይታ ድቻ ከነሐሴ 9 ጀምሮ በመቀመጫው ሶዶ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል። መሰረታዊ ከሆኑ የቅድመ ውድድር ዝግጅቶች በተጨማሪ አምና ድክመት ይታይበት የነበረው የቡድኑ ያማጥቃት አቅም ላይ አመዝኖ ሲሰራም ሰንብቷል። የዝግጅት ጨዋታዎችን በማድረጉ በኩል ግን እንደምናው ሁሉ ወላይታ ድቻ ራሱን አግልሏል ማለት ይቻላል። ከዓምና በፊት በክረምቱ መውጫ ላይ በሚደረጉ ውድድሮች ላይ ይካፈል የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ አንድ ጨዋታ ብቻ ነው ያደረገው። አሰልጣኝ ፀጋዬ ይህንን ነጥብ ሲያብራሩ “እኛ የወዳጅነት ጨዋታ አላደረግንም ማለት ይቻላል። አንድ ጨዋታ ነው ከአርባምንጭ ጋር አርባምንጭ ላይ ሄደን የተጫወትነው። በዛ ጨዋታ ደግሞ ሀያ ሁለት ተጫዋቾችን ለመጠቀም ሞክረናል። ብሔራዊ ቡድን ከሄዱት ውጪ ባሉ ልጆች መጫወት ችለናል፡፡ ቡድናችን አርባ አምስት አርባ አምስት ደቂቃ ነው ለሁለት ከፍለን የተጫወትነው። ከዚህ የተሻለ የወዳጅነት ጨዋታ ያስፈልገን ነበር ፤ ያው ከአንዳንድ ክለቦች ጋር ጀማምረን ነበር ጨዋታዎችን ለማድረግ ስላልተመቻቸላቸው ሶዶ ላይ ለማከናወን አስበን አልተሳካልንም፡፡ በተረፈ በአብዛኛው ራሳችን እርስ በእርስ ግጥሚያዎች ላይ ትኩረት አድርገናል። የተሻለ የወዳጅነት ጨዋታ ያስፈልገን ነበር።

ከሜዳ ስለራቅን ከውድድርም ስለራቅን ያው ያስፈልገን ነበር ፤ አጋጣሚ ሆኖ አልተሳካልንም። ስለዚህ ሌላ አማራጭ ስለሌለ ቀጥታ ወደ ውድድር ራሳችንን አዘጋጅተን እየቀረብን ነው ያለነው፡፡” በማለት ነበር።

በዘንድሮው የወላይታ ድቻ ቅድመ ዝግጅት ውስጥ ዋነኛ ጠንካራ ጎን ተደርጎ የሚወሰደው የቡድን ወጥነት ነው። አብዛኞቹ ክለቦች አዲስ ቡድን ገንብተው ከመምጣታቸው አንፃር ነባር ብቻ ሳይሆን አምና ጥሩ የተንቀሳቀሰ ስብስብን ይዞ መቀጠል መቻል ለድቻ መልካም አጋጣሚ ነው። በአጠቃላይ ስብስቡ ውስጥ አብዛኞቹ ተጫዋቾች ሁለተኛ የውድድር ዓመታቸውን የተወሰኑት ደግሞ ሦስት እና ከዛ በላይ ዓመታቸውን አብረው ለማሳለፍ በዝግጅት ላይ መገኘታቸው በብዙዎቹ የሊጉ ቡድኖች ውስጥ የሌለ ባህል ነው። ከዚህ አንፃር ስንመለከተው አዲስ ፈራሚ ተጫዋቾችን በየቦታቸው ላይ ተግባቦት እንዲፈጥሩ ማድረግ ከተቻለ ወላይታ ድቻ ከአምናው የተሻለ የፉክክር ደረጃ ላይ የመገኘት ዕድሉ የሰፋ ነው። በእርግጥ አሰልጣኝ ፀጋዬ 2014 ላይ በበርካታ አጋጣሚዎች የቡድናቸው የስብስብ ጥራት እና ጥልቀት እየፈተናቸው እንደነበር ሲናገሩ አድምጠናል። ዘንድሮም በዚህ ረገድ የተፈፀሙት ዝውውሮች አሰልጣኙ ያነሱ የነበሩትን ሀሳብ ሙሉ ለሙሉ ይቀርፋሉ ለማለት ያዳግታል። ሆኖም የወጣቶቹ አንድ ዓመት ጨምሮ መምጣት የቡድን ጥልቀቱን ደረጃ ማሻሻል እንደሚችል ይታመናል። አሰልጣኙ ከዚህ ነጥብ ጋር በተያያዘ ላነሳንላቸው ሀሳብ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተውናል።

“በአንድ በኩል ቡድኑ አለመፍረሱ ለእኛ ጥሩ አጋጣሚ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ በሊጉ ግን እንደሚታወቀው በውስን ተጫዋቾች ላይ ተንጠልጥሎ መቆየት በጣም ከባድ ነው። ዋንጫ የወሰደው ጊዮርጊስ እና ፋሲልንም ስታያቸው በስብስብ ፣ በጥራት ጥሩ ስለነበሩ ሰላሳውን ጨዋታ በመተካካት ጨርሰውታል። እኛ ደግሞ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ተጫዋቾች በጉዳት በሚወጡበት ሰዓት ከአስር ጨዋታ ከአስራ አምስት ጨዋታ በላይ በጉዳት በሊጉ ላይ ያልነበሩ ተጫዋቾች አልፎ አልፎ አሉና እና እነርሱን ለመተካት ተቸግረን ነበር፡፡ ስለዚህ ካለን አቅም አንፃር ወጣቶቹን የማብቃት እና አብዛኛው ደግሞ ከነባሮች ጋር ሁለገብነት ያለውን ተጫዋች ውስጥ ለማስገባት እየሞከርን ያለነው። በአንድ ፖዚሽን ሳይሆን ወጣቶች ናቸው ተጨማሪ ፓዚሽን ውስጥ ገብተው እንዲጫወቱ የቦታ ሽፍቶችን እያደረግን እየሞካከርን ነው ያለነው። እና አሁንም በዛው ልክ ነው መቀጠል የምንችለው ስለዚህ የምንችለው ነገር እናደርጋለን በአቅማችን፡፡”

በሌላ በኩል ከበጀት እና ከክለቦች ጋር ለመገናኘት አጋጣሚው ባለመፈጠሩ አንድ ጨዋታ አድርጎ ወደ ውድድር የሚገባው ወላይታ ድቻ አምናም በተመሳሳይ አኳኋን ውስጥ ማለፉ ነገሩን የተለመደ ቢያደርገውም እንደ አንድ ደካማ ጎን መውሰድ ግን ይቻላል። ቡድኑ በቂ የዝግጅት ሳምንታትን ቢያሳልፍም ከአምስት በላይ ጨዋታዎችን ማድረግ አለመቻሉ ወቅታዊው የጨዋታ ብቁነት ደረጃውን ለማወቅ እንዲቸገር ያደርገዋል። በእርግጥ ነባሩ ስብስብ አብሮ መቀጠሉ ይህን ድክመቱን የሚያቃልለት ቢሆንም በሊጉ መክፈቻ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ ወደሚፈልገው ሪትም ለማግባት ፈተና ሊሆንበት ይችላል።

በአጨዋወት ደረጃ ወላይታ ድቻ በዋናነት የዓምናውን የመከላከል ብርታት ማስቀጠል ይጠበቅበታል። በግለሰቦች ደረጃ ለውጥ ያልተደረገበት የተከላካይ ክፍሉ እንደቡድን ሲከላከል ከቀሪው የቡድኑ ክፍሎች ያገኝ የነበረው ድጋፍ ዘንድሮም በተሻለ መግባባት ከተደገመ አምና ካስተናገደው የግብ መጠን በታች የማስተናገድ ዕድሉ ይኖረዋል። በቁጥር በርክቶ እና በትክክለኛው ጊዜ ክፍተቶችን በመዝጋት የማይታማው የቡድኑ የመከላከል ሽግግር በተቃራኒው ወደ ማጥቃት ሲሸጋገር ፊት ላይ በቀላሉ የቁጥር ብልጫ ተወስዶበት ማጥቃቱ በተጋጣሚ የሚቋረጥባቸው አጋጣሚዎች ግን ዋነኛ የመሻሻያ ነጥቦቹ መሆን ይገባቸዋል። እንደቡድን ከመከላከል ባለፈ በሜዳው ቁመት እና ስፋት እንደቡድን አጥቅቶ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ከጦና ንቦቹ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ይጠበቃል። ይህ መሆን ከቻለ እና በንፅፅር ጥሩ የሆነው የቆመ ኳስ አጠቃቀሙ ከቀጠለ የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ከ2014 የተሻለ የግብ መጠነንን ሊያስመዘግቡለት ይችላሉ።

በግለሰብ ደረጃ ወላይታ ድቻ ዘንድሮም ከአጥቂው ስንታየሁ መንግሥቱ የተሻለ ግልጋሎትን ይጠብቃል። 2013 ላይ በ14 ጨዋዎች 11 ግቦች እንዲሁም በ2014 በ18 ጨዋታዎች 5 ግቦችን ያስቆጠረው ስንታየሁ የሁለቱ ዓመታት የወላይታ ድቻ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ቢሆንም ከጉዳት ነፃ መሆን ከቻለ ከዚህም በላይ የማድረግ አቅሙ እንዳለው ብዙዎች የሚስማሙበት ነው። ሌላው አምና 8 ጨዋታዎችን ጀምሮ በሦስቱ ግብ ያላስተናገደው ቢኒያም ገነቱ ነው። ግብ ጠባቂው ዕድል ባገኘባቸው ጊዜያት እጅግ አደገኛ ኳሶችን በማዳን ተከታታይ ጨዋታዎችን ማድረግ መቻሉን ስናስብ ዘንድሮ ከፅዮን መርዕድ ጋር የሚያደርጉት ፉክክር ለድቻ ግብ ክልል ይበልጥ የመጠናከር ዕድልን የሚሰጥ ሆኖ እናገኘዋለን። ከዚህ ውጪ ከላይ ያነሳናቸው ተከላካዩ መልካሙ ቦጋለ እና አማካዩ አበባየሁ አጪሶ ዘንድሮም ይበልጥ ራሳቸውን ከፍ ባለ ደረጃ የሚያሳዩበት ዓመት እንደሚሆን ሲጠበቅ ከሌሎቹ ወጣቶች መካከልም ልዩነት ፈጣሪ ሆኖ ብቅ የሚል እንደማይጠፋ ይገመታል።

ወላይታ ድቻ የ2015 የውድድር ዓመት የመጀመሪያ ጨዋታውን በመጪው እሁድ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በማድረግ ይጀምራል።

የወላይታ ድቻ የ2015 ሙሉ ቡድን ዝርዝር


ግብ ጠባቂዎች

31 ፅዮን መርዕድ
30 ወንደወሰን አሸናፊ
1 ቢኒያም ገነቱ
32 አብነት ይስሀቅ

ተከላካዮች

12 ደጉ ደበበ
26 አንተነህ ጉግሳ
15 መልካሙ ቦጋለ
4 በረከት ወልደዮሐን
16 አናጋው ባደግ
9 ያሬድ ዳዊት
28 ሳሙኤል ተስፋዬ
24 አዛሪያስ አቤል
5 ኬኔዲ ከበደ
27 ዮናታን ኤልያስ
6 ሳሙኤል ጃጊሶ

አማካዮች

25 ንጋቱ ገብረሥላሴ
14 መሳይ ኒኮል
20 ሀብታሙ ንጉሴ
8 እንድሪስ ሰዒድ
23 በኃይሉ ተሻገር
19 አበባየሁ አጪሶ
18 ውብሸት ወልዴ

አጥቂዎች

10 ስንታየሁ መንግሥቱ
21 ቃልኪዳን ዘላለም
13 ቢኒያም ፍቅሩ
11 ፍቃዱ መኮንን
29 ዘላለም አባቴ
ሚካኤል ሳርፖንግ

አሰልጣኞች

ዋና አሰልጣኝ – ፀጋዬ ኪዳነማሪያም
ምክትል አሰልጣኝ – ጣሰው ታደሰ
የግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ – ዘላለም ማቲዮስ
የህክምና ባለሙያ – ዶ/ር አበራ መና
ፊዚዮቴራፒስት – ባርካ ባካሎ