ሻምፒዮኖቹ የአራት ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ውል አድሰዋል

የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ የሆኑት ንግድ ባንኮች የወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን ውል ሲያድሱ አንድ ተጫዋቾችም ወደ ስብስባቸው ቀላቅለዋል።

በአሠልጣኝ ብርሃኑ ግዛው የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ2014 የሴቶች ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ከሆነ በኋላ በሴካፋ የቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ ውድድር ላይ ከመካፈሉ በፊት ናርዶስ ጌትነት፣ ብርቄ አማረ፣ መሳይ ተመስገን እና አርየት ኦዶንግ ያስፈረመ ሲሆን በዛሬው ዕለት ደግሞ ከአዲስ አበባ ከተማ ተከላካዩዋ ሀና ተስፋዬን በ2 ዓመት ውል ማስፈረሙ ተረጋግጧል።

ከዚህ ውጪ ክለቡ የአራት ነባር ተጫዋቾችን ውልም ማደሱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። የመጀመሪያዋ ተጫዋች ክለቡን 2011 ላይ የተቀላቀለችው ብዙዓየሁ ታደሰ ነች። ያለፉትን አራት ዓመታት በመስመር ተከላካይነት የተጫወተችው ብዙዓየሁ በቀጣዮቹ 2 ዓመታትም በክለቡ ለመዝለቅ ፊርማዋን አኑራለች። ከእርሷ በተጨማሪ የአጥቂ አማካዩዋ አረጋሽ ካልሳም በባንክ ቤት ለአራት ዓመት የምትቆይበትን የሁለት ዓመት ውል ፈፅማለች።


እንደ አረጋሽ ሁሉ 2013 ላይ የባንክን መለያ መልበስ የጀመረችው ሰናይት ቦጋለ እና ሌላኛዋ የአማካይ መስመር ተጫዋች ብርቱካን ገብረክርስቶስም በቅደም ተከተል የሁለት እና አንድ ዓመት ውል በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ተገኝተው ተፈራርመዋል።

ከክለቡ ጋር በተያያዘ የዝውውር ዜና በቅርቡ አንድ ወይም ሁለት ውጪ ሀገር ተጫዋቾች በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። ከዚህ በተጨማሪም ከሀገር ውስጥ ሁለት ተጫዋቾች ለማስፈረም እየጣረ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።


ንግድ ባንክ ከሳምንታት በፊት ከኢትዮ ኤሌክትሪክ አማካዩዋን ንቦኝ የን አስፈርሞ በአህጉራዊ ውድድር ለመሳተፍ ቢጥርም ተጫዋቿ ለቀናት የሚቆይ ውል ስለነበራት ውሉ ሳይፀና ቆይቶ አሁን በይፋ የስብስቡ አካል እንዳደረጋት ታውቋል።