የክለቦች የውድድር ዘመን ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ

የሁለት ጊዜ የሊጉ ሻምፒዮን ሀዋሳ ከተማ ለሦስታ የተዘጋጀበትን የ2015 የውድድር ዓመት ዳሰሳ እንደሚከተለው አጠናክረናል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ መልክ 1990 ላይ ከተጀመረ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫው ወደ ክልል እንዲወጣ ያደረገው እና ከመዲናይቱ ክለቦች ውጪ 2 ጊዜ ሻምፒዮን መሆን የቻለው ሀዋሳ ከተማ በየዓመቱ በሊጉ ከምናያቸው ሁለት ክለቦች (አንደኛው ኢትዮጵያ ቡና ነው) መካከል አንዱ ነው። ባለፉት 25 የውድድር ዓመታት ቡድኑ ለዋንጫ የሚፎካከርባቸው ጊዜያት እንደነበሩ ሁሉ ላለመውረድ ሲፍጨረጨርም የተመለከትንባቸው ወቅቶችም ባይዘነጉም ዓምና ግን በአስተማማኝ ደረጃ ላይ ሊጉን አገባዷል። አልፎም ለበርካታ የጨዋታ ሳምንታት ለዋንጫ እና ሀገራችንን በአህጉራዊ መድረክ ለመወከል የሚያስችለውን ቦታ ለመያዝ ሲጥር ነበር።

የዓምናው የ2014 የውድድር ዘመን ከመጀመሩ በፊት አሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን የሾመው ክለቡ በተጫዋቾች የዝውውር መስኮት በደንብ ተሳትፎ ሊጉን በመቀመጫ ከተማው ቢጀምርም በመጀመሪያዎቹ ስድስት ጨዋታ ሁለቱን ብቻ ነበር ያሸነፈው። ይህንን ተከትሎ ቡድኑ መጥፎ ጊዜ ያሳልፋል ተብሎ ቢገመትም ቀስ እያለ ወደ ላይኛው የደረጃ ሰንጠረዥ አናት እድገት እያሳየ ተጉዟል። ምንም እንኳን ቡድኑ ጨዋታ በጨዋታ በእንቅስቃሴም ሆነ በውጤት ረገድ መሻሻል እያመጣ ቢቀጥልም በሁለተኛው ዙር ግን ይህ መሻሻል ተገቶ ዳግም የውጤት ማሽቆልቆል ተከስቶበት ነበር። ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ የተጫዋቾች ጉዳት እንደሆነ አሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ከሱፐር ስፖርት ጋር ባደረጓቸው የቅድመ እና የድህረ-ጨዋታ አስተያየቶች በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይደመጣል። እርግጥ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ የሚገቡ ስድስት እና ሰባት ተጫዋቾችን በጨዋታዎች ያጣባቸው ጊዜያት መኖራቸውም የሚሸሸግ አይደለም። የሆነው ሆኖ በሁለተኛው ዙር ከተደረጉት 15 ጨዋታዎች ማግኘት ከሚገባው 45 ነጥቦችን 18ቱን ብቻ በማሳካት አጨራረሱ የበለጠ እንዳያምር ሆኖበታል። ይህ ቢሆንም ግን በአጠቃላይ የውድድር ዓመቱ 13 ጨዋታዎችን በማሸነፍ በ6ቱ አቻ ወጥቶ ቀሪዎቹን 11 ፍልሚያዎች ተረቶ በ45 ነጥብ 4ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

የዓምና አሠልጣኛቸውን ሳይቀይሩ የዘንድሮውን የውድድር ዘመን ከሚጀምሩ 9 ክለቦች መካከል (ወደ ሊጉ ያደጉ ክለቦችንም ያካትታል) አንዱ የሆነው ሀዋሳ ከተማ በተደራጀው የአሠልጣኝ ቡድን አባላቱም ላይ ለውጥ አላደረገም። ክለቡ የአሠልጣኝ ቡድን አባላቱን ባይነካካም ግን ስብስቡ ላይ ለውጦችን አድርጓል። በዚህም ከአምናው ስብስብ አስር ተጫዋቾችን በመልቀቅ ስምንት አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሞ ወደ አዲስ የቡድን ግንባታ የገባ ይመስላል።

ሀዋሳ ከተማ ያለፉትን ዓመታት በተረጋጋ የቡድን ስብስቡ የሚታወቅ ቢሆንም በክረምቱ ግን አይነኬ የሚባሉ ተጫዋቾችን ጨምሮ እንደገለፅነው 10 ተጫዋቾችን ለሌሎች ክለቦች አሳልፎ ሰጥቷል። ከግብ ጠባቂ እስከ አጥቂ ባሉት አራቱም ዲፓርትመንቶች ተጫዋቾችን ያጣው ክለቡ አዲሱን ዓመን በአዲስ የቡድን ግንባታ እንዴት ይጋፈጣል የሚለው ደግሞ ተጠባቂው ጉዳይ ነው። በተለይ በተለይ ከታዳጊነት ጀምሮ አብረው የቆዩ ተጫዋቾች ቡድኑን መምራት በጀመሩበት ሰዓት መልቀቃቸው የሚፈጥረው ተፅዕኖ እንዳለ ቢታመንም አሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ግን ይህንን ሀሳብ አይቀበሉትም።

“ምናልባት የወጡ ወሳኝ ተጫዋቾች ሁለት ናቸው፡፡ ቋሚ ተሰላፊ ሆነው ክለቡን ዓመቱን ሙሉ ሲጠቅሙ የነበሩ ተጫዋቾች ማለት ነው። ከዛ ውጪ አልፎ አልፎ አንዱ እንደውም በጉዳት ብዙ ጨዋታ ባይጫወትም እንደ ቡድን ግን ተሰርቶባቸው ነበር። ዞሮ ዞሮ አዲስ ቡድን አይሆንም። ምክንያቱም ሁለት ሰው ነው የወጣው ሁለት ሰው መተካት ነው በነበረው ቡድን ላይ ፤ ከዛ ውጪ የመጡ እና ነባር የሆኑ ተጫዋቾችም ጫና ፈጥረው መጫወት የሚችሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ ቡድኑ አዲስ መሆኑ ሳይሆን ተጫዋቾቹ አዳዲሶች ናቸው። በነባሩ እንጀምር በአዲሱ እንጫወት ግን አላወቅንም ፤ በወቅታዊ ብቃት ነው የሚወሰነው። እኛ ግን ሁለቱንም አቀናጅተን ነው ለመሥራት የምናስበው።” ካሉ በኋላ እንደ መስፍን ታፈሰ እና ብሩክ በየነ የመሳሰሉ ወሳኝ ተጫዋቾችን ቢያጡም የአጨዋወት ለውጥ በማድረግ ቡድኑ ተገማች እንዳይሆን ሥራዎችን እየሰሩ እንደሚገኝ ይጠቅሳሉ።

“እንደ ቡድን ምን አልባት የአጨዋወት ዘይቤያችን ሊቀየር ይችላል፡፡ ዓምና ቀጥተኛ ኳስ ነው ስንጫወት የነበረው ፤ ያንን እንድናደርግ የሚያስገድዱ ተጫዋቾች ብቻ ስለነበሩ ነው ሌሎች አማራጮች ለመጠቀም ያልቻልነው። ተጫዋቾቻችን ለዚህ አጨዋወት ብቻ የሚሆኑ ስለነበሩ በዛ መንገድ ለመጫወት ተገደናል፡፡ ዘንድሮ ግን በፈለግንበት መንገድ መጫወት እንችላለን፡፡ እንደ ተጋጣሚው ነው ቡድናችንን አዘጋጅተን የትኛውንም አሰላለፍ እና አጨዋወት ለመከተል የምናስበው። ዘንድሮ ከዓምናው የተሻለ እንቅስቃሴ እንድናደርግ ያደርገናል እንጂ ተገማች ሆነን እንቀርባለን ብዬ አላምንም። ምክንያቱም በየትኛውም መንገድ መጫወት ስለምንችል ተጫዋቾቻችንን የነበሩትንም ያቆየነው አዲሶቹንም ያመጣናቸው ይሄንን ታሳቢ በማድረግ ነውና ከዓምናው የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ እንገደዳለን ብዬ አስባለሁ፡፡ በየትኛውም መንገድ ተጫውተን ክለባችንን ውጤታማ ማድረግ ስለሆነ በዚህ መጠን ነው ቡድናችንን የገነባነው። የተሻለ ነገርም እንሠራለን ብዬ ነው የማምነው። የወጡ ተጫዋቾች የአጨዋወት ዘይቤያችንን አይቀይሩም ፤ የእነርሱ መውጣት ክፍተት አይፈጥርብንም። ቢኖሩ ቡድናችንን ያጠናክሩታል ምንም ጥያቄ የለውም ግን እነርሱን የሚተኩ ይበልጥ ደግሞ ቡድናችንን ጠንካራ የሚያደርጉ ተጨማሪ ተጫዋቾችን ስላመጣን በዚህ ክፍተት ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ ይሄንን ደግሞ በወዳጅነት ጨዋታዎች እየለየን ስለነበር አዲስ ቡድን የመገንባት ያህል አይደለም ብዬ ነው የማምነው።”

ሀዋሳ ከተማ በዝውውር መስኮቱ እዮብ አለማየሁ ፣ በረከት ሳሙኤል ፣ ሙጂብ ቃሲም ፣ ሰይድ ሀሰን ፣ አዲሱ አቱላ ፣ ብርሃኑ አሻሞ ፣ ሰለሞን ወዴሳ እና ዓሊ ሱሌይማንን ያስፈረመ ሲሆን ዋነኛ ችግሩ የነበረውን የመከላከል ክፍተትንም ለመሸፈን የጣረ ይመስላል። ዓምና ከሊጉ ከወረዱት ክለቦች ውጪ ሦስተኛው ብዙ ግብ ያስተናገደው ክለቡ ይህንን የኋላ ሽንቁር ለመድፈን 50% የሚሆነውን ግዢ የተከላካይነት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾች ላይ ማድረጉ ነገርየውን በደንብ እንዳጤነው ይጠቁመናል። በዚህም ሁለት የመሐል እና አንድ የመስመር ተከላካዮች እንዲሁም አንድ የተከላካይ አማካይ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል። በመከላከል ብቻ ሳይሆን ግን በማጥቃቱም ረገድ ዓምና የቡድኑን 52.7 በመቶ ግቦች ያስቆጠሩት እና በአጠቃላይ በቀጥታ ግብ እና አሲስት 26 ጎሎች ላይ የተሳተፉትን ብሩክ በየነ እና መስፍን ታፈሰን ማጣቱ በላይኛው ሜዳም ግዢ እንዲፈፅም አድርጎታል። በዚህም አይምሬው ሙጂብ ቃሲምን ጨምሮ ፈጣኖቹን እዮብ አለማየሁ እና ዓሊ ሱሌይማን አስፈርሟል።

ከሞላ ጎደል የፈረሙት ተጫዋቾች ጥሩ ጭማሪ እንደሚሰጡ ሲታሰብ አሠልጣኙም የፈረሙት 8 ተጫዋቾች ቡድኑን የሚመጥኑ ስለመሆናቸው እና የወጡትን የሚተኩ ስለመሆናቸው አስረድተው ተከታዩን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተውናል። “በዝውውሩ ቡድናችንን የሚመጥኑ፣ አቅም ያላቸው እና በሌላ ክለብ ጥሩ ነገር ሲሠሩ የነበሩ ተጫዋቾች ናቸው ወደ ቡድናችን የመጡት። የወጡ ተጫዋቾች ጥሩ የሚባሉ ነበሩ ፤ ግን የመጡት እነርሱን መተካት የሚችሉ እና በነበሩት ክለብ ላይ ያንን ሲያደርጉ ስለነበር እነርሱን በሚገባ የሚተኩ ተጫዋቾች ናቸው። ቢኖሩ ቡድናችን ይበልጥ ለማጠናከር ይጠቅመናል ፤ እነርሱ ቢወጡም የእነርሱን ቦታ ተክተናል ብዬ አስባለሁ። ሜዳ ላይም የምናየው ያንን ነው፡፡ ምክንያቱም አጥቂ ጎል ማግባት ነው ሥራው ፤ እነዛን ክፍተቶች በሚገባ ይሸፍናሉ። እስከ አሁንም ያንን እያየን ስለሆነ የወጡትን ተጫዋቾች ከመተካትም አልፎ ጠንካራ ተጫዋቾችን አምጥተናል። መተካት ብቻ ሳይሆን ይበልጥ ቡድኑን ጠንካራ የሚደርጉ ተጫዋቾችን ነው ያመጣነው። ቡድናችን ከዓምናው ይልቅ ዘንድሮ የተሻለ ስብስብ እንዳለው ነው የማስበውና በዚህ ልክ ነው ከቦርድ ጋር አውርተን ከደጋፊ አመራሮች ጋር በጋራ ሆነን የነበሩን ክፍተቶች ላይ ተነጋግረን እያንዳንዱ ተጫዋች ሲመጣ በምን መንገድ እንደመጣ ለደጋፊዎቹ ለሁሉም ይፋ ተደርጎ ነውና የመጡ ተጫዋቾችም ቡድናችን የሚጠቅሙ ታምኖባቸው የመጡ ስለሆኑ ቡድናችንን በዚህ ልክ ነው የገነባነው።”

ድክመቶቻችን እና ክፍተቶቻችን በነበሩ ቦታዎች ላይ ነው ተጫዋቾች ያመጣነው የሚሉት አሠልጣኙ በዋናነት በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ሲቸገሩበት የነበረውን የስብስብ ጥልቀት (Squad Depth) ችግርም ታሳቢ አድርገው በየቦታው ተጫዋቾችን እንዳገኙ ይናገራሉ። “በየትኛውም ቦታ ላይ ዘንድሮ ቢያንስ ከአምናው የተሻለ ስብስብ ይኖረናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ዓምና መሀል ላይ ተጫዋቾች በመጎዳታቸው የተነሳ ስብስቡ ጠባብ ስለነበር ረጅም ርቀት መጓዝ አልቻልንም፡፡ ዘንድሮ ግን በየቦታው ላይ ቢያንስ አንዱ ሲወጣ አንዱን ተክቶ መጫወት የሚችሉ ተጫዋቾችን አምጥተናል።” የሚል ሀሳባቸውን ካጋሩ በኋላ ከአዲስ ፈራሚዎቹ በተጨማሪም ከታዳጊ ቡድኑ የተገኙት ተጫዋቾችም ባላቸው ብቃት ለቡድኑ ትልቅ ግብዐት እንደሚሆኑ በመግለፅ የዓምናው ክፍተት እንደማይደገም እምነታቸውን አጋርተዋል።

ለ2015 የውድድር ዓመት የቅደመ ውድድር ዝግጅታቸውን ነሐሴ 5 የጀመሩት ሀዋሳ ከተማዎች የክረምቱን ዝናባማ የዐየር ሁኔታ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በግብርና ሜዳ እና አርቴፊሻል ሜዳ ልምምዳቸውን ሲሰሩ ቆይተዋል። በዝግጅት ጊዜያቸውም በተለይ ከላይ እንደገለፅነው በመከላከሉ ላይ ማጠናከሪያ ሥራዎችን እንደሰሩ የቡድኑ አለቃ ይገልፃሉ። “ለዓመት ውድድር የምትሰናዳበት ዝግጅት ስለሆነ ሁሉንም ያማከለ ነው የሚሆነው። ምክንያቱም በሁሉም ነገር ተጫዋቾችህ ዝግጁ እንዲሆኑ ነው የሚፈለገውና ዝግጅት ስታደርግ በዛ ልክ ነው፡፡ ከዛ ውጪ ከዝግጅቱ ጎን ለጎን አምና የነበሩን ደካማ ጎኖችን ለማሻሻል ወይም የነበረው እንቅስቃሴ በዚህ ዓመት እንዳይደገም ለማድረግ አንደኛ በተጫዋቾች ስብስብ ሁለተኛ ባሉን ተጫዋቾችም በዚህ ልክ ተነጋግረን በይበልጥ ስራዎች ሰርተናል። ዓምና እንዳያችሁት ቡድናችን ትልቁ ችግር የነበረው ብዙ ጎል እናገባለን ግን ብዙ ጎል ይገባብናል። ስለዚህ ያገባነውም የገባብንም ጎል ተመሳሳይ ነውና ይሄን ታሳቢ አድርገን በተለይ ተከላካይ ቦታ ላይ ለማጠናከር ሞክረናል፡፡ አዳዲስ ተጫዋቾችንም አምጥተናል በዚህ መንገድ ነው ቡድናችንን ያዘጋጀነው።” ካሉ በኋላ ማጥቃቱ ላይ ግን ብዙም ችግር ስላልነበር የወጡትን መተካት ላይ ብቻ እንደተጠመዱ አስረድተዋል።

“የማጥቃቱ ችግር ብዙም አልነበረንም። ምክንያቱም የነበሩ ተጫዋቾች ያንን ሲያደርጉ ነበር፡፡ ዘንድሮ ደግሞ የተወሰኑት ቢወጡም እነርሱን የሚተኩ ለማምጣት ሞክረናል። በዚህ ልክ ደግሞ የማጥቃት ሂደታችን ከአምናውም የተሻለ ነው ሊሆን የሚችለው ብዬ ነው የማስበው። አሁን ዝግጅት ላይም የወዳጅነት ጨዋታዎችም ላይ የማየው ያንን ነው። ጎሎቹም ያንን ያሳያሉና አሁንም የማጥቃት አቅማችን እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ አጥቅቶ የሚጫወት ቡድን ነው መገንባት የምንፈልገው። በተመሳሳይ እስከ አሁን ወደ አሰልጣኝነቱ ከመጣው ጊዜ ጀምሮ የምጫወትበት መንገድም ስለሆነ ይሄንን መሠረት ያደረገ ዝግጅት አድርገናል። በይበልጥ ስታጠቃ ተከላካይህንም ማጠናከር ስላለብህ ውጤታማ ለመሆን የተሻለ ቦታ ለመድረስ መከላከሉ ጠንካራ መሆን ስላለበት ከአምናውም ተሞክሮ ተነስተን እዚህ ላይ በጣም ልፋት የሚጠይቅ ሥራን ነው እየሠራን ያለነው። ቡድናችንን በዚህም ልክ እያገኘን ነውና እንደ ቡድን አሁን ወደ ማቀናጀቱ ስራ ገብተናል፡፡ ምክንያቱም ወደ ስምንት የሚሆኑ አዳዲስ ተጫዋቾች አሉን ፤ ከቀሩት ነባሮቹ ጋር አጣምረን ጥሩ ቡድን እንዲሆን ለማድረግ እየተዘጋጀን ነው ያለነው።”

ክለቡ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በተገቢው መንገድ ቢከውንም እንደ አዲስ አበባ እና ጣና ዋንጫ ባሉ የቅድመ ውድድር ፍልሚያዎች ላይ አልተሳተፈም። እርግጥ ቡድኑ አቋሙን ለመፈተሽ በተናጥል የወዳጅነት ጨዋታዎችን ቢያደርግም በጠቀስናቸው የፉክክር ጨዋታዎች አልተወዳደረም። የሆነው ሆኖ ግን ነሐሴ 5 ቡድኑ ከተሰበሰበ በኋላ የኒውትሪሽን፣ ሳይኮሎጂ እና የቅድመ ምርመራዎች ተደርገው ከሦስት ቀናት በኋላ መደነኛ ልምምዱን ጀምሯል። በዝግጅት ጊዜው እንደ ባለፈው ዓመት ከአሜሪካ ከመጡት ጎልደን ቡት አካዳሚ አሠልጣኞች ጋር የፊትነስ ስልጠናዎችን ሲወስድ የቆየ ሲሆን በአካባቢው ከሚገኙ የተለያዩ ስብስቦች ጋር እንዲሁም ከጌዲኦ ዲላ እና ከአዳማ ከተማ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርጓል። እንዳልነው ኮስተር ያለ ጨዋታ ባያገኙም ባለው ዕድል ነባር ተጫዋቾችን ከአዳዲሶቹ ጋር ለማዋሀድ እንደተጣረ አሠልጣኙ ይናገራሉ። “አዳዲሶቹን ከነባሮቹ ጋር እያጣመርን እያየን ነበርና ጥሩ ነገር ነው ያየነው። ቡድናችን ምን ላይ ነው ያለው እንዲሁም ምንድነው የሚቀረው የሚለውን በጨዋታዎቹ እያረጋገጥን ነበር። እስከ አሁን ባለው ነገር ላይ ቡድናችን የተሟላ ነው። በየትኛውም ቦታ ላይ በሁሉም ነገር ላይ ወጥ የሆነ ቡድን እንደሆነ ነው እያየን ያለነውና ይሄንን ደግሞ ወደ ውድድሩ ይበልጥ ለማምጣት እንጥራለን። በሁሉም መንገድ ግን ተጫዋቾቻችንን ባገኘናቸው ጨዋታዎች አይተናል።”

በመግቢያችን እንዳልነው ሀዋሳ ዓምና የወጥነት ችግር ነበረበት። እንደተገለፀው ከጉዳት እና ቅጣት ጋር ስብስቡ እየሳሳ መምጣቱ ዋነኛ ችግር እንደሆነ ቢታመንም ክፍተቱን ስብስብን በማስፋት ብቻ ግን እንደሚቀረፍ መገመት ልክ አይመስልም። አዕምሮዋዊ ጎዳዮችም የመዋዠቅ ነገሮች እንዳይከሰቱ መሰራት ይገባቸዋል። አሠልጣኙ ግን ዋናው ችግር የስብስብ ጥልቀት ስለነበር እርሱን በሚገባ ለመሸፈን ጥረናል ይላሉ። ከዚህ ባለፈ የመከላከሉም ሆነ በተገማች አጨዋወት የመጫወቱ ክፍተት ከተጫዋቾች ግዢ ምርጫ ጋር ተያይዞ የተቀረፈ ቢመስልም እርሳቸው እንዳሉት የቡድን ውህደት እስኪመጣ ግን ትንሽ ጊዜ ሊፈጅ ይችላል። “ይህ እግር ኳስ ነው፤ ጊዜ ሊወስድብን ይችላል። እነዚህ የመጡ አዳዲስ ተጫዋቾች በየክለቡ ጠንካራ የነበሩ ናቸው። በጨዋታዎች ምን አልባት ሶስት አራት ጨዋታ ላይ የምንፈልገውን ወጥ እንቅስቃሴ ላናገኝ እንችላለን። በዚህ መንገድ እየተቀናጁ ሲመጡ የተሻለ ቡድን ይኖረናል ብዬ ነው የማስበው።”

በሀዋሳ የዘንድሮ ስብስብ ውስጥ በርካታ ተጫዋቾች ተፅዕኖ ፈጣሪ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዋናነት ከአልጄሪያ የግማሽ ዓመት ቆይታ መልስ በሀገር ውስጥ ውድድር ካቆመበት የጎል ማምረት ብቃቱ ዓምና የቀጠለው ሙጂብ ቃሲም ዳግም በተቀላቀለው ክለቡም ይህንን አስቆጣሪነቱ እንደሚቀጥል ይታሰባል። ዓሊ ሱሌይማን እና ኢዮብ አለማየሁም ፍጥነታቸውን ተጠቅመው የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይጠበቃል። በመሐል ሜዳ ላይ ወንድማገኝ ኃይሉ እና በቃሉ ገነነ የተከላካይ አማካዩ ብርሃኑ አሻሞ መምጣት የሚሰጣቸው ነፃነት ለቡድኑ ትልቅ ግብዓት ነው። ከኋላም የላውረንስ ላርቴ እና በረከት ሳሙኤል ጥምረት ቡድኑን ጥንካሬ እንደሚያላብሰው ይታመናል።
ሀዋሳ ከተማ የ30 ሳምንታት ረጅሙን የሊግ ጉዞ የፊታችን እሁድ 10 ሰዓት ለአዲስ አዳጊው ክለብ ለገጣፎ ለገዳዲ ጋር የሚያደርግ ይሆናል።

የሀዋሳ ከተማ የ2015 ሙሉ ስብስብ

ግብ ጠባቂዎች

1 መሀመድ ሙንታሪ
30 አላዛር ማርቆስ
45 ምንተስኖት ጊንቦ

ተከላካዮች

26 ላውረንስ ላርቴይ
7 ዳንኤል ደርቤ
14 መድኃኔ ብርሃኔ
4 ፀጋሰው ዮሐንስ
3 አቤኔዜር ኦቴ
16 ሰዒድ ሀሰን
15 በረከት ሳሙኤል
5 ሰለሞን ወዴሳ
24 ፍቃደሥላሴ ደሳለኝ
28 ታምራት ተስፋዬ
32 ሚኪያስ ታምራት
34 ፋሲል ጌራሞ

አማካዮች

6 ብርሃኑ አሻሞ
8 በቃሉ ገነነ
18 ዳዊት ታደሰ
19 አቤኔዘር ዮሐንስ
29 ወንድማገኝ ኃይሉ
13 አልዱልባሲጥ ከማል
22 ብሩክ ዓለማየሁ
2 አስችሎም ኤልያስ
22 ኤርሚያስ በላይ

አጥቂዎች

11 ቸርነት አውሽ
20 ተባረክ ሂፋሞ
21 ኤፍሬም አሻሞ
25 ኢዮብ ዓለማየሁ
9 ሀብታሙ መኮንን
27 ምንተስኖት እንድሪያስ
12 ብሩክ ኤልያስ
17 ሙጅብ ቃሲም
10 አዲሱ አቱላ
23 ዓሊ ሱሌይማን
35 ሀብታሙ ገነነ

የአሠልጣኞች ቡድን አባላት

ዋና አሠልጣኝ – ዘርዓይ ሙሉ
ምክትል አሠልጣኝ – ብርሃኑ ወርቁ
ምክትል አሠልጣኝ – ገረሱ ሸመና
የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ – አዳሙ ኑማሮ
የህክምና ባለሙያ – ሂርጳ ፋኖ
የቡድን መሪ – ብርሃኑ ቴዳሞ