ሪፖርት | ሠራተኞቹ የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ሦስት ነጥብ የግላቸው አድርገዋል

በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማዎች በጌታነህ ከበደ ድንቅ የቅጣት ምት ጎል አርባምንጭ ከተማን በመርታት ዓመቱን በድል ጀምረዋል።

በአዲሱ አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እየተመሩ የውድድር ዓመቱን የጀመሩት ወልቂጤ ከተማዎች በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ካስፈረሟቸው 16 ተጫዋቾች ውስጥ ፋሪስ አላዊ፣ ተስፋዬ መላኩ፣ ቴዎድሮስ ሀሙ፣ ሳሙኤል አስፈሪ፣ አስራት መገርሳ፣ ብዙዓየሁ ሰይፈ፣ አፈወርቅ ኃይሉ፣ አቤል ነጋሽ እና ተመስገን በጅሮንድን በቋሚ አሰላለፍ አስገብተዋል። በተቃራኒው አርባምንጭ ከተማዎች ከአዳዲስ ፈራሚዎቻቸው አዩብ በቀታ፣ አካሉ አትሞ፣ ኢማኑኤል ላርዬ እና ተመስገን ደረሰን ተጠቅመው ጨዋታውን ቀርበዋል።

ጨዋታው ገና በተጀመረ በ4ኛው ደቂቃ አርባምንጭ ከተማዎች እጅግ ግልፅ የግብ ማግባት አጋጣሚ አግኝተዋል። በዚህ ደቂቃም ወልቂጤ ከተማዎች በተዘናጋ ሁኔታ ያደረጉትን የኳስ ቅብብል ስህተት ተመስገን ደረሰ አግኝቶት ወደ ሳጥን ሲልከው ያገኘው እንዳልካቸው መስፍን በወረደ አጨራረስ ዕድሉን አምክኖታል። በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻለ ድርሻ በመውሰድ መጫወት የያዙት ወልቂጤ ከተማዎች በ7ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ከርቀት አክርሮ በመታው የቅጣት ምት የመጀመሪያውን ዒላመውን የጠበቀ ጥቃት ሰንዝረው ተመልሰዋል።

አርባምንጭ ከተማዎች በበኩላቸው በርከት ያለውን ደቂቃ ከኳስ ውጪ በመሆን ቀጥተኝነት የተሞላበት የማጥቃት አጨዋወት ቢከተሉም ከግማሽ ሰዓት በኋላ የኳስ ቁጥጥሩን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት ቀጥለዋል። በ4ኛው ደቂቃ ከፈጠሩት የግብ ዕድል በኋላም በ37ኛው ደቂቃ ሌላ ለግብ የቀረቡበትን አጋጣሚ አግኝተዋል። በዚህም እንዳልካቸው መስፍን ከወደ ግራ ካደላ የሳጥኑ ክፍል ያገኘውን ኳስ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ነበር።

ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ያለ ሙከራ የዘለቀው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በአጋማሹ መገባደጃ ላይ ተከታታይ ሁለት ጥሩ ጥሩ ጥቃቶች ተስተናግደውበታል። በቅድሚያም በ39ኛው ደቂቃ የወልቂጤ ከተማው የመሐል ተከላካይ ውሀብ አዳምስ ከመዓዘን ምት የተሻማን ኳስ በመጠቀም ግብ ለማስቆጠር ጥሮ ነበር። ከደቂቃ በኋላም የቡድን አጋሩ አፈወርቅ ኃይሉ ከሳጥኑ ጫፍ የመታው ኳስ በተከላካዮች ተጨርፎ ለጥቂት ከግብነት ተርፏል። አጋማሹም ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከእረፍት መልስ ጨዋታው ግብ ለማስተናገድ ብዙ ደቂቃዎች አልፈጁበትም። በ50ኛው ደቂቃም በርናንድ ኦቺንግ ብዙዓየሁ ሰይፈ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ጌታነህ ከበደ በድንቅ ሁኔታ በቀጥታ መረብ ላይ አሳርፎት የቡድኑን እና የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ግብ በስሙ አስቆጥሯል።

ግብ እንዳስተናገዱ ወዲያው የሦስት ተጫዋቾችን ለውጥ አድርገው ወደ ጨዋታው ለመመለስ የጣሩት አርባምንጭ ከተማዎች በ56ኛው ደቂቃ አንደኛው ተቀይሮ የገባው መላኩ ኤሊያው የግብ ዘቡ ፋሪስ ክልሉን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ ወደ ግብ በመታው ኳስ አቻ ሊሆኑ ነበር። ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ሌላኛው ተቀይሮ የገባው አህመድ ሁሴን ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ ለመጠቀም ጥሮ መክኖበታል። በሁለቱ ሙከራዎች መሐል ግን ለግቡ መገኘት ምክንያት የሆነው ብዙዓየሁ ሳጥኑ ጫፍ በመሆን ያገኘውን ኳስ በቀኝ እግሩ ሞክሮት ጨዋታውን ለመግደል አስቦ ለጥቂት ወጥቶበታል።

አዞዎቹ ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት ከተጫዋች ጀምሮ የአደራደር እና የሚና ለውጦችን ቢያደርጉም የሠራተኞቹን የኋላ መስመር ሰብሮ መግባት አልቻሉም ነበር። 89ኛው ደቂቃ ላይ ግን አሸናፊ በሳጥኑ የቀኝ መስመር ጥሩ የአቻ ማድረጊያ ዕድል ቢፈጥርም ሳይሰምርለት ቀርቷል። ጨዋታውም አንድ ለምንም በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

በጨዋታው ድል ያደረጉት የወልቂጤ ከተማው አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ቡድናቸው ላይ መጠነኛ የውህደት ችግር ቢኖርም በዛሬው ጨዋታ ያሳኩት ድል በሥነ-ልቦናው ረገድ ትልቅ ጥቅም እንደሚሰጣቸው ከጨዋታው በኋላ በነበራቸው የድህረ-ጨዋታ አስተያየት ተናግረዋል።

አጀማመራቸው እንዳሰቡት ባይሆንም በቀጣይ አፈፃፀማቸው እንደሚያምር የገለፁት አሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ በበኩላቸው በጨዋታው የታየውን የማጥቃት ኃይል በቀጣይ እንደሚያሻሽሉ አስረድተው በውድድር ዓመቱ ከ1-6 ያለውን ደረጃ ይዞ ለመፈፀም ሀሳብ እንዳላቸው ገልፀዋል።